Site icon ETHIO12.COM

የምዕራብ ትንታጎች ሰ-ሰዓት…….

“የምዕራብ ዕዝ ትንታጎች ሰ-ሰዓት የጀመረ ዕለት — ምድረ-ጁንታው ወዮለት”

ከጥቅምት 24ቱ የህወሓታዊያን ባንዳዎች የክህደት ጥቁር-ምሽት ጀምሮ ከምዕራቡ የአገራችን ክፍል ወደ ሰሜን የተመሙት የምዕራብ ዕዝ ትንታጎች ከዳንሻና ባዕኸር በመነሳት ቲርካን ላይ የመሸገውን ጠላት ኩማንዶ ነው ብሎ በሻለቃ ያደራጀውን ሀይል በመደምሰስ የጀመረው ግስጋሴያቸው ኢንዱስትሪ ፓርክን ፣ ሁመራ ፣ ሽራሮ ፣ ሽሬ ፣ ሀውዜን ፣ ውቅሮ እና መቐለን ከጁንታው ሀይል በማፅዳት ወደ ተምቤን ዙሪያ-ገቦች በመፈርጠጥ ዋሻ ገብቶ የተሸሸገውን የጁንታ አመራሮች በማደን ለአፍታ እረፍት ሳያሻቸው ሌት ተቀን ተግተው ወደር የሌለው ጀግንነት በመፈፀም ህዝብ አኑረዋል ፤ አገር አሻግረዋል፡፡

በተከዜ ሸለቆዎችና በተምቤን ጉራንጉሮች በአሸባሪው ህወሀት ተዘርፈው የነበሩ ዲፖዎችንና በዘራፊ ቡድኑ ተወስደውና ተቀብረው የነበሩ መጠነ-ብዙ የአገር ሃብቶችን በማስመለስ ለተቋሙ ገቢ ያደረጉት የምዕራብ ዕዝ ትንታጎች የሽብር ቡድኑ ሴራ ወጣኝ የነበረውን አቦይ ስብሃት ነጋን ጨምሮ የጁንታውን ቁንጮ አመራሮች ከተደበቁበት በማውጣት ለህግ በማቅረብ የፈፀሙት ግዳጅ በደማቅ ቀለም ተፅፎ ለታሪክ ተቀምጧል ።

የሽብር ቡድኑ ድል ተነስቶ ወደ ሽምቅ እንቅስቃሴ ቢሸጋገርም የዕዙ አባላት በፀረ-ሽምቅ ተጋድሏቸው ወሳኝ ፍልሚያዎችን አድርገው ጠላትን ድባቅ መተዋል። በሁዋላም በመንግስት ፖለቲካዊ ውሳኔ መሰረት ከተምቤን በየጭላ ወደ ደጀን ሲወጣም ከጁንታው ሀይል እና የጁንታው የአላማ ተጋሪ ከሆነው ሃይል ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው ከቀጣናው መውጣት ችለዋል ።

ዕዙ ተጨማሪ ግዳጅ በመቀበልም በማይፀብሪ ፣ አዲርቃይ እና በዘሪማ ሾልከው በመግባት ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ለመፈፀም ያደረጉትን ሙከራ ማክሸፍ ችለዋል ።

ደጀን ወደሆነው ህዝብ ከወጡ በኋላም ባሉበት የመከላከል ቁመና ላይ ሆነው ባለፉት ጊዜያት የነበሩ ግዳጆችን ጠንካራ ጎኖች በማጎልበትና ትኩረት በሚሹ አሃዳዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ርብርብ በማድረግ ለቀጣይ ተልዕኮ በተገቢው መንገድ ማሳለጥ በሚችል ሁኔታ መሠረት ወቅቱን የዋጀ አደረጃጀትን በመከተል በነፍስ-ወከፍና በቡድን መሳሪያዎች ፣ በሜካናይዝድና በልዩልዩ ሙያዎች በየዘርፉ ተመጣጣኝ የውጊያ አካል ብቃትን የመገንባት ተግባራትን በመከወን ላይ ሲሆኑ በጋራ መናበብ ፣ በአላማዊ አንድነት ፣ በእሳት ተፈትነው ባለፉበት ጀግንነታዊ አብነት ፣ በተባበረ ክንዳቸው ተደማሪ አቅሞችን ፈጥረው ለቀጣይ ግዳጃቸው በተጠንቀቅ ቆመዋል፡፡

