Site icon ETHIO12.COM

ሳማንታ ተመለሱ፤ “የሱዳን ኮሪዶር እንዲከፈት ጥያቄ አላቀረቡም”

ዘጠኝ ወራትን ያስቆጠረው የትግራይ ጦርነት አድማሱ እየሰፋ በመሄዱ አስቸኳይ ተኩስ ቆሞ አስቸኳይ ንግግር ሊደረግ እንደሚገባ አዲስ አበባ ደርሰው ወዲያው ወደ አገራቸው የተመለሱት የ(ዩ ኤስ አይዲ) ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ገለጹ። አስተዳዳሪዋ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን ማግኘት እንዳልቻሉም አመልክተዋል። ምክንያቱንም ተናግረዋል።

ከሰላምና ከጤና ሚኒስትር ጋር የተሳካ ያሉትን ውይይት ማድረጋቸውን ያስታወቁት አስተዳዳሪዋ በሱዳን የአራት ቀን ቆይታቸው ከሃላፊነታቸው ማዕቀፍ በመውጣት የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ሲደሰኩሩና ተጻራሪ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችን አንድ የማድረግ ስራ ሲሰሩ ነበር የቆዩት። ከሁሉም በላይ ግን እግራቸው ካርቱምን ከረገጠ ጀምሮ በቲውተር መልዕታቸው ሲረጩት የነበረው የዜና ግብዓት ድሮም ሆድ ብሶት ለነበረው የኢትዮጵያ መንግስት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነ ይመስላል።

ሳማንታ ፓዎር አዲስ አበባ ስለመግባታቸውም ሆነ ስለመሄዳቸው የመንግስት ሚዲያ ያለው ነገር የለም። ሱዳን በመሪዎች ደረጃ አቀባበል ተደርጎላቸው አራት ቀን የከረሙት እንግዳ አዲስ አበባ 24 ሰዓታት መቅመጥ አልቻሉም። ” ያልተገደበ የርዳታ ማስተላለፊያ ኮሪዶር እንዲፈቀድ ጫና ለማድረግ ወደ አዲስ አበባ አቀናለሁ” በሚል የጉዟቸውን ዋና ዓላማ ሲያስታውቁ ” ግልጽ የሆነ የተንኮል ወጥመድ” የሚል ምላሽ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዳኤታ ሬድዋን ተሰጥቷቸው ነበር።

ቀደም ሲል ጀምሮ አሜሪካ በያዘችው ያልተገባና ሚዛን ያጣ አቋም ደስተኛ እንዳልሆነ ሲገልጽ የቆየው የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ አሸባሪ አካል ጋር እንደማይደራደር አስተዳዳሪዋ አዲስ አበባ ከመግባታቸው በፊት ለሚያሰራጩት ቲውተር ምላሽ በሚመስል ደረጃ ግልጹ ተነግሯቸው ነበር። በዚህና በሌሎች ፍትህ የጎደላቸው አካሄዶች የተቋሰለውን ግንኙነት ተሸክመው ወደ አዲስ አበባ የመጡት ሳማንታ ያሰቡትን ያሳኩ አይመስልም።

በመግለጫቸውና በቲውተር ሃሳባቸው እጅግ ዲፕሎማሲ የተላበሰ መረጃ ቢሰጡም ” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ለማግኘት ሞክሬ ውጭ ናቸው በሚል አላገኘሁዋቸውም” የተሰጣቸው ምክንያት የገለጹበት አግባብ ደስተኛ እንዳልሆኑ አመላካች ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን ብዙ ትክክል ያልሆነ ወሬ እንደሚወራ መጠቆማቸው ምን አልባትም ጉብኝታቸውን አስመልክቶ ከህዝብ የሚሰራጭ የነበረውን መረጃ እንደሰሙ አመላካች ይመስላል።

ይህም ብቻ አይደለም

ለትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ለማቅረብ የትኛው ወደብ ይቀርባል? ሲል የፕሬስ ድርጅት በሁሉም ቋንቋ ባተመው ጽሁፍ “ለመቀሌ ከ1 ሺህ 306.8 ኪሎ ሜትር እና ከ398 ኪሎ ሜትር ርቀት የቱ ይቀርባታል?” ሲል የጠቀው ጥያቄ ለሳማንታ ቀርቦላቸዋል።

