Site icon ETHIO12.COM

አምነስቲ መርጦ አልቃሽ!!

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ነው። በአገራት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ዳሰሳ በማድረግ በየዓመቱ ሪፖርት በማውጣት ይታወቃል። ግን ብዙዎች ተዓማኒነት እንደሌለውና የፖለቲካ ወገንተኛ መሆኑን በማስረጃ አስደግፈው ይኮንኑታል። እርሱ “አድልኦና ፍርደ ገምድልነት የለኝም። ለእውነት የቆምኩ ነኝ” ሲል ለመከራከር ቢዳዳውም ወገንተኛነቱን አንድ ሁለት ብለው ቆጥረው ያጋልጡታል።

ተቋሙ ”ከየትኛውም መንግስት፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ የኢኮኖሚና የሃይማኖት ፍላጎት ነጻ ሆኜ ተቋቁሜያለሁ” ቢልም በአገሮች ላይ በሚያወጣው ሪፖርት ማንነቱን ያሳብቃል እያሉ ይሞግቱታል። ለአብነት የኢትዮጵያን ሰብዓዊ አያያዝ አስመልክቶ በሚያወጣቸው ሪፖርቶች የፖለቲካ ወገንተኝነቱን በግልጽ ያንጸባረቀበት ነው።

አሸባሪው ህወሃት የአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ መንግስት በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለውን የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ በተመለከተ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች መሰረት አልባ ከመሆን ባለፈ፣ በተዛባ ሆን ተብሎ የተዘጋጀና የአሸባሪ ሃይሉን ድምጽ ብቻ የሚያሰሙ ሆነው ተገኝተዋል።

‘’ለሰብዓዊ መብት ጥሰት እቆረቆራለሁ’’ የሚል የትኛውም ድርጅት ወይም ግለሰብ እውነታውን እያወቀ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን ከሚፈጽሙ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ጋር ባለው ቅርበትና ወዳጅነት ምክንያት ከሐቅ መሸሽ ከጀመረ ከጀርባው የተደበቀ ዓላማ መያዙ ለማንም ግልጽ ነው።

በሰብዓዊነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ድርጅቶች ”መርጦ አልቃሽ” የሚሆኑት ቀድሞውንም የሰውን ልጅ እኩል ለማገልገል ባለመቆማቸው ነው። ዋነኛ ማጠንጠኛ ጉዳይ ድብቅ አጀንዳ የፖለቲካ ፍላጎቶችን ለማስፈጸም ለሚፈልጉ ሃይሎች አገልጋይ መሆናቸው ነው።

አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ አንዳንድ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚያወጡት የተንሸዋረረ ዘገባና ሪፖርትም ይህንኑ እውነታ በግልጽ ያንጸባርቃል። እውነትን በሀሰት ቀይረው አሊያም ያለውን መረጃ ለእነርሱ በሚመቻቸው መንገድ አጣመው በማቅረብ አገርን ሰለባ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።

አሸባሪው ህወሃት መላ ኢትዮጵያዊያን ‘’ጭቆና፣ ብዝበዛ፣ ግፍና በደል’’ በቃን ብለው አሽቀንጥረው ከጣሉት በኋላ የትግራይ ክልልን መሽጎ ሴራውን ያሴራል።

የአሸባሪው ቡድን አመራር አባላት በቴሌቭዥን መስኮት እየወጡ የፌዴራል መንግስት አስተዳደር በግልጽ ከመሳደብ ባለፈ የኢትዮጵያን ህዝብ ክብር ዝቅ በሚያደርግ ሁኔታ ዛቻና ማስፈራሪያ ሲያደርጉ እንደነበር የቅርብ ትውስታ ነው።

ከዚህ ማስፈራራትና ትዕቢት በኋላ ለዘመናት የትግራይ ህዝብ ደጀን በሆነው የሰሜን እዝ ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሟል። ይህ የአገርን ክብር የሚነካ ፍጹም ክህደት የተሞላበት ወንጀል ነው። ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የእግር እሳት የሆነውም ለእዚህ ነው።

አሸባሪው ቡድን በስልጣን ዘመኑም ሆነ በእጅ አዙር በሚያሰማራቸው የጥፋት ቅጥረኞቹ አማካኝነት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተቆጥረው የማያልቁ እና ተክሰው የማይሽሩ ግፎችን ሲፈጽምና ሲያስፈጽም ነበር። ዓለም ሰምቶ እንዳልሰማ፤ አይቶ እንዳላየ ሆነ እንጂ!

