Site icon ETHIO12.COM

መከላከያ አሳሰበ፤ ልሽርፍራፊ ሳንቲም ” ሰበር” የሚሉትን አስጠነቀቀ፣ ለጠላት መረጃ ማቀበል፣ ምስል መለጠፍና ማሰራጨት እንዲቆም መከረ

ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅት ጥንቃቄ የሚያሻው ነው። የሚታየው ግን ለተራ ሳንቲም ለቀማ፣ ወዳጅ መስሎ የባንዶችን ዓላማ ማሰራጨት፣ በወገን ላይ ሽብር መልቀቅ፣ ጠላት ሆን ብሎ የሚያሰራሸውን መረጃ ማራገብና ማዳረስ፣ “አንድ ከፍተኛ የጦር መኮንን ጋር ደውዬ” እየተባለ ስሜት ማውራትና ለጠላት ፕሮፓጋንዳ መመቻቸት፣ ጠላት አሸነፈ ብሎ በሰበር ዜና ማወጅ፣ ትንሽ ጉዳይ ይዞና በየፌስ ቡክ የሚለጠፈውን ሃሜት ማራገብ፣ ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ከምትጠየፋቸው ጉዳዮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

ጠላት ተናቦና በአንድ የመረጃ ፍሰት ውስጥ በፈጠራና በተደራጀ ፕሮፓጋንዳ ሊያፈርስ ሲነሳ፣ የተቀረው ክፍል ተደራጅቶ የጠላትን ሴራ ማክሸፍ ሲገባው ለሳንቲም ለቀማና ለተራ የእለት ከርስ የተለቀለቀውን ሁሉ እያሰራጨ በአገሩ ላይ ገመድ ያጠብቃል። የወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በምስል በማሰራጨት መረጃ ይሰጣል። መንግስት የተኩስ አቁም ላይ ሆኖ በመከላከል የሚወስደውን እርምጃ እያጋለጠ ያሳጣል። አንዳንድ የተቀዋሚ ፓርቲ አመራሮች ወደ ጦር ግንባር ሄደናል ብለው ለፖለቲካ ፍጆታ የግንባር መረጃዎችን በማህበራዊ ሚዲያ ያራባሉ። ደጀኑ ሕዝብ የሚሰጠውን ድጋፍ ያሳያሉ። በዚህና በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ መከላከያ ይህንን ብሏል። እንዳለ አቅርበነዋል።

ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ በሚችለው ሁሉ ከሠራዊቱ ጎን በመቆም “ኢትዮጵያ ፈረሰች” ብለው ያሻቸውን በህዝቡ ላይ ለመፈፀም ያሰፈሰፉ የውስጥ ቅጥረኞች ፣ ባንዳዎች እና የኢትዮጵያ ልማት የራሳቸው ጥፋትና ውድቀት የሚመስላቸው የውጭ ጠላቶችን በማሳፈር ላይ እደሚገኝ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ገለፀ።

የውስጥና የውጭ ጠላቶች የህዝቡን ስነ-ልቦና ለመስለብና የተፈጠረውን አንድነት ለማፍረክረክ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የስነ-ልቦና ጦርነት አጠናክረው መቀጠላቸውንም ሁሉመ ኢትዮጵያውያን ልረዳው ይገባል ብሏል፡፡

ህዝቡ የሠራዊቱ የማይነጥፍ አስተማማኝ ደጀን በመሆን በሎጂስቲክስ ድጋፍ ፣ ከዳር እስከ ዳር በመነቃነቅ በሰው ሃይል ሰራዊቱን በማጠናከር ታሪካዊ ሀገርን የማዳን ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሶ:”ለዚህ የህዝባችን የማይነጥፍ ድጋፍ የድላችን ቁልፍ በመሆኑ እናመሰግናለን”ብሏል፡፡