ዕዙ ያለበትን አሁናዊ የዝግጁነት አቅምና የግዳጅ ቁመና በማረጋገጥ የሰነበቱት የምዕራብ ዕዝ በየደረጃው ያለው ኮማንድ አመራሮች በተለይ አቅም ፈጣሪ አቅሞች ላይ የመረባረብ ሂደቶችን መሠረት በማድረግ በቅርቡ የተቀላቀሉ አዳዲስ አባላትን ወጥ በሆነ የግዳጅ ዝግጁነት የመፍጠር ተግባራትን ቃኝተዋል፡፡

“በውስጥም በውጭም በአገራችን ላይ እየተደረገ ያለው ጫና ይበልጥ እንድንጠነክር ፣ እንድንሰለጥን እንድንዘጋጅ አድርጎናል፡፡” የሚሉት የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ፣ መላው የዕዙ የሰራዊት አባላት በቀጣይ ለሚሰጠን ማንኛውም የግዳጅ ስምሪት በመዘጋጀት የጁንታውን የመጨረሻ ግብዓተ መሬት ለመፈፀም ሁሉም አመራር ፣ አባል መትጋት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የዕዙ አመራርና አባላት በበኩላቸው የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍለው በተለመደው የጀግንነት ተግባራቸውና አይበገሬነታቸው በአገራችን ላይ የሚነሱ እኩይ ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎችን ለመደምሰስ የሚያስችል አቅምና ብቃት ላይ እንደሚገኙ አረጋግጠውላቸዋል፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ አገራችንን ወደ ታላቅ የእድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ያለአንዳች እንከን እንዲከናወኑ ተግተው የሚገኙት የምዕራብ ትንታጎች የኦነግ ሸኔ አሸባሪ ቡድንን አከርካሪ በመስበርም ወደር የላቸውም፡፡

እነሱ እንዳሉት አሁን ሳይሆን ከቀደሙት ጊዜያት ጀምሮ የፍርሻ ጋብቻ እንደፈፀሙ ያወጁትን የህወሓትና የኦነግ ሸኔ ቡድኖችን የሴራ ትብትብ ለመበጣጠስ በሚያውቁበት የጀግንነት ብልሃት የፈረጠመ ክንዳቸውን ለማሳረፍ ዝግጁ ናቸው፡፡

መላው የዕዙ አባላት ያላቸው አሁናዊ ኢትዮጵያዊ ስነልቦና እና ስሜት የዕዙ አባል የሆነው መ/አ ዘሪሁን ኑሪ በቅርቡ ያሰፈረውን አንድ ፅሁፍ ያስታውሳል ። “በራሳችን ተይዞ የነበረውን ሰዓት አሻሽለን መቐለ እንገባለን!!” ብሎ ነበር መኮንኑ፡፡

አዎ የምዕራብ ትንታጎች የትህነግ አሸባሪ ሀይሎችን አንገት በመቁረጥ ልክ በመጀመሪያው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ወቅት መቐለን ቀድሞ በመቆጣጠር በራሳቸው ተይዞ የነበረውን ሰዓት በራሳቸው አሻሽለው ከሃዲያንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ቃላቸውም ታድሷል ። ትጥቃቸውም ጠብቋል ። የሚጠብቁት አንድ ነገር ብቻ ነው – የበላይ አካልን የመጨረሻ ትዕዛዝ ፡፡

“የምዕራብ ዕዝ ትንታጎች ሰ-ሰዓት የጀመረ ዕለት — ምድረ-ጁንታው ወዮለት”

“ኢትዮጵያ ታሸንፋለች”

መላክ በቃሉ ( ከግዳጅ ቀጣና ) ነሀሴ 8 ቀን 2013
ፎቶግራፍ ተሰማ ኡርጌሳ via Defence Facebook

Exit mobile version