Site icon ETHIO12.COM

ከባሕርዳር ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳየች ላይ የተላለፈ ውሳኔ።

በዚህ ወቅት አሸባሪው ትህነግ ሌሎች ተላላኪወችን ጨምሮ በአማራ ሕዝብ ላይ ሂሳብ ለማወራረድና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጦርነት አውጆ በክልላችን የተለያዩ አካባቢዎች ግልፅ ወረራ እየፈፀመብን ይገኛል።

ይህንንም ተከትሎ የክልላችንና የሀገራችን መንግሥት የክተት ጥሪ ማስተላለፋቸው ይታወቃል። የዚህን አሸባሪ ቡድን ቅዠት እንዳይሳካ ለማድረግና ግብዓተ መሬቱን ለመፈም በርካቶች ጥሪውን ተቀብለው በተለያዩ የሠራዊት አደረጃጀቶች ውስጥ እየተሰለፉና ጠላትን ድል እየነሱት ይገኛሉ።

በተለይም መከላከያ ሠራዊታችን፤ ልዩ ኀይላችን፤ ሚሊሻና ፋኖዎች እንዲሁም የፖሊስና የአድማ ብተና ኀይላችን በየግንባሩ እየፈፀሙት ያለው ገድል ታሪክ የማይረሳው ሲሆን አሁንም በድጋሜ የዚህ የታሪካዊ ጠላታችን ግብዓተ መሬት ለማፋጠን በሚደረገው ሀገራዊ ዘመቻ ማንኛውም የከተማችንና የአካባቢው ነዋሪ የሚጠበቅበትን ሁሉ በማድረግ እንዲሳተፍና አባቶቻችን ጠብቀው ያስረከቡንን እምየ ኢትዮጵያ በእኛ ዘመን አትፈርስም ብለው ከተሰለፉ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጎን በመሰለፍ ታሪካዊ ግዴታችንን እንድንወጣ እያሳሰብን የከተማ አስተዳደሩ የጸጥታ ምክር ቤት የሚከተሉትን ዋና ዋና ውሣኔዎች አስተላልፏል፦

1.በከተማችን እና አካባቢዋ የሚገኝ ማንኛውም ኅብረተሰብ ወቅቱን በጠበቀና ባገናዘበ መንገድ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለበት በማመን፤ ስምሪት ከተሰጠው የሕግ አስከባሪ ኃይል ውጭ የማንኛውም ዜጋ የእንቅስቃሴ ገደብ ማስቀመጥ ስለታመነበት ከጠዋቱ 12፡00 እስከ ምሽቱ 2፡00 ብቻ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚቻል ሲሆን የተለየ ድንገተኛ ችግር በገጠመ ጊዜ የአካባቢውን ሰላምና ደኅንነት አካላት በማሳወቅ ከሚደረግ እንቅስቃሴ ውጭ የተገኘ አካል ካለ የጠላት ተባባሪ ተደርጐ እርምጃ እንደሚወሰድበት አምኖ ሁሉም ህዝብና ባለ ድርሻ አካላት ተባባሪ እንዲሆን እናሰገነዝባለን።

  1. በከተማችን የምትገኙ መጠጥ ቤቶች፣ ጭፈራ ቤቶች፣ ፑል ቤቶች እና ማነኛውም የንግድ እንቅስቃሴ ከተቀመጠው የሰዓት ገደብ ውጭ ምንም አይነት አገልግሎት መስጠት የማይቻል መሆኑን በጥብቅ እናሳስባለን፡፡

3.የህዝባዊ ንቅናቄ ሥራን ለመስራት በከተማው በተለያየ መንገድ የተመረጡ አደረጃጀቶችን በመጠቀም የማነሣሣትና ህዝባዊ ግንባር በመፍጠር ለጠላት እሾህ የሆነ ሕዝብ እንዲሆን የማደራጀትና የማንቃት ሥራ ለመስራት ርብርብ ማድረግ ይጠበቃል፡፡

ለዚህም መላው ሕዝብ ተደራጅቶ አካባቢውን ከሰርጎገብ ጠላቶች ሁሉም በቀን ፖትሮል ቅኝት እና በሌሊት ሮንድ እንዲጠብቅ ጥብቅ መመሪያ አስተላልፏል።