“አንድ አንድ ምዕራባዊያን አገራትና ተቋሞቻቸው ከሱዳን ወደ ትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ ለማጓጓዝ መተላለፊያ ኮሪደር ይከፈት ሲሉ መንግስት አጥብቀው ይጠይቃሉ።የአሸባሪው ህወሓት አመራሮችም በተለይም አፈቀላጤው ጌታቸው ረዳ እና ጻድቃን ገ/ትንሳኤ በሱዳን በኩል ለተረጂዎች እርዳታ ለማስገባት መተላለፊያ ኮሪደር ለማስከፈት መንግስት ላይ ጫና እንፈጥራለን ሲሉ መናገራቸውም ይታወቃል” ያለው ዜና “የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ሳማንታ ፓወር በተመሳሳይ ይህ ኮሪደር ይከፈት ዘንድ በአካባቢው ያለው የአማራ ሀይል ለቆ ይውጣ ሲሉ በግልጽ ተናግረዋል” ሲል ምክንያታማነቱን ያስረዳል።

“ለመሆኑ” ይላል ዜናው “ለመሆኑ ለትግራይ ክልል እርዳታ ለማቅረብ የትኛው ወደብ ይቀርባል” ሳማንታ ” አስቤው አላውቅም” ያሉት ሃቅ በሂሳብ ስሌት ነበር የቀረበላቸው።

“ታዲያ የጥያቄው ዓላማ ለተረጂዎች የሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ ብቻ ከሆነ እነዚህ አገራት እና ተቋሞቻቸው ለምን ሩቁን የፖርት ሱዳን ወደብ የሙጥኝ አሉ? እርዳታ ለማቅረብስ የቱ ይቀርባል” ሲል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያሰራጨው ቅድመ ጥያቄ ለሳማታን በወጉ በካርታ ተደግፎ እንደቀረበላቸው ስምተናል። ለዚህም ነው መሰል ” የኮሪዶር ክፈቱ” ጥያቄ እንዳልተነሳ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ሲናገሩ የተሰማው።

ከጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያና ከጤና ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ጋር ጥሩ የሚባል ውይይት እንዳደረጉ ያስታወቁት ሳማንታ ሕወሃት በሚያደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ በአማራ ክልል 150 ሺህ ሰዎች በአፋር ደግሞ 76 ሺህ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ቁጥርና ቦታ ጠቅሰው ተናግረዋል። እርዳታና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አስያውቀዋል።

አፈጻጸሙ እንዴት ይሆናል የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ግጭቱ ከትግራይ ወጥቶ እየሰፋ በመሆኑ ከዚህም ሳይብስ ወደ ንግግርና የሰላም መንገድ መመለስ እጅግ አስፈላጊና አገራቸው አሜሪካ ትኩረት የምትሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ማስታወቃቸው ከአንጀትና በሚዛናዊነት ከሆነ አግባብነት ያለው ጉዳይ ነው።

ከውይይታቸው በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ሳማንታ ፓወር “ለግጭቱ ወታደራዊ አማራጭ መፍትሔ እንደማይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይወቅ” ሲሉ በቁጣ ለተነሳው ኢትዮጵያዊ መልዕክት አስተላልፈዋል። ወታደራዊ ዘመቻ አማራጭ አይደለም ሲሉ ያቀረቡት የውይይት ሃሳብ ” መንግስቴን መርጫለሁ” ለሚለው ሕዝብ የሚሰተው ትርጉምም የታሰበበት አይመስልም። ለዚህም ነው ነገሩ ተንኮል ያዘለ በመሆኑ ሲተየዋ ሲገቡም ሲወጡም ዝም የተባለው።

አገራቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የወዳጅነት ስሜት እንዳላት፣በዚሁ መርህ የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰው በቀጠናው ኢትዮጵያ አስፈላጊያቸው መሆኗን አመልክተዋል።ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ” በመርህ ላይ የተመሰረተና በመከባበር አብረን ጥቅማችን ላይ እንስራ እንጂ እንዘዛችሁ ማለት አይቻልም” ሲሉ የገለጹት የአሜሪካ የጥቅም ሂሳብ ለዛሬው ፍትጊያ መነሻ ነው። ቀይ ባህር ላይ ሊተከል የታሰበውን ፕሮጀክት ለማምከንና የግብጽን የቤት ስራ ለመተግበር መላ ሲፈለግ ትህነግ ቅርብ የተገኘ አርጩሜ ሆነ። እናም የዚህ ሁሉ ቀውስ ዋና ምክንያት እየታወቀ ” ጦርነት መፍትሄ አይሆንም” ሲባል ማን ” ግፋ በለው” አለ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

