ሱዳን እና ኢትዮጵያ በይገባኛል ሲወዛገቡበት የቆዩበትን የድንበር ጉዳይ ለመፍታት ቱርክ ያቀረበችውን የማደራደር ጥያቄ ሱዳን መቀበሏ ተዘገበ። የቱርክ የዜና ወኪል የሆነው አናዱሉ እና የሱዳን መንግሥት የዜና ወኪል ሱና፤ የቱርክን የማደራደር ጥያቄ ሱዳን መቀበሏን የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ማሪያም አል-ሳዲቅ አል-መሃዲን ጠቅሰው ዘግበዋል።

ቢቢሲ ሚዲያዎቹን ጠቅሶ እንዳለው “የሱዳን የሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀ-መንበር አብዱል ፋታህ አል-ቡርሐን ባለፈው ወር ወደ ቱርክ በተጓዙ ወቅት፤ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈጠረውን የድንበር አለመግባባት ለመፍታት ከቱርክ ባለሥልጣናት የቀረበውን የማደራደር ጥያቄ ተቀብለዋል” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ለጋዜጠኞች መናገራቸውን አናዱሉ ጨምሮ ዘግቧል።

የሱዳን የዜና ወኪል ሱና በተመሳሳይ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የገባችበትን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት የቱርክን ጥያቄ ስለመቀበሏ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ቅዳሜ ዕለት ለጋዜጠኞች መናገራቸውን አመልክቷል።

በኢትዮጵያ በኩል በጉዳዩ ላይ እስካሁን የተባለ ነገር የለም። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የድንበር ውዝግቡን በንግግር ለመፍታት በሬ ክፍት ነው ስትል ቆይታለች።

የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤቱ ሊቀ-መንበር አብዱል ፋታህ አል-ቡርሐን አብዱል ራህማን ሰኔ ወር ላይ ወደ ቱርክ መጓዛቸው ይታወሳል። አል-ቡርሐን በአንካራ ቆይታቸው ከፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ጋር ተገናኝተው በርካታ ምጣኔ ሀብታዊ ስምምነቶችን ተፈራርመው ነበር።

በማስከተልም የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ በተመሳሳይ ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ቱርክ ተጉዘው ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር በመገናኘት የተወያዩ ሲሆን፤ የተለያዩ የትብብር ስምምነቶችን ላይ ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።

የሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር

ኢትዮጵያና ሱዳን ያላቸውን ረጅም የጋራ ድንበር ለማካለልና ሕጋዊ ቅርጽ ለማስያዝ የጋራ የድንበር ኮሚሽን አዋቅረው ለዓመታት ሲወያዩና ሲደራደሩ ቆይተዋል። ነገር ግን እንዳሁኑ የጎላ ውዝግብ ውስጥ አልገቡም ነበር። በተለይ አፍፋሽቃ በሚባለውና ለእርሻ ተስማሚ በሆነው አካባቢ ላይ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች የነበሩበት ሲሆን ሱዳን ግን የይገባኛል ጥያቄ አንስተበት ቆይታልች።

በአካባቢው በተለያዩ ጊዜያት በአርሶ አደሮቹ ላይ ጥቃት ይሰነዘር ስለነበረም ኢትዮጵያ የተወሰነ ቁጥር ያለው ሠራዊቷን አሰማርታ ጥበቃ ስታደርግ የቆየች ሲሆን ባለፈው ዓመት ነገሮች ተቀያይረው ፍጥጫው መከሰቱ ይታወሳል።

በ2013 ዓ.ም ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ ጦርነት በተቀሰቀሰበት ጊዜ ኢትዮጵያ ሠራዊቷን ለሌላ ተልዕኮ ማስወጣቷን ተከትሎ ሱዳን ጦሯን ወደ ስፍራው በማዝመት ኢትዮጵያውያኑን እንዲወጡ አድርጋ አካባቢውን በቁጥጥሯ ስር አስገብታለች። የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም በኢትዮጵያ ቁጥጥር ስር የቆዩ አብዛኞቹን ግዛቶቻቸውን ማስመለሳቸውንና የቀሩትንም እንደሚቆጣጠሩ አሳውቀዋል።

