Site icon ETHIO12.COM

የትግራይ ወጣቶች እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ የተማረኩ የአሸባሪ ቡድን አባላት ጥሪ አቀረቡ

ሽብርተኛው ትህነግ የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ሠላም ሆኖ ማደር ያመዋል፤ የህጻናት፣ ወጣቶች እና አረጋውያን በሚመጥናቸው መስክ መሰማራት ለሱ ሽንፈት ነው፡፡ እናም ሀገር የማፍረስ እኩይ ጥማቱን ለማሳካት በከፈተው ጦርነት ዛሬም በርካታ ንጹሃን የሕይወት፣ የገንዘብ እና የሞራል ዋጋ እየከፈሉ ነው፡፡

ይህ የሽብር ቡድን ከምድረ ገጽ ካልጠፋ የትግራይ ብሎም ለተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም የማይሰጥ ነቀርሳ መሆኑን ነው በሰሜን ወሎ ዞን የተማረኩ የሽብር ቡድኑ አባላት የገለጹት፡፡

ለትሽ መረሳ ትባላለች፤ ሽብርተኛው ትህነግ ሰሜን ወሎ አካባቢ ባደረገው ወረራ በጦርነት መሃል ከበርካታ የሽብርተኛው ትህነግ አባላት ጋር ተሰልፋ ነው በአናብስቱ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት የተማረከችው፡፡ ለትሽ ለቤተሰቦቿ የመጀመሪያ ልጅ ናት፡፡ ቤተሰቦቿ ትግራይ ክልል ተንቤን አካባቢ በግብርና ሥራ ነው የሚተዳደሩት፡፡ እንደ በኩር ልጅ ለዛውም አንደ ኢትዮጵያዊ ሴት ልጅ ከወላጆቿ ቀጥሎ ታናናሾቿን ብሎም ቤተሰቡን የማስተዳደር ሙሉ ኀላፊት በሷ ትከሻ ላይ ነበር፡፡ እድሜዋ 17 ዓመት ቢሆንም ያለባት የቤት ውስጥ ኀላፊት ትምህርቷን እንኳ ከስድስተኛ ክፍል ፈቅ እንዲል አላስቻላትም፡፡ ትምህርቷን አቋርጣ ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን የቤተሰቦቿን ኑሮ ለማገዝ ብትወስንም “ተወራችኋል፤ ጠላት መጣ፤ ሊፈጇችሁ ነው፤” የሚለው የስግብግቡ እና በሕጻናት ደም የሚነግደው አሸባሪው ቡድን ትህነግ ኑሮዋን ምስቅልቅሉን አወጣው፡፡

እዛ በየቤቱ እየዞሩ እረፍት የለሽ ጦር ደላቂ የሽብርተኛው ትህነግ ካድሬዎችን ጩኸት አልሰማም ብሎ አርፎ መቀመጥ አይቻልም፡፡ የእርዳታ እህል ያስከለክላል፤ ያሳስራል፤ ሲልም ያስገድላል፡፡ የእነ ለትሽ ቤተሰብ እድሜዋ ባይደርስም የቤቱ ታላቅ እሷ ናትን ቤተሰቡን ወክላ ለሽብርተኛው መሰለፍ ግድ ሆነባት።

ለወትሮውም “የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይበላችኋል፤ ሌላ ቋንቋ እንዳትናገሩ፤ መዋጋት፣ መግደል ብቻ ነው አማራጫችሁ፤” ብሎ በጥላቻ እየመረዘ ያሳደጋቸውን ሕጻናት ለጦርነት እየማገዳቸው እንደሆነ ነው ለትሽ በሲቃ የምታወራው፡፡

የሽብርተኛው እና ወራሪው ትህነግ ትጥቅ ጥላቻ፣ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እና ማስፈራራት እንጂ ስለ ጦር መሳሪያ አጠቃቀም እንኳን በቂ ስልጠና እንዳልሰጣቸው ነው የነገረችን፡፡