ፓወር ውይይት ስለመጀመሩ ብቻ ሳይሆን ትህነግ ከማራና አፋር ክልል ለቆ እንዴወጣ፣ የአማራ እና የኤርትራ ኃይሎችም ከትግራይ ክልል ለቀው እንዲወጡ ሲጠይቁ በስህተት እንኳን የመከላከያን ስም አለማንሳታቸው አንድ ሚስጢር አሳብቋል። ኢትዮ12 ከሳምንት በፊት ትህነግ ወልቃይትን ጨምሮ የማንነትና የወሰን ችግር ባሉባቸው አካባቢዎች ሁሉ የፌደራል መንግስት እንዲያስተዳድር የድርድር ሃሳብ ማቅረቡን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም። በዚሁ የርቅ አሳብ ላይ በቦታዎቹና በማንነት ዙሪያ ያሉት አለመግባባቶች በውልና በመግባባት እስኪፈቱ የተፈናቀሉ ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ያስታውሳል። ይህ ዜና ይፋ በሆነ ማግስት አቶ ጌታቸው በጦር ሜዳ ድል እየቀናው መሆኑንን፣ ክፍ ቃል እንዳይናገሩ መመከራቸውን ጠቅሰው እስካሁን ወደ ቲውተር አልተመለሱም።

። በአፋር እና በአማራ ክልሎች በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ስለመፈናቀላቸው በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ ሳማንታ ፓዎር አመልክተው እርዳታ በኩል ደረጃ እንደሚያሻቸው በቲውተር አምዳቸው ገልጸዋል። ከቲውተር ዘመቻቸው በተለየ መልኩ በዲፕሎማሲ ቋንቋ መረጃ የሰጡት ፓዎር፣ ቀደም ሲል ለትግራይ የዕርዳታ አቅርቦት ከተለገሰው 149 ሚሊዮን ዶላር በተጨማሪ 45 ሚሊዮን ዶላር ለጤናና ሰብአዊ ድጋፍ ይውል ዘንዳ ለኢትዮጵያ መሰተቱን ይፋ አድርገዋል።

በሌላ በኩል ከሳማንታ ፓወር ጋር በተደረገው ውይይት ተጨማሪ የሰብዓዊ አገልግሎት መስመር እንዲከፈት የሚል ጥያቄ እንዳልተነሳ የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል መግለጻቸውን ቪኦኤ በድምጽ አሰምቷል።

የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ከሳማንታ ፓወር ጋር ከተወያዩ በኋላ በሰጡት መግለጫ መንግሥት የሰብዓዊ አገልግሎት በትግራይ ክልል ተደራሽ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ እና በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ለመረዳት ፓወር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው ደስተኛ መሆኑንም ነው ወ/ሮ ሙፈሪያት ተናግረዋል፡፡ እርዳታ በአግባቡ እንዲደርስ ካስፈለገ ትህነግ ከፀብ አጫሪ ድርጊቱ እንዲቆጠብ ጫና ሊደረግበት እንደሚገባ መንግሥት በውይይቱ ላይ ማሳሰቡን አመልክተዋል። ፓዎር ጉዳዩ የገባቸው እንደመሰላቸውም ተናግረዋል።

ከመንግሥት የተናጥል ተኩስ አቁም ውሳኔ በኋላ አሸባሪው ትህነግ በከፈተው ጥቃት ምክንያት በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ከአፋር እና ከአማራ ክልሎች ስለመፈናቀላቸውም ያነሱት ሚኒስትሯ፣ የሰብዓዊ አገልግሎት ድርጅቶች ከትግራይ ክልል በተጨማሪ እነዚህን ተፈናቃዮችም ሊደርሱ እንደሚገባ በውይይታቸው መነሳቱንም ጠቁመዋል፡፡ ፓዎርም ይህንኑ በቲውተር ገጻቸው አስፍረዋል።

Exit mobile version