Site icon ETHIO12.COM

አሸባሪው ሕወሓት የሽብር ድርጊቱን ወደ ጎረቤት አገራት እንዲዛመትና ቀጣናዊ የማድረግ ሥራ ውስጥ ገብቷል

አሸባሪው ሕወሓት የሽብር ድርጊቱን ወደ ጎረቤት አገራት እንዲዛመትና ቀጣናዊ የማድረግ ሥራ ውስጥ መግባቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሠላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ በተመለከተ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ገለጻ አድርጓል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ሕወሃት መንግሥት የወሰደውን የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ውድቅ አድርጎታል።

ይህንንም ተከትሎ በአጎራባች ክልሎች በተለይም በአፋርና በአማራ የሽብር ጥቃት በመክፈት በሁለቱ ክልሎች ከ500 ሺ በላይ ዜጎች ማፈናቀሉንና ንጹሃን ዜጎችን መግደሉን ገልጸዋል።

ጎን ለጎንም ቡድኑ ሰርጎ በገባባቸው የአማራና የአፋር አከባቢዎች ሴቶችን መድፈሩን፣ የመንግሥትና የግለሰብ ንብረቶችን ማውደሙንና ከፍተኛ ምዝበራ መፈጸሙን አስረድተዋል።

በተጨማሪም አሸባሪው ቡድን በአገር ውስጥ አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀ ቡድን ጋር ጥምረት መፈጸሙን አስታውሰው፤ በሽብር ድርጊቱ አገሪቷን ለመበታተን እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ቡድኑ በውክልና በተለያዩ ክልሎች በሚፈጽማቸው የሽብር ጥቃቶች ፤ አሁንም ደግሞ ቀጣናዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በጎረቤት አገራት ውስጥ ብጥብጥ በመፍጠር ችግሩ አከባቢያዊ ቅርጽ እንዲይዝ የማድረግ ሥራ እየሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሸባሪው ሕወሓት የሚያደርገውን የሽብር ሥራ ከማውገዝ መቆጠባቸውን ገልጸው፤ ይህም ትክክል አለመሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሸባሪው የሕወሃት ቡድን የሚፈጽማቸውን የሽብር ተግባሮች ዓለም አቀፉ ማኅረሰብ በጽኑ እንዲያወግዘው ነው ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ ጥሪ ያቀረቡት።

የሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ከሚል በበኩላቸው፤ አሸባሪው ሕወሃት ከትግራይ አልፎ በአጎራባች ክልሎች ላይ በሚያደርሰው ጥቃት ሰብዓዊ ቀውሱን ማባባሱን ገልጸዋል።

ቡድኑ በተደጋጋሚ በሚያደርጋቸው የጠብ አጫሪነት ትንኮሳዎች በትግራይና በሌሎች አካባቢዎች ለሚገኙ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ በትክክል እየደረሰ አለመሆኑን አስረድተዋል።

በተጓዳኝም ቡድኑ በትግራይ ክልል በሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ላይ አደጋ መደቀኑን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ አሸባሩ ቡድኑ በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጽማቸውን እኩይ ተግባራት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሚገባው እያወገዘው አለመሆኑንና ይህም ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል።

አጋር ዓለም አቀፍ ሀገራትም ቡድኑ የሚሰራቸውን እኩይ ተግባራት “በይፋ ወጥተው ማውገዝና መኮነን ይጠበቅባቸውል” ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሚሰራቸውን አዎንታዊ ሥራዎች እውቅና መስጠትም እንደሚገባ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች ጥቃት ሲፈጽም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተገቢውን ትኩረት አለማግኘቱንና ድርጊቱን አለማግዙ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ከረድኤት ተቋማት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው ተቋማቱ ሥራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ መሆኑን ሊፈትሹ ይገባል ብለዋል።

በተለይም ለተሸገሩ ወገኖች የሚቀርቡ ምግቦች አሸባሪው ቡድን እንዴት እየደረሰው እንደሆነ እነዚህ ተቋማት ሊያስረዱና ብዥታዎች ሊያጠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመድረኩ መንግሥት በሦስትም ክልሎች የሚያደርገውን የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎች ከአጋር አካላት ጋር በመሆን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስትሮቹ አረጋግጠዋል።

ENA

Exit mobile version