ለትሽ እጆቿ እንኳን ለጦር መሳሪያ ያለባትን የብኩርና ኀላፊነት በአግባቡ እንድትወጣ እንኳ እንደማይመጥኑ ነው የገለጸችው፡፡ በጦርነት መኀል ሰብዓዊነት ተሰምቷቸው በህይወት እንድትተርፍ የረዷትን እና እድል የሰጧትን የአማራ ልዩ ኃይል አባላት አመሥግናለች፡፡ “አካባቢያችሁን እንድትጠብቁ ነው የሚፈለገው፤ ርቃችሁ አትሄዱም ብለው ነው ከቤተሰቦቻችን የነጠሉን፤ ነገር ግን መሃል ጦርነት ውስጥ ነበር ጋሸና አካባቢ የማገዱን፤ በርካታ ጓደኞቼ ሞተዋል፤ እኔ እጄን ሰጠሁ” ነው ያለቸው፡፡

እዚህ በአማራ ልዩ ኀይል እና በኀብረተሰቡ እየተደረገላት ያለው እንክብካቤ ሽብርተኛው ትህነግ መንደራቸው ከሚነዛው የሐሰት ቅስቀሳ እጅግ ተቃራኒ እንደሆነ ነው ለትሽ የተናገረችው፡፡ የትግራይ ወጣቶች በፍጹም መታለል እና ራሳቸውን ለመስዋእትነት ማቅረብ እንደሌለባቸውም ነው የመከረችው፡፡

በጦር ሜዳ ያሉትም ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ እጅ መስጠት አለባቸው ብላለች፡፡

ገብረ ሕይወት ተከስተም እነ ለትሽ በሳተፉበት የጦር ግንባር ነው የተማረከው፡፡ ትግራይ ክልል ሓሓይለ ወረዳ ነዋሪ እና በበግ ንግድ ነበር የሚተዳደረው፡፡ ገብረ ሕይወት የንግድ ሥራው እስከ ሁመራ ባሉ የአማራ ክልል አካባቢዎች ስለሚመጣ የአማራን ብሎም የተቀረውን ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ደግነት፣ ሠላማዊነት እና ሽብርተኛው ትህነግ እንደሚለው እንዳልሆነ በደንብ ያውቀዋል፡፡ ከዚህ በፊት በማንም ምንም ጉዳት እንዳልደረሰበትም ነው የተናገረው፡፡

ሽብርተኛው ትህነግ “ትግራይ ተወራለች” ቅዠቱ ራሱን እንቅልፍ ሲነሳው የነ ገብረ ሕይወት ሰላማዊ ሕይወትም መበጥበጥ ጀመረ፡፡ በግድ መዝመት እንዳለባቸው አለበለዚያ የከፋ ችግር እንደሚገጥማቸው በተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርሳቸው እንደነበር ነው ገብረ ሕይወት የገለጸው፡፡

እሱ እና በርካታ የሓሓይለ ወረዳ ነዋሪዎች ታፍሰው ወደ ስልጠና ከዛም ወደ ጦርነት ተማገዱ፡፡ ጋሸና ላይ የጦር አመራሮቻቸው እንደተገደሉ እና የተወሰኑት ጥለዋቸው እንደሸሹ ተናግሯል፡፡ ገብረሕይወት በደረሱባቸው የአማራ ክልል ከተሞች በሙሉ ዝርፊያ እና ያገኙትን ሰው ሁሉ እንዲገድሉ ትእዛዝ እንደተሰጣቸው ተናግሯል፡፡

ገብረሕይወት በፊትም የሽብርተኛው ትህነግን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ እንደማይቀበለው እና እጁን በሰላም ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ከሰጠ ጉዳት እንደማይደርስበት ስለሚያውቅ “እጄን ሰጠሁ” ነው ያለው፡፡

ገብረሕይወት የትግራይ እናቶች በግድ ወደጦርነት የሚማገዱ ሕጻናት ልጆቻቸውን እጅ እንዲሠጡ እንዲመክሯቸው ነው መልእክት ያስተላለፈው፡፡

ዘጋቢ፡-የማነብርሃን ጌታቸው – (አሚኮ)

Exit mobile version