Site icon ETHIO12.COM

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዝምታን የመረጠበት የአፋር እና የአማራ ክልል የንጹሀን ጭፍጨፋ!!

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እስካሁን ዝምታን የመረጠበት የአፋር እና የአማራ ክልል የንጹሀን ጭፍጨፋና መፈናቀልን በተመለከተ ዓለምአቀፍ ተቋማት እና መገናኛ ብዙሀን የተለያዩ መግለጫዎችን እያወጡ ነው

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እስካሁን ዝምታን የመረጠበት የአፋር እና የአማራ ክልል የንጹሀን ዜጎች ጭፍጨፋ፣ መፈናቀልና ዝርፊያን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ መገናኛ ብዙሀን እና የተለያዩ አካላት ድርጊቱን በማውገዝ መግለጫ እያወጡ ነው።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት እስካሁን በአፋር እና በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት ምክንያት ስለተጨፈጨፉ ንጹሀን እና ስለተፈናቀሉ ዜጎች ምንም አይነት ሪፖርት አላወጣም።

በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ዋና ኮሚሽነሩ “ከአገር ውጭ ነኝ” በማለታቸው በቂ ምላሽና ማብራሪያ ማግኘት አልቻለም።

ኮሚሽኑ ትናንት በማህበራዊ ገጹ ላይ የአፋሩን ጭፍጨፋ በተመለከተ ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን ወደስፍራው ልኬያለሁ የሚል መረጃ ብቻ ሰጥቷል።

አሸባሪው ህወሓት በሁለቱ ክልሎች ላይ በፈጠረው ወረራ ምክንያት በተለይም በአፋር ጋሊኮማ በትምህርት ቤት እና በጤና ጣቢያ ተጠልለው በነበሩ ንጹሀን አርብቶ አደሮች ላይ በከባድ መሳሪያ በፈጸመው ድብደባ ከ200 በላይ ሰዎችን ሲጨፈጭፍ፤ 107ቱ ህጻናት መሆናቸውን አልጀዚራ አጋልጧል።

በተመሳሳይ የመንግስትን የተናጠል የተኩስ አቁም ወደ ጎን በማለት ህጻናትን ጭምር በማስታጠቅ የአፋር እና የአማራ ክልሎች ላይ ትንኮሳ እየፈጸመ ያለው አሸባሪው ህወሓት፤ በአፋር ክልል ህጻናትን ጨምሮ ንጹሀን ዜጎችን መጨፍጨፉን ተከትሎ ዩኒሴፍ ጉዳዩ እንዳሳሰበው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የኒሴፍ በዚሁ መግለጫው የሰብአዊ የተኩስ አቁም ተግባራዊ ሊሆን ይገባል ሲልም ጠይቋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ህወሓት ወሮ በያዛቸው የአፋር እና የአማራ አካባቢዎች ከ226 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሳማንታ ፓወር አስታውቀዋል።

ሳማንታ ፓወር በሰጡት መግለጫ፤ የህወሓት ታጣቂዎች ጥቃት በፈጸሙባቸው የአፋር ክልል አካባቢዎች ከ76 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

በተመሳሳይ ታጣቂዎቹ ጥቃት በፈጸሙበቸው የአማራ ክልል ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ሣማንታ ፓወር ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግስት ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል በሕክምና ተቋም የተጠለሉ ከ200 የሚበልጡ ሰዎችን ሲያርድ፤ ከ300 ሺህ በላይ ዜጋዎችን ማፈናቀሉን አስታውቋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአፋር ክልል በጋሊኮማ ጊዚያዊ መጠለያ በነበሩ ንፁሃን ዜጎች ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ አስመልክቶ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሀዘን ቀን እንዲሆን የአፋር ክልል መንግስት አውጇል።

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version