ይህንን ተከትሎ ኢትዮጵያ ሱዳንን እርምጃው ወረራ መሆኑን በመግለጽ ሠራዊቷን ከተቆጣጠረቻቸው ቦታዎች በማስወጣት ጉዳዩን በተጀመረው ሕጋዊ የድርድር መስመር በሰላማዊ ሁኔታ መፍትሄ እንዲገኝለት ስጥጠይቅ ቆይታለች።

ሁለቱ አገራት በከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው አማካይነት ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ሀሳብ ሲለዋወጡና የተለያዩ አገራትም ለድርድር ጥሪ ሲያቀርቡ ቢቆዩም መፍትሄ የሚሆን እርምጃ ሳይታይ ለወራት ቆይተዋል።

ለዚህም በኢትዮጵያ በኩል የቀረበው ሃሳብ ወደ ንግግር ከመገባቱ በፊት ሱዳን በወታደራዊ ኃይል ከያዘችው አካባቢ ለቃ መውጣት እንዳለባት ስታሳስብ ሱደን ግን ለዚህ ፈቃደኛ ሳትሆን ቆይታለች።

አወዛጋቢው ግዛት

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በይገባኛል የምትወዛገብብት የድንበር አካባቢው አልፋሽቃ ለእርሻ ሥራ ተስማሚ የሆነ ለም በመሆኑ ሁለቱም አገራት በእጅጉ ይፈልጉታል።

ይህ በሁለቱ አገሮች ዓይን ውስጥ ያለው አካባቢ የአልፋሽቃ ሦስት ማዕዘን (ትራይአንግል) ወይም የአልፋሽቃ ጥግ ተብሎ ይጠራል።

አልፋሽቃ ለኢትዮጵያ በሰሜን ምዕራብ ግዛቷ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ለሱዳን ደግሞ በደቡብ ምሥራቅ ከሚገኘው ግዛቷ ጋር ይዋሰናል።

የአልፋሽቃ መሬት 250 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና 600 ሺህ ኤክር ለም መሬትን የሚሸፍን ነው። ለለምነቱ ምክንያት የሆኑት እንደ አትባራ፣ ሰቲት እና ባስላም ወንዞችን በቅርብ ይገኛሉ።

የሱዳን ባለሥልጣናት አልፋሽቃ የሱዳን ግዛት ነው ይላሉ። በኢትዮጵያን እጅ ለምን ቆየ የሚል ጥያቄ ሲነሳ “የሱዳን መንግሥት ከአገሪቱ ጋር ባለው የትብብርና የመግባባት ስምምነት መንፈስ ነው የኢትዮጵያ ገበሬዎች ቦታውን እያለሙት የቆዩት” ይላሉ የሱዳን ባለሥልጣንት።

ሁለቱ መንግሥታት ከዚህ ቀደም ይህንን አወዛጋቢ ድንበር በድጋሚ ለማስመር፣ የጋራ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር እና የአካባቢው ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

ቀደም ካለው አስተዳደር ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሬው ሕዝብ ሉዓላዊ መሬቱን ቆርሶ እየሰጠ ነው በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ ሲቀርብበት ነው የቆየው።

እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2014 የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የወቅቱ ሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን ድንበሩ መሬት ላይ የሚመላከትበትን የመጨረሻ ቀን እንዲያሳውቁ መመሪያ አስተላልፈው ነበር።

ሆኖም አወዛጋቢውን ድንበር መሬት ላይ የማመላከቱ ሥራ እስከዛሬም አልተሳካም።

አሁን ግዛቱ በአብዛኛው በሱዳን ቁጥጥር ስር ገብቶ ነዋሪዎች እየሰፈሩበትና መንግሥትም መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ይዞታውን ለማጽናት ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ውዝግቡ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድርድር ባይጀመርም የሁለቱም አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣንት በተለያዩ ጊዜያት በሰጡት መግለጫ ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት እንደሌላቸው በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው

Leave a Reply