Site icon ETHIO12.COM

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ሁለት አማራጮች ብቻ ቀሩት

አሸባሪው ህወሃት እጅ ከመስጠት ወይም ከመወገድ ውጭ ምርጫ የለውም ሲሉ ሁለት አማራጮች ብቻ እንዳሉት ተገለጸ። ሰርጎ የገባው አሸባሪው ህወሃት በተከታታይ በተካሄደበት ዘመቻ በመዳከሙ አሁን ላይ እጅ ከመስጠት ወይም ከመወገድ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለው የገለጹት የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ ናቸው።

ቢሮው ሰሞኑን የተካሄዱ ዓውደ ውጊያዎችንና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ዶክተር ሰማ ጥሩነህ እንዳሉት ጠላት በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ጎንደር፣ ዋግ ኽምራና ሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ወረራ መፈጸሙን ።አሸባሪ ቡድኑ ያካሄደው ወረራ በመከላከያ ሰራዊት፣ በየክልሉ ልዩ ሃይሎችና በአማራ ሚሊሻ የጸጥታ ሃይሎች ተጋድሎ እየተመከተ መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪው በአሁኑ ወቅት በገባባቸው የጉናና ሌሎች አካባቢዎች ተቆራርጦ የሚገኝ በመሆኑ ሊደምሰስ ወይም እጅ መስጠት ግድ እንደሚለው አስረድተዋል።በሰሜን ወሎና አካባቢው ግንባር ከጋሸና፣ አንጎት፣ እስታይሽ፣ ቀበሮ ሜዳና ሌሎች አካባቢዎች በጸጥታ ሃይል በህዝቡ የነቃ ተሳትፎ ከአሸባሪው ቡድን ነጻ ሊሆን መቻሉን ተናግረዋል።“ጠላት በነበረው ያረጀና ያፈጀ የፖለቲካ አስተሳሰብ በአማራ ክልል የሚገኙ ብሄሮችን በመከፋፈል የራሱን እኩይ ፍላጎት ለማሳካት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም” ብለዋል።

አሸባሪው ህወሃት ባሰማራቸው ጥቂት ቅጥረኞች አማካኝነት የቅማንትን ማህበረሰብ ከጎኑ በማሰለፍ ደጀን ለማድረግ ያደረገው ሙከራ መክሸፉ ለዚህ ማሳያ መሆኑን አስረድዋል።“ይልቁንም የቅማንት ህዝብ አብሮት ከኖረው የጎንደር ህዝብ ጋር በመሰለፍ የአሸባሪውን ቡድን መውጫ መግቢያ በማሳጣት የፈጸመው ተጋድሎ ታሪክ ለወደፊት ሲዘክረው የሚኖር ነው” ብለዋል።

መላው የክልሉ ህዝብ አሸባሪው ቡድን ገዳይ፣ ጨፍጫፊ፣ ዘራፊና አውዳሚ መሆኑን መገንዘቡን ጠቁመው፤ በአውደ ውጊያዎች ላይም ከጸጥታ ሃይሉ ጎን በመሰለፍ ኪሳራ እያደረሰበት እንደሚገኝ አመልክተዋል።“የጠላት ዓላማ የአማራን ህዝብ በማጥፋት ኢትዮጵያን ማፈራረስ ነው” ያሉት ዶክተር ሰማ ፤ “አሁን ላይ በየግንባር የሚገኘው የጸጥታ ሃይል ከአካባቢው ህዝብ ጋር በመተባበር እብሪቱን እያስተነፈሰው ይገኛል” ብለዋል።

“ጠላት አሁን ላይ በየቦታው ተቆራርጦ በከበባ ውስጥ በመሆኑ መውጫና መግቢያ በማጣቱ በቅርብ ጊዜ በማስወገድ የህዝባችንን ህልውና እናረጋግጣለን” በማለትም ገልጸዋል።አቅም ያለው ወደ ግንባር በመዝመት አቅም የሌለው ደግሞ ስንቅና ትጥቅ በማዘጋጀት ለህልውና ትግሉ ህዝቡ በሙሉ አቅሙ እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ማሳሰባቸውን የአማራ መገናኛ ኮርፖሬሽን ነው የዘገበው።

Exit mobile version