Site icon ETHIO12.COM

ለሸኔ የሽብር ቡድን ሊላክ የነበረ የጦር መሳሪያ ተያዘ

በአንድ የሲሚንቶ ማጓጓዣ ከባድ ተሽከርካሪ በድብቅ ተጭኖ ከደብረ ብርሃን በአዲስ አበባ በኩል ወደ ሰሜን ሸዋ ሊጓጓዝ የነበረ የጦር መሳሪያ ተይዟል።

ለሽብር ቡድኑ ሊደርስ የነበረው የጦር መሳሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ ሳይወጣ በተደረገበት ልዩ ክትትል በቁጥጥር ሥር መዋሉን የደህንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ገልጿል።

መሳሪያው ለሸኔ የሽብር ቡድን እንዲደርስ ታስቦ ሲጓጓዝ መያዙንም ነው መግለጫው ያስታወቀው።

ተጠርጣሪዎቹ ስሚንቶ ከጫነ ከባድ ተሽከርካሪ በተለምዶ ደርብራተር ተብሎ ከሚጠራው የውስጥ አካል ውስጥ መሳሪያ ደብቀው በመጫን ለማሳለፍ ሲሞክሩ አዲስ አበባ ሲደርሱ፤ከመነሻው በደህንነትና በፀጥታ አካላት ጥብቅ ክትትል ሲደረግባቸው ስለነበር በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።

የወንጀል ድርጊቱ ተዋናይ የነበረው ሹፌር እንደተደረሰበት ሲያውቅ አደጋ በማድረስ ለጊዜው የተሰወረ ቢሆንም ክትትል እየተደረገበት ይገኛል።

ተሽከርካሪውን በፒክ አፕ መኪና ሲከተሉት የነበሩት ሌሎች የወንጀሉ አራት ተጠርጣሪዎች ግን በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ለተፈረጀው የሸኔ የሽብር ተግባር መፈጸሚያ የሚውሉ በርካታ የጦር መሳሪያዎችና ጥይቶች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲጓጓዙ በደህንነትና በፀጥታ አካላት ጥብቅ ክትልልና ፍተሻ በተደጋጋሚ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን የፌደራል የደህንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ሀይል መግለጫው አስታውሷል።

Via EBC

Exit mobile version