የኢፌዴሪ አየር ሃይል ኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክተር ኮሎኔል ተሾመ በዳዳ አሸባሪው ሕወሓት በስልጣን በቆየበት ወቅት አየር ኀይልን በትኖ እና ዘርፎ ወደ መቀሌ መሸሹን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ከለውጡ በኋላ በተቋሙ በተሠራው የሪፎርም ሥራ አየር ኀይሉ በሙሉ ቁመናና ዝግጁነት ላይ ሆኖ እንዲደራጅ መደረጉን ነው ያብራሩት።
መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በማድረግ ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ አሸባሪው ቡድን በአጎራባች የሚገኙ የአማራና አፋር ክልሎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ነው የተናገሩት።
ይህ አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውስጥና ከውጭ ኀይሎች ጋር በመሰለፍ የተለያዩ የጥፋት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ነው ያነሱት። ሆኖም የዚህ የሽብር ቡድኑ ዓላማ በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሀገር ወዳድ ዜጎች የጋራ ትብብር እየከሸፈ መሆኑን ተናግረዋል።
ደጀን ሕዝባችንን ይዘን በአጭር ጊዜ ውስጥ ጦርነቱን በመቋጨት “አሸባሪውን ሕወሓት በመደምሰስ ፊታችንን ወደ ልማቱ እናዞራለን” ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በየትኛውም የጥፋት ኀይል የማትፈርስ ታላቅ ሀገር ናት ያሉት ኮሎኔሉ በቡድኑ ላይ በጋራ ክንድ ድል እናረጋግጣለን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።