Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያ ፌስቡክንና ትዊተርን ሊተካ የሚችል የማህበራዊ ትስስር ገጽ ስራ ላይ ልታውል ነው


ፌስቡክን እና ትዊተርን ሊተካ የሚችልና ቢያንስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጠቀም የሚስያችል የማህበራዊ ትስስር ገጽ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) አስታወቁ።

ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ” አሁን ባለንበት ሁኔታም ፌስቡክ እና ትዊተርን ለአብነት ማንሳት ይቻላል ” ብለዋል።

“ኢትዮጵያዊ የሆኑ እና እውነትን የያዙ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚሰራጩ እና ተጽእኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ መልእክቶች ካሉ ፌስቡክ በአስቸኳይ እንዲጠፉ እያደረገ ነው” ያሉት ዶ/ር ሹመቴ፤ ትዊተርም አሁን ጀምሯል ሲሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያዊ እውነታ ይዘት ያላቸው፣ ለሀገር ግንባታ የሚውል፣ አንድነትን፣ ፍቅርን እና ሰላምን የሚሰብኩ ይዘቶችን የሚያሰራጩ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ገጾች እየተዘጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

እነዚህ የማህበራዊ ትስስር ገጾች የኛ አይደሉም ያሉት ዶ/ር ሹመቴ፤ “የሚያዋጣን ነገር የራሳችን የሆነ ፌስቡክን እና ትዊተርን ሊተካ የሚችል እንዲሁም ቢያንስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጠቀም የሚስያችል የማህበራዊ ትስስር ገጽ መፍጠር ነው” በሚል እየተሰራበት መሆኑን አስታውቀዋል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የለሙ የተግባቦት (የኮሙዩኒኬሽን) ፕላትፎርሞች ወደ ሙከራ መግባታቸውንም ገልጸዋል ።

ከእነዚህም ውስጥ ለስብሰባ የሚሆኑ፣ የኮሙዩኒኬሽን እንዲሁም የመረጃ መለዋወጫ መተግበሪያዎች አሁን ላይ የለሙ እና በሙከራ ደረጃ እየተሰራባቸው ያሉ መሆኑን ጠቅሰዋል። አስፈላጊው መሰረት ልማት ተሟልቶላቸው በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚለቀቁ መሆኑንም ዶክተር ሹመቴ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል።

Exit mobile version