አሸባሪ ቡድኑ ”ዓላማዬን ያስፈጽሙልኛል”ያላቸውን የውስጥና የውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶችን ወዳጅ በማድረግ አገራችን እንድትወድቅና ከዓለም ካርታ ላይ እንድትወገድ በመቃዠት ተግቶ እየሰራ ይገኛል። ያው ቅዠት ሆኖ እንደሚቀር የታወቀ ቢሆንም ።

አሸባሪው ህወሃት የሰራቸውን ግፎች ለመዘርዘር ጊዜም ቦታም አይበቃም። ከዚህ ይልቅ እርሱ የሰራቸውን ወደ ጎን ብሎ የአዞ እንባ ለማለቀስ የሞከረውን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ”መርጦ አልቃሽነትን” እንመልከት። አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና በሰብዓዊነት ስም የተቋቋሙ አንዳንድ ዓለምአቀፍ ድርጅቶችና የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአሸባሪው ቡድን ጉዳይ አስፈጻሚ መሆናቸውን በግልጽ ማሳየት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

ለዚህም ማሳያው የሚያወጡት ሪፖርትና የሚሰሩት ዘገባ ድርጊታቸውን ያሳብቃል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል የትግራይ ክልልን የተመለከቱ ሪፖርቶችና ክሶች በቀጥታ የጉዳዩን ባለቤቶች ሳይሆን ወንጀል ሰርተው የሸሹትን፣ አሊያም ወንጀል ይፈጸምብኛል በማለት በፍርሃት ውስጥ ያሉ ግለሰቦች በማነጋገር እንደሆነ ከመረጃ አሰባሰቡ ስልት መረዳት ይቻላል።

ድርጅቱ በየጊዜው በሚያወጣቸው ሪፖርቶች በምንጭነት ከጠቀሳቸው እማኞች ውስጥ በማይካድራ ንጹሃንን ጨፍጭፈው ወደ ሱዳን የሸሹ የሳምሪ ቡድን አባላትን ምንም እንዳልሰሩ አድርጎ በዋቢነት መጥቀሱን ልብ ማለቱ ተገቢ ነው።

ድርጅቱ የአሸባሪው ቡድን ጉዳይ አስፈጻሚ መሆኑን ከሚያጋልጡበት ተግባራቱ ማይካድራ ላይ ንጹሃን በማንነታቸው ምክንያት ብቻ ሲጨፈጨፉና በጅምላ ሲቀበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያሳስበኛል የሚል ድርጅት ድርጊቱን ክብደት ሳይሰጠው ቀለል አድርጎት በማየት ሲያልፍና ድርጊቱን ፈጽመው ከሸሹ ወንጀለኞች የሀሰት ምስክርነት ተቀብሎ ሪፖርት ማውጣቱ ነው። ይህ ከጉዳይ አስፈጻሚነት በምን ይለያል?

ድርጅቱ አድሏዊ ሪፖርቱን ሲያወጣ ቢያንስ እንኳን የፌዴራል መንግስትን አቋም ማካተት አልፈለገም። ይህም ከአሸባሪ ቡድኑ ጋር ያለውን ድብቅ አጀንዳ ያጋለጠ ሆኗል። ይህ ባይሆንማ አሸባሪው ታሪካዊቷን የአክሱም ከተማ መንገድን ጨምሮ መሰረተ ልማቶች አውድሞ ሲፈረጥጥ ንጹሃንን ያለ ሃጥያታቸው ሲገድልና ሲያቆስል ሲያቃጥልና ሲያሳድድ ሰሚ ጆሮ ኖሮት ባወገዘ ነበር።