ይህ ለሰራዊቱና ለመላው ህዝብ ከፍተኛ የሞራልና ስነ-ልቦና ከፍታ ያሳየ በመሆኑ በጠላት በሀገር ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋን ለመሻገር ሁሉም ዜጋ ከመቼውም ግዜ በላይ መተባበር ፣ ጠላት ከሚነዛው አሉባልታ ወሬ ራስን መጠበቅ ፣ አንድነት እና ህብረትን ማጠናከር ወቅቱ የሚጠይቀው አብይ ጉዳይ መሆኑም ተገልጿል።

በመላው ኢትዮጵያ ህዝብ የታየው ህብረትና በአንድነት መቆም ጠላቶቻችንን አስደንግጧል ያለው መከላከያ ሰራዊት የአሸባሪው ጁንታ ጎራ በፍርሃት እንዲርድ ማድረጉንም አስታውቋል፡፡

ይህ ቢሆንም የህዝቡን አንድነትና ፅናት ለመሸርሸር ጠላት እየፈበረከ የሚረጨው አሉባልታዎችን መከላከል ፣ ሳያውቁ ጠላት ሆን ብሎ የሚለቀውን አሉባልታ በመቀባበል የጠላት ወኪል የሚሆኑ ወገኖችን መምከርና መገሰፅ አስፈላጊ መሆኑም ተገልጿል።

በአሸባሪው ህወሓት እየተፈበረኩ በማህበራዊ ሚዲያ የሚረጩ የውሸት መረጃዎችን ፣ በየአገልግሎት መስጫዎች የሚነዙ አሉባለታዎች ፣ ስለ ሠራዊቱ የግዳጅ ውሎ ሰው የሚቀባበለው ወሬ ለጠላት ግብዓት የሚሆኑና የወገንን እንቅስቃሴ የሚጎዱ በመሆናቸው ማህበረሰቡ ቀጥሎ የተዘረዘሩ ጉዳዮችን በማህበራዊ ሚዲያ እርስ በርስ አለመቀባበልና እና እንዳይጋራ ወይም ሼር እንዳያደርግ አሳስቧል፡፡

1.የመረጃ ምንጩ ያልታወቁ ቀልብ የሚስቡ መረጃዎችን ሼር ከመድረግ መቆጠብ፤

2.የሠራዊቱን ከቦታ ቦታ እንቅስቃሴ ፣ የሚጓጓዙ የጦር መሳሪያዎች አይነትና ብዛት ፣ የሎጂስቲክስ ድጋፍ እንቅስቃሴዎችን ፎቶ በማንሳት በማህበራዊ ሚዲያ አለመለጠፍ፡፡ ይህን የሚፈፅም ከተመለከቱም ማስቆም፡፡ ፍቃደኛ ካልሆነ ለፀጥታ ሃይሎች ወዲያው መጠቆም፡፡

3.በመንግስት በተወሰነው የተናጠል ተኩስ አቁም ወቅት የሚደረግ የጠላትን ትንኮሳ መከላከል ሥራ በማህበራዊ ሚዲያ አለመለጠፍ፤

4.አንዳንድ ዩ-ቲዩበሮች ለሽርፍራፊ ሳንቲም ብለው ሰበር ! ሰበር ! እያሉ ምንጩ ያለታወቀና ያልተረጋገጠ አሉባልታ በመንዛት የወገንንና የሀገርን ጥቅም አሳልፍው ለጠላት አለመስጠት፤

5.ወቅታዊ ወታደራዊ እንቅስቃሴን በሚመለከት በታወቀ መንግስታዊ ወይም በሚመለከተው የመከላከያ ሃላፊ ወይም አዛዥ ያልተሰጠ መረጃ ከሆነ አለማመንና ሼር አለማድረግ፤

6.ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ በሰራዊቱ ግዳጅ አፈፃፀምና በህዝብ ሞራልና ስነ-ልቦና የበላይነት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩና ጠላት ሆን ብሎ የሚለቃቸውን መረጃዎች ባለማሰራጨት መተባበር እንደሚገባ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ አሳስቧል።


Exit mobile version