Site icon ETHIO12.COM

መውለድ የእናቶች ሰቀቀንና …

ወጣት ቸኮል በርሔ 21 ዓመቱ ነው።ለእናቱ ብቸኛ ልጅ ነው።ወላጁ በድህነት ክፉኛ የተፈተኑ በመሆናቸው ከአራተኛ ክፍል በላይ ትምህርቱን መቀጠል አልቻለም።ያላቸው አንድ ልጃቸው በመሆኑ ያለ ዕድሜው ሐላፊነት ይሰማው ነበር።

የሚወደውን ትምህርቱን አቋርጦ የመኪና ረዳት ሆኖ በሚያገኘው ገቢ የእራሱንና የእናቱን ኑሮ ይደጉም ያዘ።ትልቁ ህልሙ ትምህርቱን እንደ ምንም አሻሽሎ መንጃ ፍቃድ በማውጣት ዘላቂ ገቢ አግኝቶ ከህይወቱ በላይ የሚሳሳላቸው እናቱን ከድህነት ደዌ መታደግ ነበር – በነበር ቀረ እንጂ !

በአንድ የተረገመ ቀን ባይሆን በሚመኘው ወቅት ጥቅምት 24 ጥቁር ምሽት በሠራዊታችን ላይ ባልታሰበ ሠዓት ጥቃት ተፈፀመ።የቸኮለ ህልምና ተስፋም አከተመ። የህይወት አቅጣጫው የሚቀይር ምናልባትም ህይወቱን በአጭር የሚያስቀር አጋጣሚ መጣ።

በበቂ ሁኔታ ሳይሰለጥን ወደ ውጊያ እንዲሠማራ ተደረገ።አንድ ልጄ ነው የሚረዳኝ የለም።ብቸኛው ተስፋዬ አትንጠቁኝ የሚል ተማፅኖ በትህነግ ምድር አይሠራም ብቻ ሣይሆን ለባሰ አደጋ ያጋልጣል። ሰሚ ጆሮ አስተዋይ ልቦና እዚያ ሐይል ጋ የለም።እናም የቻለውን አድርጎ ሲያቅተው በህይወት ለመቆየትና ነገን ለማየት ወደ ሱዳን ተሰደደ።

ምን ዋጋ አለው።ህውሐት ቀድሞ ተሻግሮ ጠበቃቸው።ቸኮልና ከእሱ በዕድሜ የሚያንሱትን ሁሉ እንደገና መልምሎ በቅርቡ መላ ሀገሪቱን እንቆጣጠራለን።ድል በድል ሆነናል።ወደ ትግራይ ተመልሳችሁ ሄዳችሁ ድልን ከውድብ ጋር ታጣጥማላችሁ ተብሎ ተደለለ።

እዚያ የሚገኙ የጁንታው አመራሮች መሣሪያ አደሉ።መሣሪያ ለሌላቸው የሬዲዮ መገናኛ ዘመናዊ መሣሪያ አሳዘሉ።ጉዞ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ደግም ወደ ኢትዮጵያ ሆነ -ኢትዮጵያን ጀሌ ሰብስቦ እኩይ አስቦ ወድቀቷን ከሚመኙ ጋር በደቦ እንዴት ቀላል መስሎ እንደታየ እንጃ !

ሲነሱ ሦስት መቶ አከባቢ እንደነበሩ ያስታውሳል።ቀን ከለሊት ተጉዘው ኢትዮጵያ ሲደርሱ የገጠማቸው ድል ሳይሆን እሳት ነበር።የሞተው ሞቶ 106 ያህሉ በሠራዊታችን ቁጥጥር ሥር ገቡ።

ለወጣት ቸኮል መከላከያ ሠራዊቱ እሩቅ አልነበረም።በቅርበት ያውቀዋል።እስከ አራት የተማረው መከላከያ ሠራዊቱ በገዛለት ደብተርና ባለበሰው ዩኒፍርም ነው። የእናቱና የእሱን መሠረታዊ ፍላጎት የሚያሟላ አስተማማኝ አገር ነበር። ያጎረሰንን እጅ ነክሰናል።ጥቁር ክህደት ፈፅመናል የሚለው ቸኮለ ሲያምን የተካደው ሠራዊት እጅ መልሰን ስንገባ ቁጣው ምን ሊያደርስባቸው እንደሚችል እያሰበ በጨነቅም የሆነው ግን በተቃራኒው ነው።

