Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ ንጹሃንን ጨፈጨፈ የ30ሺህ ተረጂዎች ቀለብ አቃጠለ

አሸባሪው ትህነግ ለ30 ሺህ ሰዎች የተዘጋጀውን የወር ቀለብ በማቃጠል ጸረ-ሕዝብነቱን እንዳሳየ የአፋር ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

አሸባሪው ትህነግ በአፋር ክልል ፈንቲ-ረሱ ዞን ጋሊኩማ ቀበሌ ለ30 ሺህ ሰዎች የወር ቀለብ የሚሆን የተለያዩ ምግብ ነክ ቁሳቁስ በከባድ መሣሪያ በመምታት ጸረ-ሕዝብነቱን እንዳሳየ የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

በፈንቲ-ረሱ ዞን አሸባሪ ቡድኑ በፈጸመዉ ወረራ ከቤት ንብረታቸው ከተፈናቀሉ 76 ሺህ በላይ ሰዎች ውስጥ ከ55 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ መቻሉን ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል።

በጽሕፈት ቤቱ የቅድመ- ማስጠንቀቅና ፈጣን ምላሽ ዳይሬክተር አቶ አይዳሂስ ያሲን ለኢዜአ እንደተናገሩት ቡድኑ በክልሉ ፈንቲ-ረሱ ዞን በፈጸመው ወረራ አሰከፊ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት እያደረሰ ነው።

“በክልሉ ፈንቲ-ረሱ ዞን የጀመሩትን ጦርነት የክልሉ ልዩ ኀይልና መከላከያ ሠራዊት ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ እየወሰደበት ባለው እርምጃ መቆሚያ መቀመጫ አሳጥቶታል” ብለዋል።

በዚህም አሸባሪ ቡድኑ ነገሮች እንዳሰበው ቀላል እንዳልሆነለት ሲረዳ በተሰፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ገብቶ የተለያዩ የሽብር ተግባራትን በአፋር ክልል ንጹሃን ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ በአርብቶ አደሮች ላይ የጭካኔ ድርጊት በመፈጸም ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።

“ከዚህም መካከል ትናንት በክልሉ ፈንቲ-ረሱ ዞን ጉሊና ወረዳ ጋሊኩማ ቀበሌ በከባድ መሳሪያ በመታገዝ ጭምር ባደረገው ድብደባ ለ30ሺህ ሰዎች የሚሆን በመካዘን የነበረ የተለያዩ የምግብና የፍጆታ እቃዎችን አቃጥሏል” ብለዋል።

ትናንት ማታ በከባድ መሳሪያ ካቃጠለው ንብረት ውስጥ በጋሊ ኮማ ቀበሌ መጋዘን ውስጥ 250 ኩንታል ዱቄት፣ 68 ካርቶን ዘይት፣ 199 ካርቶን ተምር፣200 ካርቶን ፋፋ፣ 180 ካርቶን ብስኩትና ወተት እና 10 ቦንዳ ልብስ ይገኙበታል”ብለዋል።

ይህም በአካባቢዉ በግጭቱ ለተፈናቀሉ 30 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች ለመስጠት የተዘጋጀ የእርዳታ እህል መሆኑንም ተናግረዋል።

“ቡድኑ እየደረሰበት ያለውን ጥቃት መቋቋም ሲያቅተው በተስፋ መቁረጥ ስሜት ባደረሰው የጭካኔ ድርጊት ለአፋር ሕዝብ ያለውን ድብቅ ጥላቻ ግልጽ ያወጣ ተግባር አሳይቷል” ብለዋል

በአፋር ክልል በፈንቲ ራሱ አሸባሪ ቡድኑ በከፈተው ትንኮሳ 76 ሺህ በላይ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን በ9 መጠለያ ተጠልለው እንደሚገኙም አቶ አይዳሂስ ገልጸዋል።

“እስካሁን ለተፈናቃዮቹ በአጠቃላይ 8 ሺህ 656 ኩንታል ሰብዓዊ ድጋፍ ተደርጓል” ያሉት ዳይሬክተሩ ቀጣይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮች እገዛ ለማድረግ ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመሆን ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ)

Exit mobile version