Site icon ETHIO12.COM

የፀረ-ሙስና ኮሚሽን 34 የተለያዩ ወንጀል ነክ ጥቆማዎችን ለፖሊስ ላከ

የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን 34 የተለያዩ ወንጀል ነክ ጥቆማዎችን ለፖሊስ መላኩን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ከሙስና ቅድመ መከላከል ሥራዎች ጋር በተያያዘ ሲቀበላቸው ከነበሩ ጥቆማዎች ውስጥ 34ቱ ከኮሚሽኑ የሥልጣን ክልል ውጭ በመሆናቸውና የወንጀል ምርመራ የሚያስፈልጋቸው ሆነው በመገኘታቸው ለአዲስ አበባና ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርምራ መላኩን አስታውቋል፡፡

በፀረ-ሙስና ህግ ምክር፣ ትግበራና ልምድ ቅመራ ዳይሬክቶሬት በኩል የሚቀርቡለትን የተለያዩ የሙስና መከላከል ጥቆማዎችን እየተቀበለ አስፈላጊውን መረጃ በማጠናከር የቅድመ መከላከል ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የወንጀል ድርጊት ሆነው የተገኙ ጥቆማዎችን ደግሞ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 22(3) መሰረት ጉዳዩን የመመርመር ሥልጣን ላለው አካል ይልካል፡፡

በዚህም መሰረት ከግንቦት እስከ ሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ለኮሚሽኑ ከቀረቡ ጥቆማዎች ውስጥ 34ቱ ወንጀል ነክ ጥቆማዎች ሆነው በመገኘታቸውና ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልጋቸው በመታመኑ ለአዲስ አበባና ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል መላካቸው ታውቋል፡፡

ለምርመራ የተላኩት የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች በአብዛኛው በሚከተሉት ጉዳዮች ዙሪያ የተፈፀሙ መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በተለያዩ ቼኮች በግለሰብ ስም ገንዘብ መውሰድ፣ የመንግስትን ቤትን ወደ ግል ይዞታነት እንዲዞር ማድረግ፣ በመንግስት ይዞታ ላይ ካርታ እንዲሰጥ ማድረግ፣ ለዋጋ ማረጋጊያ የመጣን የፍጆታ ዕቃ ለህብረተሰቡ ሳይደርስ መሸጥ፣ በተቋም ገንዘብ ለግለሰብ አክሲዮን መግዛት፣ ያልተገባ ስጦታ መቀበል፣ የመንግስትን እና የህዝብን ገንዘብ ማጉደል፣ ከውጭ የተላከን ንብረት ባለቤት ላልሆነ ሰው መስጠት፣ ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት የመንግስት ገንዘብን ለመመዝበር ጥረት ማድረግ እና ሕግን ባልተከተለ መልኩ የጨረታ ሂደት ቅድሚያ ክፍያ መክፈል የሚሉት በዋናነት የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎች እንደሆኑ የቀረቡት ጥቆማዎች ያመለክታሉ፡፡

FBC

Exit mobile version