Site icon ETHIO12.COM

ሰልስቱ !!!

ሁለተኛው የጦርነት ስልት ስትራቴጂክ የሚባሉ ቦታዎችን ይዞ ጠላትን መውጫ መግቢያ አሳጥቶ ማዳከም ነው። ይህ ስልት የሰውና የቁስ ውድመትን የሚቀንስ በመሆኑ ከመጀመሪያው ስልት በተሻለ ተመራጭ ነው።

መከላከያ ትግራይን ለቅቆ ከወጣ በኋላ መንግስት ተግባራዊ እያደረገ ያለው የጦርነት ስልት ይህ የከበባ ስልት ነው። ህወሃትም ለሚደርሰው የሰው እልቂት ሳይጨነቅ ከበባውን ሰብሮ ለመውጣት በ ሶስት አቅጣጫዎች ጦርነት ከፍቷል።

የአድዋ ጦርነት ከመጀመሩ ቀደም ብሎ መቀሌ ላይ ጠንካራ ውጊያ ተካሄዶ ነበር። ጣሊያን እጅግ ጠንካራ የሚባል ምሽግ ሰርቶ በመቀመጡ፣ ያንን በአነስተኛ የሰው ሃይል ማስለቀቅ ለኢትዮጵያ ሰራዊት ቀላል አልነበረም። ጦርነቱ በድንገት በአንዲት የደነበረች በቅሎ ተጀመረ። የኢትዮጵያ አርበኞች በስሜት ወደ ምሽጉ ሲገሰግሱ፣ ጣሊያን መድፍ እየተኮሰ ብዙ ሰው አለቀ።

የኢትዮጵያ የጦር አበጋዞች ቁጭ ብለው ሲመክሩ፣ እቴጌ ጠሃይቱ ጣሊያን የሚጠጣበት ምንጭ እንዲያዝ ሃሳብ አቀረቡ። አርበኞች በጀርባ ዞረው ይህን ቁልፍ ስትራቴጂክ ቦታ ያዙ። ጣሊያን በውሃ ጥም እንደሚያልቅ ሲረዳ፣ ከቀናት ማንገራገር በኋላ ተደራድሮ ከምሽጉን ወጣ። ኢትዮጵያም በጠሃይቱ ብልጠት፣ በአነስተኛ ዋጋ ትልቅ ድል አገኘች።

ከበባ ጥሩ ስልት ቢሆንም፣ አንዳንዴ ጠላት መፈናፈኛ ሲያጣ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት እስከመጨረሻው እየተፋለመ በወገን ጦር ላይ ብዙ ጉዳቶችን ሊያደርስ ይችላል። የአማዲዮ ዲ አኮስታ ታሪክ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።

አማዲዮ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት፣ ግራዚያኒን ተክቶ ኢትዮጵያን እንዲገዛ የተላከ ልኡል ነበር። ጣሊያን በአርበኞች የ 5 አመታት ተጋድሎ አዲስ አበባን ለቅቆ ሲወጣ፣ አማድዮ ቀሪ ጦሩን ይዞ አምባላጌ ተራራ ላይ ወጥቶ መሸገ። እጅ ስጥ ተብሎ ቢለመን “እምቢ” አለ። የእንግሊዝ አውሮፕላኖች እና የኢትዮጵያ አርበኞች በቦንብና በጥይት እየለበለቡት ሰራዊቱን ጨረሱበት። አማዲዮ ግን አንድ ሰው እና አንድ ጥይት እስኪቀር ለመዋጋት የቆረጠ መሰለ። በመጨረሻ ተስፋ እንደሌለው ሲያውቅ፣ ከሞት የተረፉትን ተዋጊዎቹን ይዞ እጁን ሰጠ።

አንዳንድ ጊዜ ከበባ ብቻውን በቂ አይሆንም። ተከታታይ ድብደባዎችን በማድረግ ረፍት መንሳት ከተራዘመ ከበባ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል የአሜዲዮ ታሪክ ያሳያል። ( በነገራችን ላይ የጥንት ታሪኮችን በምሳሌነት የማነሳው የአሁኖቹ አወዛጋቢ ስለሚሆኑ ነው።)

