ETHIO12.COM

እየዘረፈ ሲሸሽ የነበረ የትህነግ ሃይል ተመታ፣ በምዕራብ ግንባር “ትልቅ”የተባለ ድል ተመዘገበ

በአማራ ክልል በምዕራበ ግንባር በዛሬማ፣በጨው በር እና በር ማሪያም በተባሉ አካባቢዎች ላይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአየር ሀይል፣ ለሰራዊቱ ደጀን የሆነው የአማራ ህዝብ፣ የክልሉ ልዩ ሀይልና ታጣቂው በመቀናጀት በሽብርተኛው ህወሃት ታጣቂ ቡድን ላይ በወሰዱት እርምጃ ሽብርተኛው ቡድን ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንደደረስበት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ይህን ተከትሎም በበርካታ ተሸካርካሪዎች አስክሬኖችን ጭኖ ወደ ማይፀብሪ የወሰደ ሲሆን፤ በዚህ ውጊያ ላይ ስሙ ለግዜው ያልታወቀ አንድ የበድኑ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር አስክሬንም በፓትሮል ታጅቦ ወደ ማይፀብሪ ተወስዷል፡፡

በተመሳሳይ በአድርቃይ በነበሩ የታጠቂው ቡድን ላይ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም የክልሉ ልዩ ሀይልና ታጣቂው ሀይል የወሰደባቸውን እርምጃ የሽብርተኛው ታጣቂ ቡድን አመራሮችም የቀረው ሀይል ወደ ማይፀብሪ እንዲሸሽ ትዕዛዝ የሰጡ ሲሆን፤ በእነዚሁ አካባቢዎች ተቆርጦ የቀረውን የአሸባሪውን ታጣቂ ሀይል እዚያው ለማስቀረትና ለመደምሰስ እርምጃው ተጠናከሮ ቀጥሏል ብለዋል ምንጮቻችን፡፡

በተያያዘም በጋሸና ግንባር ሳሊና እና ጎብጎብ በተባሉ አካባቢዎች በአሸባሪው ቡድን ላይ በተወሰደ የአየር ጥቃት እርምጃ ቡድኑ ከፍተኛ ሰበአዊና ቁሳዊ ኪሳራ የገጠመው ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም ቡድኑ ወደኋላ
በመሸሽ ከሰሜን ወሎ ዞን እስታይሽ፣ አሁንተገኝ፣ ጋሸና፣ ገርገራ እና ፍላቂት ከተሞች ላይ ከመንግስት ተቋማት፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ደርጅቶችና ተቋማት እንዲሁም ከህብረተሰቡ በርካታ ንብረቶችን በመዝረፍ ቁጥራቸው በዛያለ ተሸከርካሪዎች ላይ ጭኖ ወደ ትግራይ ለመውሰድ ሲንቀሳቀስ ቲሃ የተባለ አካባቢ ቆፍጣናው የአማራ አርሶአደሩ ንብረቱን ይዞ እንዳይሄድ በከፈተበት የደፈጣ ተኮስ ተደናግጦ ሲደናበር፤ የአማራ ልዩ ሀይልና ታጣቂው በቦታው በመድረስ ከአርሶአደሩ ጋር በመቀናጀት በወሰዱት እርምጃ በትናንትናው ዕለት የዘረፈውን ንብረት ጥሎ አስ ወደ ተባለ ከተማ አቅራቢያ መሸሹ ታውቋል።

ጀግናው የአማራ ክልል ልዩ ሀይልና ታጣቂው ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን አሸባሪው ህወሃት ያሰማራውን ታጣቂ ሀይል እግር በእግር በመከታተል እርምጃ መውሰዱን በዛሬው ዕለትም የቀጠሉ ሲሆን፤ ይህንን ሀይል ባለበት ለማስቀረት እየተደረገ ያለው ከፍተኛ ትንቅንቅና ተጋድሎ መቀጠሉን ምንጮቻችን ከስፍራው አረጋግጠዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአፋር ግንባርም በሀሮ መስመር በድሬእሮቃ አረርቲ በተባለች ቦታ ላይ የሽብርተኛው ህወሃት ታጣቂዎች ትናንት ማታ (በ8/12/2013 ዓ.ም) የፈፀሙትን ድንገተኛ ትንኮሳ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከአፋር ክልል ልዩ ሀይልና ታጣቂ ጋር በቅንጀት በወሰዱበት የአፀፋ እርምጃ ቡድኑ ተደምስሷል።
በዚህም በርካታ የቡድኑ ታጣቂዎች ሙትና ቁስለኛ ሲሆኑ፤ ዲሽቃዎችን ጨምሮ በርካታ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ከቡድኑ መማረካቸውን ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡

Exit mobile version