ጠላቶቿ ፈርሰው ያልቃሉ እንጂ ኢትዮጵያ መቼም አትፈርስም፤ አዲስ አበባም ከሰላማዊ የብልፅግና ጉዞዋ አትስተጓጎልም!

ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ለበርካታ ጊዜያት ከውጭ ጠላቶች ወረራ እና መሰል ጥቃቶች ተሰንዝሮባታል፤ ሁሉንም የውጪ ወረራ እና ጥቃቶችን በጀግኖች ልጆቿ በመመከት ጠላትን አሳፍራ መመለስ የቻለች ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ ከአብራኳ የወጡ ከሃዲዎች እና ባንዳዎች ከውጭ ጠላት ጋር በማበር ሲያደሟት የነበሩ መሆኑን ከታሪካችን እንረዳለን።

አሁን ባለንበት ዘመን አገራችን እና ሕዝቦቿን አዋርደው ከኖሩት ድህነት፣ ብልሹ አስተዳደር እና አፈና በማላቀቅ ብልጽግና፣ ነፃነት እና እኩልነትን መዳረሻችን በማድረግ በመደመር መንገድ በመረባረብ ላይ በምንገኝበት ወሳኝ ወቅት ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እና የውስጥ ባንዳዎች በመቀናጀት ሀገራችንን ለማፈራረስ እየተረባረቡ ይገኛሉ።

በእርግጥም ይህ ወቅት ለኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ለጠላቶቻችን ወሳኝ ወቅት ነው። በያዝነው ዓመት መገባደጃ የሀገራችንን ታሪክ የሚቀይሩ ሁለት ታላላቅ ኹነቶች እውን ይሆናሉ።

አንደኛው ሀገራችን በታሪኳ ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ ሕዝቦቿ ወድደው እና ፈቅደው በመረጡት መንግሥት ለመተዳደር የሚወስኑበት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ድህነትን እና ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ከሀገራችን ጫንቃ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማውረድ እጅግ ወሳኝ መነሻ እና የብልጽግናችን ነፀብራቅ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከውስብስብ የአፈፃፀም ችግሮች ተላቅቆ ሁለተኛው ሙሌት የሚከናወንበት እንዲሁም ኃይል ማመንጨት የሚጀምርበት ወቅት ነው።

እነዚህ ታላላቅ ኹነቶች ለኢትዮጵያ እጅግ ወሳኝ ስለመሆናቸው እኛ ብቻ ሳንሆን ጠላቶቻችንም ጠንቅቀው ያውቁታል። ለዚህም ነው ያለ የሌለ ኃይላቸውን በማረባረብ ከብልጽግና ጉዟችን ሊያደናቅፉን ሌት ተቀን የሚሠሩት። እነዚህ ታላላቅ እና ታሪካዊ ኹነቶች ከተሳኩ ለሀገራችን ብልጽግና ጠንካራ መሠረት ከመሆናቸውም በላይ በየትኛውም የውስጥ እና የውጭ ጠላት ሴራ ሸብረክ የማትል፣ በሁለንትናዊ ጥንካሬዋ ለአፍሪካ ተምሳሌት የምትሆን፣ የበለፀጉ ሀገራትን ምፅዋት የማትመለከት ኢትዮጵያ እውን እንደትሆን እኛ ብቻ ሳንሆን ጠላቶቻችንም ጠንቅቀው ይረዱታል።

ሀገራችን እነዚህን ኹነቶች እውን ማድረግ ካልቻለች ደግሞ ድህነቷ ስር እየሰደደ ለውስጥ እና ለውጭ ጠላቶች የተጋለጠች፣ በቀላሉ የምትፈራርስ ሀገር ትሆናለች። ጠላቶቻችን በውል ስለሚያውቁ ኢትዮጵያ አሁን ካላፈራረስን መቼም አይሳካልንም ብለው እየተረባረቡብን ይገኛሉ። የዘመናችን ባንዳዎች ደግሞ ከሀገር ይልቅ የውጭ ጠላቶች ፍርፋሪ ይበልጥብናል ብለው በክህደት ተሰልፈዋል።

ሕወሓት እና ሸኔ ከላይ የተጠቀሱ ፀረ-ኢትዮጵያ እኩይ ዓላማዎችን ለማሳካት በክህደት የተሰለፉ ሲሆን በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በሽብር ተግባራት በመሰማራት የሉዓላዊነታችን ዋልታ እና ማገር በመሆነው መከላከያ ሠራዊታችን እና በዜጎቻችን ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ፈፅመዋል፤ እየፈፀሙም ይገኛሉ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እነዚህን የሽብር ቡድኖች በሽብርተኝነት መፈረጁ በተገቢው ስማቸው መጥራቱ በመሆኑ ትክክለኛ እና ተገቢም ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በስም የተለየ፣ በገቢር ግን አንድ የሆነው የክህደት ቡድን “ስለ አዲስ አበባ ዝም አንልም” በሚል መፈክር 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በሽብር በማደናቀፍ ሕጋዊ መንግሥት በኃይል በማስወገድ የውጭ ጠላቶቻችን ተላላኪ የሆነ አሻንጉሊት መንግሥት ለመመሥረት እየተራወጠ ይገኛል።

