Site icon ETHIO12.COM

“አሸባሪው ሃይል ህጻናትና አዛውንቶችን በጅምላ ጨፍጭፏል”አፋር

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በየደረሰበት ስፍራ ህፃናት፣ ሴቶች እና አዛውንቶች ላይ የጅምላ ግድያ መፈጸሙን የአፋር ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ አስታወቁ።ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሀገር ሽማግሌዎችና ማህበረሰብ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡በዚህ ወቅትም የህወሓት ሽብር ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስና ህዝቦቿን ለማተራመስ የጀመረው ጥረት እንደማይሳካለት ተናግረዋል፡፡

የአፋር ህዝብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አላስደፍርም በማለት መስዋዕትነት እየከፈለ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ሁላችንም ባለንበት ለሀገራችን የቻልነው ሁሉ በማድረግ ግዴታችንን ልንወጣ ይገባልም ብለዋል።አሸባሪው ህወሓት በእብሪት ተወጥሮ በክልሉ የፈጸመውን ወረራ ለመቀልበስ እየተወሰደ ያለው የአጸፋዊ ምላሽ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በሌላ ተመሳሳይ ዜና አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል በህጻናትና ንጹሃን ዜጎች ላይ ያደረሰውን ጭፍጨፋ እንደሚያወግዝ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ አስታወቀ፡፡

አሸባሪው ሕወሓት በአፋር ክልል በፈጸመው ጥቃት 107 ሕጻናትን ጨምሮ 240 ንጹሃን ዜጎችን መግደሉን አልጀዚራ በሰራው ዘገባ ማጋለጡ ይታወሳል፡፡ ቡድኑ በፈጸመው ጥቃት በአፋር ክልል “ካሊኩማ” በሚባል ሥፍራ የሚገኙ ከተማዎችና ትምህርት ቤቶች ላይ ያነጣጠረ ነበር።

መንግሥት ምንም እንኳን የተናጠል የተኩስ አቁም ቢያደርግም አሸባሪው ሕወሓት በአጎራባች ክልሎች ላይ የሚያደርገውን ጥቃት አጠናክሮ መቀጠሉን ዘገባው አካቷል። አሸባሪ ቡድኑ በአፋር ክልል ላካሄደው የሽብር ጥቃት ሕፃናትን ማሰለፉንም ዘገባው አውስቷል። የሽብር ጥቃቱን ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸውም ተመልክቷል፡፡

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አሸባሪው ቡድን በንጹሃን ላይ የፈጸመውን ጥቃት የሚያወግዝ መሆኑንና በተፈጸመው ድርጊትም በእጅጉ ማዘኑን አስታውቋል፡፡ የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሙሉብርሃን ኃይሌ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፥ አሸባሪው ከዚህ ቀደም ሲፈጽመው የቆየውን ድርጊት አሁንም መድገሙ አሳዝኗቸዋል፡፡

ይህ የሽብር ቡድን “ከትግራይ በቀለ እንጂ ፍጹም የኢትዮጵያና ትግራይ ስነ-ልቦና የሌለው” ነው ያሉት ሃላፊው፥ ቡድኑ እስኪጠፋ ድረስም ይህን ድርጊት ሊያቆም የማይችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሽብር ቡድን መጥፋትና መደምሰስ በጋራ ሊቆም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በደረሰው ድርጊትም ለአፋር ህዝብና መንግስት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል፡፡ በመንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ከተደረገ በኋላ የአሸባሪ ቡድኑ የአገሪቷን ሠላምና ደኅንነት እያወከ መሆኑን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገነዘብ ተጠይቆ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ በቅርቡ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካው ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩ ኤስ ኤድ) ኃላፊ ሳማንታ ፓወርም የአሸባሪው ሕወሓት ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳሳሰባቸው መናገራቸውን ይታወሳል ሲል ፋና ዘግቧል።

Exit mobile version