Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያ እና ቱርክ ወታደራዊ ዘርፎች ስምምነት ፈጸሙ

ኢትዮጵያ እና ቱርክ በወታደራዊ እና በውሃ ዘርፎች ዙሪያ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡የወታደራዊ ዘርፍ ስምምነቱን የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነአ ያደታ ከቱርክ አቻቸው ጋር ተፈራርመውታል፡፡ስምምነቱ በይፋ አልተዘረዘረም።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በኢትዮጵያ እና በቱርክ መካከል የተደረጉ ስምምነቶችም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ መሆኑን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡ቱርክ በኢትዮጵያ ቀጣይነት ላለው እድገት እና ሰላም የምታደርገውን ድጋፍ እንደሚያደንቁም አውስተዋል።

“የለውጥ ሂደቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያና ቱርክ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ተናግረዋል። ኢትዮጵያና ቱርክ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር የሚያስችሉ ተጨማሪ ስምምነቶችን ዛሬ ተፈራርመዋል።በቱርክ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥተዋል።

ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን በመግለጫቸወ እንደተናገሩት፤ ሁለቱ አገሮች ያላቸው ግንኙነት ወንድማማችነት ነው።በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው ልዑክ ጋር በነበራቸው ቆይታ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል።ከመከሩበት ጉዳይ መካከል አንዱ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቱን ማሳደግ እንደሆነ ተናግረዋል።

የቱርክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸው ኢንቨስትመንት 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ገልጸው፤ ይህንን ማሳደግ በሚቻልበት ዙሪያ መምከራቸውን ተናግረዋል።በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት የሚያደርጉ የቱርክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ለኩባንያዎቹ ድጋፍ እያደረገች ስለመሆኗም ገልጸዋል።በቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን ያወሱት ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን “የኢትዮጵያ ሰላም መሆን እኛን ጨምሮ ለሁሉም ወሳኝ ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ግጭቶች እንደሚፈቱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተፈጠረው አለመግባባት መፈታት እንደሚገባው የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ ቱርክ ማደራደርን ጨምሮ ሰላም ለማምጣት የድርሻዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በበኩላቸው ቱርክ በምሳሌነት ሊወሳ በሚችል የአገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ማለፏን ጠቅሰው፤ በሁሉም ዘርፍ ወጥነት ያለው እድገት ማስመዝገቧን እንደቀጠለች ገልጸዋል።

የአውሮፓና የእስያ መገናኛ ድልድይ ከሆነችውና ስትራተጂካዊ አቀማመጥ ካላት ቱርክ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር በኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ከጀመረበት መጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።ለቱርክ ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረች እንደምትገኝ አረጋግጠዋል።የሁለቱን አገሮች የቆየ ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ዛሬ ተጨማሪ ስምምነት መፈረሙን ጠቁመዋል።

የተደረገው ስምምነት ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነትን ለማጠናከር፣ ለማስቀጠልና በተግባር ለመተርጎም እንደሚያግዝ ተናግረዋል።የኢትዮጵያና የቱርክ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ፤ ከአዲስ አበባ ኢስታንቡል በየዕለቱ የሚደረገው በረራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ሚናውን እየተወጣ እንደሆነ ገልጸዋል።የቱርክ የፊልም ኢንዱስትሪም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ረገድ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከተለያዩ የመንግስት መገናኛዎች የተወሰደ

Exit mobile version