አምነስቲ በዚህ አላበቃም! በኢትዮጵያ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር ተያይዞ ነሃሴ 5 ቀን 2013 ዓ.ም የመርጦ አልቃሽነቱን የሚያረጋግጥ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። ሪፖርቱ ከትግራይ ግጭት ጋር ተያይዞ የመከላከያ ሰራዊት፣ የኤርትና ወታደሮችና የአማራ ልዩ ሃይል በመቶዎች በሚቆጠሩ ሴቶችና ልጃገረዶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት መፈጸማቸውን የሚያትት ነው።

የፌዴራል መንግስት የትግራይ ክልልን ጨምሮ በየትኛውም አካባቢ በሚኖሩ ዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በየትኛውም ወገን መፈጸም እንደሌለበትና የድርጊቱ ፈጻሚዎችን አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳውቋል። ከዚህም በላይ በወንጀሉ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩትን ለፍትህ ለማቅረብ ብዙ ርቀት እየተጓዘ መሆኑም ይታወቃል።

ከትግራይ ክልል የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ጋር ተያይዞም በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተሳትፈዋል ተብለው በተጠረጠሩ የመከላከያ አባላት ላይ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወሰድና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግም በጉዳዩ ላይ ምርመራ መጀመሩ አይዘነጋም።

ለዚህ እርምጃ እውቅና መስጠት ያልፈገው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ግን ከፌዴራል መንግስት በኩል ያለውን እውነታ እያወቀ እንዳላወቀ በዝምታ አልፎ የአሸባሪውን ጩኸት ብቻ ማስተጋባቱን ቀጥሏል። ይህ ዓይነቱ ከጊዜው ጋር ያልተጣጣመ፣ ፍጹም አድሏዊ የሆነ ሪፖርት አሁን ለማውጣት ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ ቢቀርብ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ከሚለው ውጪ ሌላ ምላሽ አይገኝም።

በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን ያጋሩን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት ዳይሬክተርና የህግ ባለሙያ መስሁድ ገበየሁ እንደሚሉት፤ በአለምአቀፍም ሆነ በኢትዮጵያ ህግ በግጭት ጊዜ ንጹሃን ዜጎችን፣ የህዝብና የሃይማኖት ተቋማት የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው።

ይሁንና የፌዴራሉ መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ከትግራይ ክልል አልፎ በአጎራባች ክልሎች ላይ ጥቃት ማድረሱን ተያይዞታል። ይህ ደግሞ ሰብዓዊ እርዳታ በአግባቡ እንዳይደርስ ከማድረግ ባለፈ ከግጭቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ንጹሃን ዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጥስ ተግባር ነው።

ይህ የአለምአቀፉን የጦር ህግ ከመጣስ ባለፈ በግጭት ጊዜ አፋጣኝ የህክምና እርዳታ የሚፈልጉ ዜጎችን ከፍተኛ ተጎጂ የሚያደርግም ነው።

“ለሰብዓዊ መብት እንሟገታለን” የሚሉ ተቋማት፤ በክልሉ ጾታዊ ጥቃትን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆኑን በሚያወጡት ሪፖርት ቢያሳውቁም፤ የችግሩን ባለቤት በማጋለጥ ረገድ ግልጽ የሆነ አድሏዊነት እንደሚታይባቸው ነው ያመለከቱት።

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ኩሌ ኩርሻ እንደሚሉት፤ በሰብዓዊነት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች በየትኛውም ወገን የሚፈጸም ወንጀልን ማውገዝና ማጋለጥ ይገባቸዋል።

የአሸባሪው ህወሃት ቡድን በከባድ መሳሪያ እየተኮሰ መንገድ ዘግቶ የፌዴራል መንግስት ለትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ አለመሆኑን ለአለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ በመግለጽ ሲወቅስና ሲከስ ይሰማል። እነርሱም እወነታውን ወደ ጎን ትተው ለእርሱ ያለቅሳሉ። ይጮሃሉ።

