Site icon ETHIO12.COM

“ረሃብን እየነገደ ሞት የሚያተርፈው ጁንታ እስከወዲያኛው ይቀበራል”

ህልውናው ያለ ተቃርኖ መቆም የማይችለው የጥላቻው ፊታውራሪ ባንዳ መኖር የሚችለው የሚያናቁር ፣ የሚያጠላ እና የሚያጋድል ሴራ ሲኖር ብቻ መሆኑ – ክፉነቱን ከጋኔልም ከፍ ያደርገዋል።

“ራስ መውደድ ያባት ነው” ያስብል ይሆናል።ነገር ግን “መኖር የምችለው በሌሎች መጎዳትና መጎስቆል ብሎም መሞት ነው” ብሎ ማመን ግን እጅጉን አሳዛኝና ከሰብዓዊ እሳቤ ያፈነገጠ መረን የለሽ ዕብደት ነው።

ከሃዲው ባንዳ ይህንን እሳቤ ነው እንግዲህ “ዓላማዬ” የሚለን።

በዚህ ስሁት እሳቤው በመንበረ-ስልጣኑ ጊዜ ያደረገብን ሳያንስ – ታሪኩ በአሳፋሪ ውርደት አክትሞም ብዙ ብዙ ሆኖ ካበቃም በኋላ – የትግራይ ህዝብን ተከልሎ አሁንም የትርጉም አልባ ዕልቂትና ማባሪያ የሌለው የሞት ነጋሪት በገዛ ህዝቡ ላይ በመጎሰም ላይ ይገኛል።

ምንም የማያውቁ ህፃናትን አዕምሮ በክፉ ሴራው እየቆለመመ ፣ የየዋህ አርሶ አደሩን ዕምነት የገራው ልቦናን በክፋት መርዙ በለወሰው ሴራ እየቀየረ ወደ ሞት መሸኘቱን ስራዬ ብሎ ተያይዞታል።
ከእንግዲህ ግን ያበቃለታል።

ይህ ልጅ ሳለን በተረት እንሰማው የነበረን የ”ጭራቅ” ገፀ-ባህሪን መተወን እንደ ጀብዱ የሚቆጥርና አቅሎን ስቶ በክህደት ያበደ ሽብርተኛ ተደጋጋሚ “የማሪያም መንገድ” ቢሰጠውም – “ኢትዮጵያ እስካለች እንቅልፍ የለኝም” ብሏልና ከእንግዲህ የእስከወዲያኛው መቃብሩ ተዘጋጅቶለታል።

እነርሱ እንዳሻቸው የሚዘርፉበት ስልጣን እስካሊያዙ – እንኳንና የህዝብ ሰላምና ደህንነት ግድ ሊላቸው – ህዝብ ማገዶ ሆኖ በእሳቱ መሞቅ የማይሰቃቸው የደም ጥማት ያሰከራቸው ናቸውና ለእነዚህ ከእንግዲህ አንዳችም መፈናፈኛ መስጠት አደጋው የትየለሌ መሆኑ ግልፅ ሆኗል።

ለዚህም ይመስላል የኃጢያት ነውራቸው ቁልል በሀገሩ ጉዳይ ቀልድ የማያውቀውን በሌላ መልኩ ደግሞ ፍቅር የሚገዛው ደግና አዛኙን ብሎም ቅንና አስተዋዩን የኢትዮጵያ ቁጣ እንደ እቶን ያንቀለቀለው።

ወጣቱም “ለኢትዮጵያ እዘምታለሁ።የትም፣መቼም፣በምንም!!” ብሎ ይኸው ሰሞኑን በፋመ፣በጋመና እውነትን ባለ ታላቅ የሀገር ፍቅር ስሜት ሲተም የምናየው እንዲሁ አይደለም።

የምናከብራቸው አስተዋይና ጥበብ ያላቸው የሀገር ዋርካ አዛውንቶች፣ሽማግሌዎች ማህበረሰባዊ ሃላፊነት የሚሰማቸው አባቶች ከውስጥ በመነጨ ሀዘንና ቁጭት ልጆቻቸውን ፈቅደውና ወደው ስለ ሀገራቸው ሳግ በሚተናነቀው ምርቃት እየሸኙ የምናየው ስለ ኢትዮጵያችን ነው።

አሁን ኢትዮጵያዊያን ሁሉንም መርምረው አይተዋል።ሀቁ እንደ ማለዳ ምንጭ ጥርት ብሎ ታይቷቸዋልና የሽብርተኛው ወያኔ ፋይል የሚዘጋበት ዕለት ሩቅ አይደለም።

ጀግናው መከላከያ ሰራዊቱ ደግሞ በህዝቡ ማዕበላዊ ድጋፍ፣በወጣቱ ወኔና በአጠቃላይ ሀገራዊ ንቅናቄው ሞራል፣እልህ፣ወኔውና ጀግንነቱ በዕጥፍ ድርብ ተመንድጓል።

እናም “ረሃብን እየነገደ ሞትን የሚያተርፈው ጁንታ እስከወዲያኛው ይቀበራል”
ኢትዮጵያም በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ እስከወዲያኛው በክብርና ኩራት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረች ትቀጥላለች።
“ኢትዮጵያ አሸንፋለች”

ሻምበል አስቻለው ሌንጫ ENDF Facebook

Exit mobile version