ሠራዊቱ እጅ እንደገቡ የደረቀው ጎሮሮአቸው በውሃ ራሰ።ለቀናት ምግብ ያልዞረባቸው አፋቸው ብስኩት ቀመሠ።ይሄ ህዝባዊ ሠራዊት የያዘው እውነት፤ሊገድለው መጥቶ አቅቶት በእጁ የገባን ጠላት በእንክብካቤ የመያዝ አዛኝነት ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ጀግንነትን አየ።እናም እንደ አዲስ አስነባው።

ቸኮል የኢፌዴሪ መከላከያን የሚያውቀው ደም ሲለግስ ፣ቤት ሲያድስ፣ የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮች ማሣ ላይ ጠሞዶ ሲያርስ፣ ሲያርም፣ ሲጎለጉል ፣ሲያጭድ ሲወቃና ከጎተራ ሲያስገባ ፣ መንገድ ትምህርት ቤት የጤና ተቋማት ሲገነባ ነው።ይሄን ሐይል መውጋት በራስ ቁስል ላይ እንጨት መስደድ መሆኑን እያሰበ ከልቡ ይፀፀታል።

በመጀመሪያ ልጆች ስለነበርን ተታለን የእራሳችንን ደጀን የወጋን ፣ ተገደን ወደ እሳት የገባን በኋላም የተማረክን ፣ ዕድሉን አግኝተን የበደልናትን ሀገር ብንክስ የሚል ሐሳብ አለው።

አሁን ያሉበትን ሁኔታ ሲያይ ሀገር መቼም ቢሆን በልጆቿ እንደማትጨክን እንደ ተረዳ ያወጋል።በቀን ሦስት ጊዜ በአግባቡ ምግብ ይቀርብላቸዋል ።ገላቸውን ሁለቴ ይታጠባሉ።ሠራዊቱ የሚያነጋግራቸው በፍቅር ነው።የመዝናኛ ጊዜም አላቸው።

ሃፍቶም አብራሃሌ ይባላል ፡፡ ይሄኛው የ17 ዓመት ታዳጊ ነው።ከኢፌዴሪ መከላከያ ጋር ፊት ለፊት እንዲጋፈጥ የተደረገው የሦስት ቀናት ወታደራዊ ስልጠና ወስዶ ነው።አሁን ባለበት ምንም የጎደለበት ነገር ባይኖርም እናቱ ያለበትን ስለማያውቁ ምን ሆና ይሁን እያለ ይጨነቃል።እናቱም ይሙት ይኑር አያውቁም።

እነዚህ በሠራዊታችን እጅ በፍቅርና እንክብካቤ የተያዙ ወጣቶችና ህፃናት ዕድለኞች ናቸው።ቢያንስ መመለስ ከማይችሉበት የሞት አደጋ ተርፈዋል።እንደማንኛውም ሰው የሀገር ተቀርሳ ተቆርጦ የተሻለ ነገ መጥቶ በተስፋ ለመኖር ተስፋ ያደርጋሉ።

ያሉበትን ሁኔታ የገለፁልን ……

ሁለቱ ህፃናት ያሉበትን ሁኔታ የገለፁልን በተመሣሣይ መልኩ ነው። ያሉበት ሁኔታ በፍቅር የታጀበ በእንክብካቤ የታያዘ የቤተሰብ ያህል መሆኑን በመግለፅ።

ሠሞኑን የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጀይላን አብዲ የተመራ በመንግስት ቁጥጥር ሥር ያሉ ምርኮኞችን በጎበኘበንት ወቅት በርካታ የህውሐትን ግፍ የሚያጋልጡ ግፎች የታዘብን ቢሆንም ልብ የሚነኩ ነገር ግን ለቤተሰባቸው ደህንነት ሲሉ እናልፋቸው ዘንድ የጠየቁንን አክብረናል ትተናል።

በአጠቃላይ ትህነግ የሀገር በተለይ የትግራይ ህዝብ ጠላት መሆኑን የሚያረጋግጡ መረጃና ማስረጃዎች አግኝተናል። በልክ ፍካት ሳይሆን ሰቀቀንና ስጋት የገጠማው እናቶች እፎይ የሚሉት አጥፊው ሲጠፋ ብቻ መሆኑ አያጠራጥርም።

ሻለቃ ፈይሳ ናኔቻ
ፎቶግራፍ ፈይሳ ናኔቻ

Exit mobile version