የሀገራችን እና የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባችን ላለፉት 30 ዓመታት የመንግሥት መሬት በጁንታው እና ተከታዮቹ ሲዘረፍ፣ የኮንዶሚኒየም እና የመንግሥት ኪራይ ቤቶች ከሕግ ውጭ ለጁንታው ቤተሰቦች ሲቸበቸቡ፣ የሕዝብ ሀብት እና ንብረት እየተዘረፈ ባለቤት አልባ ሕንፃዎች በመዲናችን ሲቆሙ ድምፃቸውን ያልሰማነው ባንዳዎች ዛሬ ከዘራፊዎች እየነጠቅን ደሃውን የከተማችን ነዋሪን የቤት ባለቤት ማድረግ ስንጀምር ከለውጡ ማግስት ጀምሮ አዲስ አበባን ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ የሚችሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ፍፃሜ እያገኙ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ እና ኢ-ፍትሐዊ እና አድሎአዊ አሠራሮች እየተስተካከሉ፣ ከተማችንን ለነዋሪዎቿ ምቹ ማድረግ ስንጀምር “ስለ አዲስ አበባ ዝም አንልም” በሚል መፈክር ወደ ሽብር ተግባር የገቡ አጥፊ ቡድኖች እየጮኹ ያሉት ስለሆዳቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ሕዝብ ይገነዘባል።

አዲስ አበባ የጥፋት ማዕከል እንድትሆን ሌት ተቀን እየሠሩ እና ዋናው ተልእኳቸውም አዲስ አበባ እስክትወድም፣ ኢትዮጵያም እስክትፈርስ አናርፍም ማለት ሆኖ ሳለ፣ “ስለ አዲስ አበባ ዝም አንልም” ማለት በነዋሪዎቿ ላይ በእጅጉ ማፌዝ ነው።

ለእነዚህ አካላት አንድ ግልጽ ሊሆን የሚገባው ነገር አዲስ አበባ የልማት ድግስ እንጂ የጥፋት ድግስ የሚሰናዳባት አትሆንም። ይህንን እኩይ ተግባር የከተማው ነዋሪዎች እና ከተማ አስተዳደሩ በፅናት ይታገለዋል።

በዚህ ፈታኝ ወቅት የውጭ ጠላቶቻችን እና ባንዳዎች የሸረቡብንን ሴራ በማክሸፍ ረገድ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት፣ የሀገር መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስ እና የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጄንሲ በመቀናጀት ለፈፀማችሁት እጅግ ውጤታማ ተግባር እጅግ የኮራንባችሁ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመግለጽ ይወዳል።

በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የምትገኙ ኢትዮጵያውያንም ለዚህ አኩሪ ተግባር ላበረከታችሁት አስተዋፅኦ ታላቅ ምስጋና ይገባችኋል፤ ኮርተንባችኋል።

ውድ የከተማችን ወጣት ሆይ፣ ለእኩይ ፍላጎታቸው ማስፈፀሚያነት የወጣትነት ጊዜህን ሊነጥቁህ እና መጠቀሚያቸው ሊያደርጉህ የሚታትሩ አካላት እና ግለሰቦችን በመለየት ዕውቀትህን፣ ጉልበትህን እና ጊዜህን ተጠቅመህ ራስህን፣ ቤተሰብህን፣ እና ሀገርህን እንድትደግፍበት አደራ እንላለን።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፊት ለፊታችን የሚጠብቁንን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እና ሁለተኛውን የታላቁ ሕዳሴ ግድባችንን ሙሌት በስኬት ለማጠናቀቅ በሚደረገው ርብርብ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ፣ መላው የከተማችን ሕዝብ እና በመላው ዓለም የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ታሪካዊ ስኬት ያለማሰለስ በመሥራት የሽብርተኞችን እንቅስቃሴ በመከታተል እና ለፀጥታ አካላት መረጃ በማቀበል የጠላቶቻችንን ሴራ በማክሸፍ ለአዲስ አበባችን ሁሉ አቀፍ ብልጽግና እና ለኢትዮጵያ ትንሣኤ የበኩላችሁን እንድታበረክቱ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
ሚያዝያ 30 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Leave a Reply