ሱዳን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የሉዓላዊነት ጥያቄ እንደምታነሳ አስጠነቀቀች፤ “ብሄራዊ የጀግንነት ጥሪ ያፈልጋል”

“ቅጥረኛ” ሆናለች የምትባለው ሱዳን እየዋለ ሲያድር አዳዲስ ጉዳይ እያነሳች ነው። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የሉዓላዊነት ጥያቄ ልታነሳ እንደምትችል ይፋ ማድረጓን ተከትሎ አገር ወዳዶች ” የጀግንነት ወታደራዊ ጥሪ በይፋት መታወጅ አለበት” እያሉ ነው። ህዝብ አገሩን የሚታደግበት ወቅት አሁን እንደሆነም አመልክተዋል።

አብነት ሃይሌ በሜሴንጀር ” እኔና ጓደኞቼ አገራችንን ከጠላት ለመጠበቅ ዝግጁ ነን። መንግስት ጥሪ እስከሚያስተላልፍ ነው የምንጠብቀው” ሲል ሃሳቡን ከባልደረቦቹ ጋር አስታውቋል። ይህ ሃሳብ ሰሞኑንን በማህበራዊ ገጾችም እየተዘዋወረ ነው። እንደሚሰማው ከሆነ ኢትዪጵያ በበርካታ ችግር ተወጥራላችና ዜጎች ማሰብ የሚገባቸው ጊዜ ላይ ናቸው። ከታች የሱዳን ዜና ነው። ኢትዮ ኢንሳይደር ያቀረበው ነው።

በታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድሮች እና ሁለቱ አገሮች በይገባኛል በሚወዛገቡባቸው የድንበር ጉዳዮች የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎች መልሰው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የሉዓላዊነት ጥያቄ እንደሚያስነሱ ሱዳን አስጠነቀቀች።

የሱዳን ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ትላንት አርብ ዕኩለ ለሊት ገደማ ባወጣው መግለጫ፤ የሁለቱ አገሮች ልዩነት በግድቡም ሆነ በድንበር ውዝግባቸው መበርታቱን የሚጠቁም የከረረ ትችት በኢትዮጵያ ላይ ሰንዝሯል።

የሱዳን ማስጠንቀቂያ የተደመጠው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ መርየም አል-ሳዲቅ በግድቡ ጉዳይ የአገራቸውን አቋም ለማስረዳት እና ድጋፍ ለማሰባሰብ በአፍሪካ አገራት ጉዞ በማድረግ ላይ በሚገኙበት ወቅት ነው።

የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በትላንት መግለጫው፤ ሱዳን ኢትዮጵያን በአባይ ውሃ እና በድንበር ጉዳዮች ላይ ከተፈረሙ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ለማቆራኘት እየሰራች ነው እያሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ የሚሰጧቸውን መግለጫዎች በጥልቅ ሀዘኔታ እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል።

“አገራት እና መንግሥታት በቀደሙ አገዛዞች እና መንግሥታት ለተፈረሙ ስምምነቶች እና ውሎች ቁርጠኛ መሆናቸው በዓለም አቀፍ ግንኙነት መሠረት የጣለ ልማድ ነው” ብሏል የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ መግለጫ።

“ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና ውሎችን፤ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን በማውጣት፣ ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል እነርሱን የሚቃረን የህዝብ አስተያየት በማደራጀት ገሸሽ ማድረግ፤ ዓለም አቀፍ ግንኙነትን የሚበክል፣ ለአንድ ወገን ፍላጎት ተጋላጭ የሚያደርግ፣ ቀውስን የሚያስፋፋ፣ የጥሩ ጉርብትና መሠረትን የሚያናጋ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው” ሲል የከረረ ተቃውሞ ሰንዝሯል።

See also  አብይ አሕመድ ለሁሉም ወገን ጥሪ አቀረቡ

ስምምነቶች ሲፈረሙ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር ሱዳን በአንፃሩ ቅኝ ተገዢ እንደነበረች በመግለጫው የጠቀሰው የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተናጠል የትኞቹ ስምምነቶች እንደሆኑ ማብራሪያ አልሰጠም።

“ለፕሮፓጋንዳ እና ለሀገር ውስጥ የፖለቲካ ምክንያቶች እንዲህ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እየመረጡ ውድቅ ማድረግ በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት ካለው ስምምነት ለመድረስ የማይረዳ ጎጂ እና ዋጋ የሚያስከፍል እንደሆነ ለማሳሰብ እንወዳለን” ብሏል።

የሱዳን ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በመግለጫው “አሳሳች ሀሳብ ማቅረብ እና ከዚህ ቀደም የተፈረሙ ስምምነቶችን ውድቅ ማድረግ ማለት ከስምምነቶቹ በአንዱ ከሱዳን ተላልፎ በተሰጠው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ መክተት እንደሆነ ለኢትዮጵያ ማስታወስ አያስፈልገንም” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይዞታ “ቀደም ሲል የሱዳን አካል ነበር” የሚለው ክስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሱዳን ፖለቲከኞች፣ ምሁራን እና መገናኛ ብዙሃን ዘንድ በተደጋጋሚ እየተነሳ ይገኛል።

(Ethiopia Insider)

Leave a Reply