በአሸባሪው ህወሓት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ይሰራል


አሸባሪው ህወሓት በአገርና በህዝብ ላይ ያደረሰውን ውድመትና የፈጸማቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በመመርመር ለህዝብና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ እንደሚሰራ የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ጠበቆችና የህግ ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመቀናጀት ለአማራ ክልላዊ መንግስት የ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እና የአይነት ድጋፍ አድርጓል።

በድጋፍ ርክክብ ስነስርአት ላይ የተገኙት በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ አሸባሪው ህወሓት የአፋርና የአማራ ክልሎችን በመውረር ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳቶችን አድርሷል።

አሸባሪው በማህበረሰቡ ላይ የተለያዩ የጭካኔ ተግባራትና ሰብአዊ ጥሰቶች በመፈጸም በማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይም ውድመት ማድረሱን ተናግረዋል።
“የሽብር ቡድኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ ያደረሰው ውድመት ከፍተኛ መሆኑን በአካል ማረጋገጥ ተችሏል” ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት ዘርፎ ከወሰደው ንብረት በተጨማሪ በንብረት ላይ ያደረሰውን ውድመትና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በመመርመር ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው የአማራ ክልል ህዝብ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን የደረሰበት የጭካኔ ተግባር፣ ግፍና ጥቃት ተዘርዝሮ እንደማያልቅ ገልጸዋል።
ከሁሉም በላይ ህብረተሰቡ የስነ-ልቦና ጉዳት እንደደረሰበት የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አሸባሪው ቡድን ሴቶችን መድፈሩንና ከመኖሪያ አካባቢያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ ዳግም እንዳይነሳ በወገን ጥምር ጦር እርምጃ እየተወሰደበት መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ይልቃል፤ አሸባሪው በክልሉ ህዝብ ላይ የፈፀመው የከፋ ሰብዓዊ ጥሰትና የአገር ሃብት ውድመት ለህዝብና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚገባ ማሳወቅ እንደሚገባ ተናግረዋል
ለዚህም የፍትህ ሚኒስቴር ባልደረቦችና ሌሎች የህግ ባለሙያዎች ጉዳዩን በዝርዝር መርምሮ በማጥናት የደረሰውን ሁለንተናዊ ጉዳት በማሳወቅ የአሻባሪውን እኩይ ተግባር አደባባይ ማውጣት እንደሚገባ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ከግለሰብ እስከ መንግስት ንብረቶች ማውደሙ እንደተጠበቀ ሁኖ በንጹሃን ላይ ከፍተኛ ኢ-ሰብአዊ ወንጀሎችን መፈጸሙ ይታወቃል።
Source – ENA

See also  በአዲስ አበባ የጦር መሳሪያ ከአዘዋዋሪዎቹ ጋር ተያዘ

Leave a Reply