የኢትዮጵያ ጦር ህወሃትን ከቦ ለተወሰኑ ወራት መቆየት ከቻለ፣ ህወሃት በራሱ ጊዜ እየሟሸሸ (degenerate) ይሄዳል። አንደኛ፣ ዙሪያው ስለታጠረ የሚተኩሰውን ጥይት ከውጭ አገር ገዝቶ የሚተካበት መንገድ አይኖርም። የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችን እያሾለከ ማስገባት ቢችልም፣ መድፍና ታንክ እየገዛ ማስገባት አይችልም። ሁለተኛ፣የሚሞቱበትን ሰዎች ለመተካት ከትግራይ ውጭ ሌላ ቦታ መሄድ አይችልም። ከትግራይ ደግሞ እስካሁን ከመለመለው በላይ ሌላ ሃይል መመልመል አይችልም። ወጣቱ ሁሉ ተሰልፏል። ሶስተኛ፣ ለጦርነት የሚያስፈልጉ የምግብ፣ የነዳጅ፣ አልባሳትና የመሳሰሉ አስፈላጊ ነገሮችን እንደ ልቡ መተካት አይችልም።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ በተቃራኒው፣ ከየትኛውም የአለም ክፍል ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን እየገዛ ሃይሉን ማጠናከር ይችላል። በቂ የሰው ሃይል ከክልሎች እየመለመለና እያሰለጠነ፣ ጉዳት የሚደርስባቸውን ወታደሮች መተካትና ውጊያውን ማስቀጠል ይችላል። ምግብ፣ ነዳጅ፣ አልባሳትና የመሳሰሉትን መሰረታዊ ነገሮች ለማሟላት አይቸግረውም።

የመከላከያ ሰራዊቱ እየተጠናከረ እንጅ እንደ ህወሃት እየሟሸሸ አይሄድም። ይህ በሂደት ሰፊ የሆነ የሃይል ሚዛኑ ልዩነት ይፈጥራል። የሃይል ሚዛን ልዩነቱ ህወሃትን በማያሸንፍበት ሁኔታ ውስጥ ስለሚከተው፣ ጦርነቱ ውጤታማ ሆኖ ሊጠናቀቅ የሚችልበት እድል ሰፊ ይሆናል።

የከበባ ጥቅም ከፍተኛ ቢሆንም፣ ሁሉንም ቦታዎች አስሮ መቀመጥ ግን አስቸጋሪ ነው። ህወሃት የሳሳ ቦታ አለ ባለበት ሁሉ ጥቃት እየፈጸመ፣ የሃይል ማዛባት ለመፍጠር መንቀሳቀሱ አይቀርም። በወልድያ መስመር የምናየው ተደጋጋሚ ጥቃትም ይህን ታሳቢ ያደረገ ነው።

ሁሉንም በሮች ዘግቶ ለመቀመጥ፣ ብዙ የሰው ሃይልና ብዙ የጦር መሳሪያዎች ያስፈልጋሉ። ወደ ጦር ግንባር የሚተመውን ወጣት አሰልጥኖ ለማውጣት ትንሽ ጊዜ ማስፈለጉ አይቀርም። ያ እስኪሆን ህዝቡ በሮችን የመጠበቅ ግዴታ አለበት። የከበባ ስልት በጥንቃቄ ከተመራ በአነስተኛ ኪሳራ ብዙ ድል ሊመዘገብበት ይችላል።

የጦርነት ድል በብዙ፣ በሚታዩና በማይታዩ፣ ነገሮች ላይ እንደሚመሰረት የተለያዩ የጦርነት አዋቂዎች ጽፈዋል። እንኳንስ በሩቅ ሆኖ ሜዳ ላይ ሆኖም፣ ስለጦርነት ውጤት መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። በወረቀት ላይ ያስፈርከውን እቅድ ሙሉ በሙሉ መሬት ላይ ላታወርደው ትችላለህ ። ትንሽ ስህተት ለብዙ ጉዳት ሊዳርግህ ይችላል። ያ ሆኖ ግን ብዙ አስቦ፣ ተረጋግቶ ማቀድ ወሳኝ ነው።

ጽሁፌን የማጠቃልለው መሪዎችን እየለዩ እርምጃ በመውሰድ ላይ ያለኝን ምልከታ በማካፈል ነው ( ይቀጥላል)
Fasil Yenealem

Exit mobile version