Site icon ETHIO12.COM

የሽብር ቡድኑ ሙት፣ቁስለኛና ምርኮ ሆኖ የተረፈው ከመርሳ ከተማ ለቆ ወጣ፤”በመርሳ መሪፌ ተወግተው የሞቱ ተገኝተዋል”

“አሁን የምናደርገው ትግል በጊዜያዊ ድል የምናቆመው አይደለም፤ ትልቁ ዓላማ አሸባሪውን ሙሉ በሙሉ በመደምሰስና ተላላኪዎቹንም የኢትዮጵያ ስጋት መሆን እንዲያቆሙ በማድረግ ነው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ መረጃ የሰጡት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ አሸባሪው ትህነግ በፈጸመው ወረራ የወገን ኀይል ተገቢውን ምላሽ እየሰጠው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በተለያዩ አካባቢዎች ከፈጸመው ወረራ ባሻገር በኦሮሚያ ክልል በተላላኪዎቹ አማካኝነት አማራ በብዛት በሚኖርበት አካባቢ ጥቃት ለመሰንዘር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

“አሁን የምናደርገው ትግል በጊዜያዊ ድል የምናቆመው አይደለም፤ ቦታን የማስለቀቅ እና የመያዝ ጉዳይም አይደለም፤ ትልቁ ዓላማ አሸባሪውን ሙሉ በሙሉ መደምሰስና ተላላኪዎቹንም የኢትዮጵያ ስጋት መሆን እንዲያቆሙ ማድረግ ነው” ብለዋል፡፡

የቡድኑ ዓላማ አማራን የማጥፋትና ኢትዮጵያን መበተን መሆኑን አቶ ግዛቸው ተናግረዋል፡፡ ሽብርተኛው ትህነግን ለመቅበር መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ሕዝቡን ደጀን በማድረግ ትግል እያካሄዱ ነው፤ በዚህም ከትናንት ጀምሮ ባለው መረጃ መርሳ ከተማን ሙሉ በሙሉ ከሽብር ቡድኑ ነፃ ማድረግ ተችሏል፤ በዚህም የጠላት ኀይል ሸሽቷል፤ በሰላም እጁን የሰጠም አለ፤ ቀሪውም ተደምስሷል ነው ያሉት፡፡ የሽብር ቡድኑን እኩይ ዓላማ የተረዱ አባላቱ በሰላም እጃቸውን እየሰጡ ነው ብለዋል፡፡ የጠላት ኀይል በየግንባሩ እየተደመሰሰና በርካታ የቡድን መሣሪያዎች ሳይቀር እያስረከበ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የሽብር ቡድኑ ተዋጊዎች ብቻ ሳይሆን አዋጊ መሪዎቹም እየረገፉ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ሕይወቱን እየሰጠ ለሚገኘው የወገን ኀይል የስንቅ ዝግጅቱ ሳይቆራረጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቶ ግዛቸው አሳስበዋል፡፡

አቶ ግዛቸው ለህልውና ዘመቻው በሀገር ውስጥም ኾነ በውጪ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች መንግሥት በከፈተው ሕጋዊ የባንክ የሒሳብ ቁጥሮች ብቻ ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን ከጦርነት የተራረፉ፣ ከማኅበረሰቡ ጋር ተመሳስለው መረጃን የሚያቀብሉ፣ ስንቅና መሣሪያ የሚሰጡ ሰርጎ ገቦችን ያሰማራ ስለሆነ በየአካባቢው ከወትሮው በተለየ መልኩ ጥብቅ ፍተሻ ሊደረግ እንደሚገባ አቶ ግዛቸው አሳስበዋል፡፡ ፍተሻ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የጸጥታ ኀይሉ እጅ ከፍንጅ ካገኘ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ነው አቶ ግዛቸው የገለጹት፡፡

የሽብር ቡድኑን ማጥፋት ማለት ኢትዮጵያን መታደግ ስለሆነ ሁሉም በጋራ ሊረባረብ እንደሚገባ ጥሪ አድርገዋል

ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ -ከላይ ያለው ከ(አሚኮ) የተወሰደ ነው

በተያያዘ ሌላ ዜና መርሳ መርፌ ተውግተው የተገደሉ ንጽሃን መኖራቸውን፣ እስክ አሁንም ሃያ አራት የሚደስ አስከሬን መገኘቱን ከአካባቢውን ነዋሪዎች መካከል እንደ ከድር እድሪስን ጠቅሶ ኤርሚያስ ተኩማ በማህበራዊ ገጹ አስፍሯል። በመርፌ ተውገተው ምንም ቁስልና የጥይት ምልክት ሳይኖርባቸው የተገደሉት ሰዎች ምን ዓይነት መርዝ እንደተወጉ ይፋ አልሆነም። ይሁን እንጂ ትህነግ ስፍራውን በተቆጣጠርበት ወቅት እተበከለ መርፌ መውጋቱን ነው ምስክሮቹ የሚገልጹት። ድርጊቱ እጅግ ከፍተኛ ወንጀል በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ሊያጣሩትና ምርመራ ሊያደረጉበት እንደሚገባ ተመልክቷል። ይህን መረጃ አስመልክቶ የአማራ ክልል መንግስትም ሆነ የፌደራል እስካሁን በይፋ ያሉት ነገር የለም። ምስክሮቹ ግን የምስል ማስረጃ እንዳላቸው ገልጸዋል።

Exit mobile version