Site icon ETHIO12.COM

የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ለፀጥታው ምክር ቤት በቱኒዚያ የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ እንዲደረግ ተጠየቀ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በቱኒዚያ የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ እንዲያደርግ ተጠየቀ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት አምባሳደሮችን አነጋግረዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ በቱኒዚያ አማካይነት የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ እንዲያደረግ የምክር ቤቱ አባል ሀገራት አምባሳደሮችን ባነጋገሩበት ወቅት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ በበኩላቸው የአባይን ውሃ አጠቃላይ መረጃ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የግንባታ ደረጃ እና የግድቡ ጠቀሜታን፤ በቱኒዚያ አማካይነት ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ይዘት በተመለከተ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያን አቋም አስመልክቶ ለአምባሳደሮቹ ገለጻ ሰጥተዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የልማት ፕሮጀክት በመሆኑ በጸጥታው ምክር ቤት መታየት የሌለበት ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

አያያዘውም ከዚህ በፊት በፈረንጆቹ ሃምሌ ወር ጉዳዩ ለጸጥታው ምክር ቤት ቀርቦ፤ ሶስቱ ሀገራት በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚካሄደውን የሶትስትዮሽ ድርድር በማስቀጠል መፍትሔ ላይ እንዲደርሱ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ጉዳዩ ዳግም በቱኒዚያ በኩል ወደ ምክር ቤቱ መቅረቡ ተገቢ እንዳልሆነ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በቱኒዚያ የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም መብት የሚጋፋ እና ኢ-ፍትሃዊ የሆነውን የታችኞቹን የተፋሰሱ ሀገራት ጥቅም ብቻ ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ሱዳንና ግብጽ ጉዳዩን ፖለቲካዊና ዓለም አቀፋዊ ከማድረግ ይልቅ በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር እንዲሳተፉ እንዲሁም የናይል አጠቃላይ ስምምነት ማዕቀፍን እንዲፈርሙ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

አያይዘውም ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሶስትዮሽ ድርድሩን በማስቀጠል የሶስቱን ሃገራት ሃሳብ በማካተት ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ እንዲደረስ በዝግጅት ላይ ናት ማለታቸውን የጭው ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድርን በማስቀጠል ከስምምነት ላይ እንዲደረስ ቁርጠኛ መሆኗን ጠቅሰው፥ በቱኒዚያ የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ምክር ቤቱ እንዳያሳልፈው አምባሳደሮቹ ለየሀገሮቻቸው መልዕክቱን እንዲያስተላልፉ ጠይቀዋል፡፡

OBN

Exit mobile version