Site icon ETHIO12.COM

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ “በጸረ ሰላም ኃይሎች” ላይ በጣምራ እርምጃ እንዲወሰድ ታዘዘ

በሃሚድ አወል

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 8 ጀምሮ ሁሉም የጸጥታ አካላት “በክልሉ ሽብር ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ ጸረ- ሰላም ኃይሎች” ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰዱ ትዕዛዝ አስተላለፈ። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚገኙ የደቡብ፣ ሲዳማ እና ጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይሎችም እርምጃ በመውሰድ ስራው ላይ እንደሚሳተፉ የክልሉ የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የእርምጃ ትዕዛዙ የተላለፈው፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ትላንት አርብ ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው። የቢሮው መግለጫ፤ በክልሉ በመተከል፣ ካማሺ እና አሶሳ ዞኖች ሲፈጸሙ የቆዩ ጥቃቶች ጀርባ የህወሓት እጅ አለበት ሲል ወንጅሏል። የቢሮው ኃላፊም፤ ህወሓት የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ “ማስተር ማይንድ ሆኖ እየሰራ ነው” ሲሉ የሚመሩትን መስሪያ ቤት ክስ አጠናክረዋል።

ህወሓት “እጁን በማስረዘም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ዋነኛ የሽብር ቀጠና ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል” ሲል የሚከስሰው የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ፤ ይህ ተግባሩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን እስከ ማደናቀፍ የተጓዘ እንደሆነ በመግለጫው አንስቷል። ህወሓት በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተባባሪ ኃይሎች ጋር በመሆን “እኩይ ተግባሩን ቀጥሎበታል” ብሏል። 

የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮው፤ ከህወሓት ጋር አብረዋል በሚል በመግለጫው የጠቀሳቸው ኃይሎች ሸኔ እና የጉሙዝ ታጣቂዎችን ነው። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል፣ ካማሺ እና አሶሳ ዞኖች ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በተደጋጋሚ የሰላም ድርድር ቢያቀርብም፤ የሰላም ጥሪውን አለመቀበላቸውን መግለጫው ጠቅሷል። 

በቢሮው መግለጫ “የጥፋት ቡድን” በሚል በተደጋጋሚ የተጠቀሰው ህወሓት፤ በክልሉ ተጨማሪ ጥቃቶች ለመፈጸም በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑም ተገልጿል። “ክልሉ ከሱዳን ጋር ሠፊ ድንበር የሚጋራ እና ጠረፋማ መሆኑን እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀም፤ አሁንም ይህ አሸባሪ ቡድን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ትልቅ ቀውስ ለመፍጠርና ተጨማሪ ጉዳት ለማድረስ አባላቱን ማሰማራቱ ተደርሶበታል” ሲል የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል።

“ከዚህ በኋላ የክልሉ መንግስት እነዚህን ጸረ-ሰላም ኃይሎች የሚታገስበት ጊዜ አልቋል” ያለው የቢሮው መግለጫ፤ “በክልሉ ሽብር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ” በተባሉ ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ትዕዛዝ አስተላልፏል። አቶ አብዮት ከዚህ በፊትም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ “ጸረ-ሰላም ኃይሎች” ላይ እርምጃ ሲወሰድ እንደነበር አስታውሰው፤ የአሁኑ እርምጃ በህዝብ አደረጃጀት ጭምር የሚወሰድ መሆኑ የተለየ እንደሚያደርገው አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Exit mobile version