ይሁንና መንግስት ለሰብዓዊ ድጋፍም ሆነ ለእርሻ ስራው ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ አሳልፎ ሕዝቡ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲያገኝ በከፍተኛ ትዕግስት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ሆኖም አሸባሪው ቡድን ወደ ክልሉ የሚላኩ የሰብዓዊ ድጋፎችን በማስተጓጎል “በአንድ ራስ ሁለት ምላስ መሆኑን በተግባር አሳይቷል” ብለዋል።

ይህን ጨምሮ ዕድሜያቸው ያልደረሱ ህጻናትን ለጦርነት በማሰለፍና አብያተ ክርስቲያንን እና በርካታ የህዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶችን ሲያወድም “ለሰብዓዊ መብት እንሟገታለን” የሚሉ ድርጅቶች የት ነበሩ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ አቶ ኩሌ።

የኢትዮጵያ መንግስት ‘’አሸባሪ’’ ብሎ ከፈረጀው ድርጅት ጋር ህብረት መፍጠራቸው በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት ሽፋን ያላቸውን “ድብቅ ዓላማ የሚያሳይ ነው” ብለውታል።

አሸባሪ የተባለን ድርጅት ዓላማ መደገፍና ጥፋቱን መሸፋፈን የየትኛውም ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ወይም ግለሰብ መገለጫ ሊሆን እንደማይችል በማንሳት።

የታሪክ መምህሩ ታዬ ቦጋለ እንደሚሉት፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሚያወጣቸው ሪፖርቶች አድሏዊ መሆናቸው ለየትኛውም ወገን የተደበቀ አይደለም።

ለአብነትም አሸባሪው ቡድን በትግራይ ክልል በሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች እንዲሁም የማይካድራውንና በቅርቡ በአፋር ክልል በንጹሃን ላይ ያደረሰውን ኢ- ሰብዓዊ ድርጊት ”ጆሮ ዳባ ልበስ” ብሎ ማለፉን ያነሳሉ።

የአሸባሪው ህወሃት ታጣቂዎች በንጹሃን ላይ የፈጸሙትን ግፍና በደል በመደበቅ ባልተረጋገጠ መረጃና በሀሰት ምስክር የፌዴራል መንግስትን መውቀሱ “የአሸባሪው ቡድን ዓላማ አስፈጻሚ መሆኑን የሚያመላክት ነው” ብለውታል።

አሸባሪ ቡድኑ የምዕራቡ አለም መገናኛ ብዙሃንና በሰብዓዊ መብት ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን ለእኩይ ዓላማው ማስፈጸሚያ ቀድሞ ያመቻቸው መሆናቸውንም ነው መምህር ታዬ የሚያስረዱት።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን የሚያወጧቸው ዘገባዎች መርጦ አልቃሽነታቸውን የሚያሳብቁ በመሆናቸው ለሚያወጡት ሪፖርትና  ዘገባ ጆሮ መስጠት አቁመዋል።

‘’ውሾች ይጮሐሉ ግመሎችም ይጓዛሉ’’ እንደሚለው ብሂል፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አሸባሪውን የህወሃት ቡድን ግብዓተ መሬት ለመፈጸም ከመቼውም ጊዜ በላይ ቆርጠው ተነስተዋል።

የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ልማትና ብልጽግና የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ ጠላቶችም እውነታውን ወደ ጎን ብለው በሀሰት የመሰከሩበትን ጊዜ የሚረግሙበት ጊዜ ተቃርቧል።

በሰብዓዊ መብት ሰበብ በኢትዮጵያውያን ላይ ጫና ለማድረስ የሚፈልጉ ዓለምአቀፍ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙሃን ተቋማት በጸጸት አንገታቸውን የሚደፉበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።

ኢትዮጵያ  በልጆቿ የተባበረ ክንድ አንድነቷና ነጻነቷን ጠብቃ አለምን እያስደመመች በከፍታ ትኖራለች።ሰላም!

ከኢዜአ

Exit mobile version