Site icon ETHIO12.COM

ሱዳን በኢትዮጵያ ያሉ አምባሳደሯን መጥራቷ ተሰምቷል

ሱዳን ትግራይ ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነትን ለማምጣት የጀመረችውን ጥረት አዲስ አበባ አሻፈረኝ ማለቷን ተከትሎ ለምክክር በሚል በኢትዮጵያ ያሉ አምባሳደሯን መጥራቷ ተነግሯል።

የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒንስቴር መስሪያ ቤት እንዳስታወቀው ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ እና የኢጋድ አባል ሀገራት “ሁሉም የኢትዮጵያ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ለማበረታታት እና ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይቶች ለማድረግ” ፍላጎት እንዳላቸው በሰጠው በመግለጫ አስታውቋል።

ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢለኔ ስዩም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ ሱዳን መንግሥትን እና ህወሓትን የማሸማገል ሃሳብ እንዳላት ተጠይቀው፣ ሱዳን በዚህ ወቅት ለማደራደር ወሳኝ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የሆነውን ታዓማኒነት እንደማታሟላ ገልጸው ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥትን እና ህወሓትን ለማሸማገል ከማሰቧ በፊትም ጦሯን ከኢትዮጵያ ማስወጣት እና መታመን አለባት ማለታቸው ይታወሳል።

አሁን ላይ የሱዳን ጦር በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ መሆኑን የጠቀሱት የፕሬስ ሴክሬታሪዋ የሱዳን ባለስልጣናት የካርቱም እና የአዲስ አበባ ግንኙነት እንዲሻክር ባደረጉበት በዚህ ወቅት ሱዳን ታማኝ አደራዳሪ ልትሆን እንደማትችል ገልጸዋል ሲል ዘ ኒው አረብያ ዘግቧል።

በዚህ ምክንያት ይሁን በሌላ ጉዳይ ግን ሱዳን በኢትዮጵያ ያሉትን አምባሳደሯን ወደ አገሯ መጥራቷ ተነግሯል፡፡

ያይኔአበባ ሻምበል Ethio fm
ነሐሴ 02 ቀን 2013 ዓ.ም

Exit mobile version