4.ለፀጥታ ሥራ ስምሪት ከተሰጣቸው ተሽከርካሪዎች ውጭ በከተማው ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ተሽከርካሪ መንቀሳቀስ የሚችለው ከጧቱ 12:00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2:00 ሰዓት ብቻ ሲሆን ከምሽቱ 2:00 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት በከተማው ውስጥ መንቀሳቀስ እንዲችሉ የተፈቀደላቸው 120 ባለ 3 እግር ተሽከርካሪዎች ብቻ መሆኑ ታውቆ ከተፈቀደላቸው ተሽከርካሪዎች ውጭ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ማንኛውም ተሽከርካሪ በፀጥታ አካላት ተይዞ እርምጃ እንዲወሰድበት ታዝዟል።

  1. ግልፅና የታወቀ ስምሪት ከተሰጣቸው የፀጥታ አካላት ውጭ ከተማው ውስጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ፤ የከተማችን ሰላምና መረጋጋት በጥይት ተኩስ መረበሽ፤ በደስታም ይሁን በሀዘን ምክንያት ጥይት መተኮስ ከዛሬ ጀምሮ ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑ ታውቆ ይህንን ተላልፎ በተገኘ ማንኛውም አካል ላይ መሳሪያውን በማስወረድ እርምጃ እንዲወሰድ የታዘዘ ሲሆን ለተግባራዊነቱ ሁሉም የከተማችን ነዋሪ ቀና ትብበር እንዲያደርግ በጥብቅ እናሳውቃለን።
  2. በከተማም ይሁን በገጠር ያሉ ሁሉም የእምነት ተቋማት፣ የግል ሆቴሎችና ፔንሲዮኖች ውስጥ ጠላት ለመደበቂያና ለመረጃ መረብ አገልግሎት የሚሆኑ ግለሰቦች መሸሸጊያ እንዳይሆኑ ሁሉም አካላት በቅንጅት አስፈላጊውን ፍተሻና ክትትል በማድረግ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ልዩ ስምሪት እንዲሰጥና በጥብቅ ዲሲፒሊን ተግባራዊ እንዲሆንና የወጣት አደረጃጀቶች ከፀጥታ አካላት ጋር ስምሪት ተሰጥቷቸው ተግባሩን በፍፁም የኀላፊነት መንፈስ እንዲፈፀምና የአሸባሪውን የትህነግና የተላላኪዎችን እንቅስቃሴ ተከታትሎ በመያዝ ለህግ አካል ተላልፎ እንዲሰጥ ጥብቅ ውሳኔ ተወሰኗል።

7.የጠላት ፕሮፖጋንዳና ውሸት እጅግ አደገኛ ከመሆኑ የተነሳ የሕዝባችንን ሥነ ልቦና በመስለብ የተሸናፊነትና የፍርሀት ስሜት እንዲያድርበት በማድረግ አለመረጋጋት እንዲፈጠር እያደረገ ነው።

በተለይም የውስጣችን ተላላኪና የጁንታ ሰርጎ ገብ ጦር ግንባር ላይ ያልተፈጠረ ሁኔታ ተፈጠረ በማለት የደጀኑ ህዝብ እንዳይረጋጋ የሚያደርጉ አካላትን ፊት ለፊት በመታገል እና ለፀጥታ አካላት መረጃ በመስጠት የተጠናከረ የስነልቦናና ያልሸነፍም ባይነት የአባቶቻችን ወኔ እንዲላበስ ሁሉም ተልእኮውን እንዲወጣ ማሳሰብ እንወዳለን።

በአጠቃላይ በዚህ ስምሪት ላይ ለሀገር ክብርና ለህዝብ ደህንነት የማይሰለፍና የተቀመጡ አቅጣጫዎችን የማይተገበሩ አካላትም ሆኑ ግለሠቦች ከጁንታው እና ከተላላኪወቻቸው ተለይተው ስለማይታዩ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የፀጥታ ም/ቤቱ በጥብቅ ያሰገነዝባል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ምክር ቤት
ነሐሴ/2013 ዓ.ም
ባሕር ዳር

Exit mobile version