Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ ወደ ጨው ፖለቲካ መዞሩ ተሰማ

የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር በአፋር ክልል በኩል “የሞከረው ተስፋፊነትና ወረራ” መከሸፉን ተከትሎ በሚዲያቸው ” ለአፋር ወንድም ህዝብ ስንል ዘመቻውን ተተነዋል” ብለው ነበር። የአፋር ክልል መንግስታዊ መዋቅር በቪዲዮ አስደግፎ፣ መንግስትም በመረጃ በአፋር በኩል የሆነውን በይፋ በማሳየት “አሸባሪ” በተባለው ሃይል ላይ የደረሰውን ጉዳት አሳይተዋል።

የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ” አሸባሪው ትህነግ በአፋር ሕዝብ ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋ በየትኛውም ወቅት የሚረሳ አይደለም” ሲሉ የገለጹትና ዜጎችን አንገት ያስደፋው የጅምላ ግድያ ትህነግ የደረሰበትን ሽንፈት ለማካካስ የተፈጸመው መሆኑም ተገልጿል። “ነጭ ወያኔ” የሚባሉት የትህነግ ቃል አቀባይና አቅጣጫ አመላካቾች በአፋር ግንባር ትህነግ ድል ተቀዳጅቶ የጅቡቲን መንገድ እንደሚዘጋ በገጾቻቸውና በድረ ገጾቻቸው አስፍረው ነበር።

እስካሁን በአፋር በኩል ምንም የተፈጠረ ነገር በየትኛውም ሚዲያ አልተሰማም። መንግስት ያቀረበውን በማስረጃ የተደገፈ “ድል” የትህነግ አመራሮች በቀጥታ አላስተባበሉም። ይሁን እንጂ 240 ንጽህ ዜጎቹ ተጨፍጭፈውበት ሃዘን ላይ ላለው የአፋር ህዝብ “ለወንድም የአፋር ህዝብ ስንል ዘመቻውን ትተነዋል” ብለዋታል።

የጦር ሜዳ ውሎው እንዲህ ሆኖ ሳለ ነው እንግዲህ ” አፋርን ትህነግ ተቆጣጥሮታል። ጨው ከአገር ሊጠፋ ነው” የሚል ፖለቲካ የተጀመረው። በሰማው የሚበረግገው ደግሞ ይህንን “የጨው የሽብር ፖለቲካ” ተከትሎ ጨው ለመግዛት ሲረባረብ ታይቷል።

መንግስት፣ የተለያዩ የአስተዳደር አካላት፣ ሚዲያዎች፣ የመከላከያ መኮንኖች በርካታ የፈጠራ ወሬና ሽብር እንደሚነአ በተደጋጋሚ እያስታወቁ ባለበት በአሁኑ ወቅት “የምግብ ጨዉ ሊጠፋ ነዉ በሚል የተሳሳተ መረጃ ዜጎች ካልተገባ ወጪ እራሳቸዉን እንዲጠብቁ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አሳሰበ” የሚል ዜና ተሰምቷል። ኢትዮ ኤፍ ኤም የሚከተለውን ዘግቧል።

በአገሪቱ የጨው ምርት የሚገኝበትን የአፋር ክልልን የህዋሃት የሽብር ቡድን ስለተቆጣጠሩት የጨው ምርት እጥረት አጋጥሟል በሚል በህብረተሰቡ ውስጥ መደናገጥ እንደተፈጠረበትም ኢትዮ ኤፍ ኤም ከነዋሪዎች ሰምቷል፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የምግብ ጨዉ ሊጠፋ ነዉ በሚል የተሳሳተ መረጃ ነዋሪዎች በገፍ በውድ ዋጋ እየሸመቱ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ግን ህብረተሰቡ ጨው ሊጠፋ ነው በሚል እየተሰራጨ ባለ የተሳሳተ መረጃ የተነሳ ያልተገባ ወጪ ከማውጣት እራሱን እንዲጠብቅ አሳስቦ፣ በከተማችን ምንም ዓይነት የምግብ ጨዉ እጥረት እንደሌለ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ ነግረውናል፡፡

በአሁኑ ሰአት የምግብ ጨዉ በበቂ አቅርቦት እየቀረበ መሆኑን ያነሱት ምክትል ኃላፊዉ፤ ይህንን ወቅት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመዉ ያልተገባ ትርፍ የሚያጋብሱ ነጋዴዎችም ከድርጊታቸዉ እንዲቆጠቡ ሲሉ ነዉ ያሳሰቡት፡፡

ኢትዮጵያ አይደለም ለራሷ ይቅርና ለሌሎ ች የሚተርፍ የምግብ ጨዉ አቅርቦት ያላት መሆኑን ያስገነዘቡት አቶ መስፍን ህብረተሰቡ ከሚነዛዉ የተሳሳተ የማህበራዊ ሚዲያ መረጃ እራሱን ሊጠብቅ ይገባል ነዉ ያሉት፡፡

ይልቁንም የመንግስት ተቋማት ብቻ የሚሰጧቸዉን መረጃዎች ህብረተሰቡ እንዲጠቀምም አሳስበዋል፡፡

የህዋሃት የሽብር ቡድን የአፋር ክልልን ተቆጣጥሯል በሚል የሃሰት መረጃ አማካኝነት የጨዉ ምርት በአፋር ክልል በስፋት ስለሚመረት እጥረት ሊያጋጥም ይችላል በሚል ህበረተሰቡ መደናገጥ እንደተፈጠረበትም ከነዋሪዎች ሰምተናል፡፡

Exit mobile version