Site icon ETHIO12.COM

ወደ ጅቡቲ በህገወጥ መንገድ ሊሻገር የነበረ ዶላር ተያዘ

የሽብርተኛው ህወሃት የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የሰጧቸውን ተደጋጋሚ የሰላም ዕድሎች መጠቀም ተስኗቸው እየፈፀሙ ያሉትን ትንኮሳና ወረራ እንደ ሽፋን በመጠቀም አንድ አንድ አካላት ከመሳሪያና ከገንዘብ ዝውውር ጋር በተያያዘ የተለያዩ ህገ ወጥ እንቅስቃሲዎችን ለማድረግ እየሞከሩ ነው፡፡

ይሁንና እነዚህ አካላት የህዝባቸውንና የሀገራቸውን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለመረጋገጥ ለአፍታም አይናቸውን ከማይከድኑት የደህንነትና የፀጥታ አካላት እይታ ውጭ መሆን አልቻሉም፡፡ከእነዚህ አካላት ውስጥ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር እንቅስቃሴ ተጠርጥሮ ትናንት ምሽት ኮምቦልቻ ከተማ ላይ በቁጥጥር ስር የዋለውን ዓሊ መሀመድ አደምን ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡

ዓሊ መሀመድ አደም ኮንቴነሮችን ከጅቡቲ አዲሰ አበባ የሚያመላልስ የከባድ መኪና አሸከርካሪ ነው፡፡ ግለሰቡ ነሃሴ 20/2013 ዓ.ም ማለዳ ላይ ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ ጉዞ ከመጀመሩ በፊት፤ በህገወጥ ጥቅም ከተሳሰረው ከአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ጎራ በማለት 49 ሺህ 300 ዶላር በሚስጥር በመቀበል ወደ ጅቡቲ የሚያደርገውን ጉዞ ይጀምራል፡፡

ዓላማውም ገንዘቡን ወደ ጅቡቲ በማጓጓዝ በጥቁር ገበያው ወይንም Black Market በከፍተኛ ምንዛሬ በመቸብቸብ ትርፍ ማጋበስ ነው፡፡ ይሁንና ግለሰቡ በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ክትትል ሲደረግበት ስለነበር ከሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ከአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ትናንት ከምሽቱ አምስት ሰአት ገደማ አካባቢ ኮምቦልቻ ከተማ ላይ በቁጥጥር ስር መዋሉን የኢትዮጵያ ፕሬስ ርጅት ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪው ዓሊ መሀመድ አደም አድርስልኝ ካለውና አዲስ አበባ ከሚኖረው መተዳዳሪያውን እንዲህ አይነት ህግወጥ የገንዘብ ዝውውር ከደረገው ግለሰብ የገንዘብ ጉርሻ በመቀበልና ተባባሪ በመሆን ጅቡቲ ለሚኖር ሌላ ተቀባይ አካል የአድራሽነት ሚና እንዳለው የመረጃ ምንጮቻችን ያሰረዳሉ፡፡የመረጃ ምንጮቻችን ከስፍራው የተጠርጣሪውን የዓሊ መሀመድ አደምን የወንጀል ድርጊት ያቀረቡልን፤ የሀገርን ህልውና ለማስቀጠል እንዲሁም የዜጎችን ደህንነትና ሰላም ለማረጋገጥ የደህንነትና ፀጥታ አካላት እያደረጉ ያሉት ርብርብ በህዝቡ የተለመደ ትብብርና ተሳትፉ ተጠናክሮ መቀጠሉን ለመግለፅ እንዲሁም የጁንታውንና የተባባሪዎቹን አከርካሪ ለመምታት መላው ህዝብና መንግስት ርብርብ እያደረጉባሉበት በአሁኑ ወቅት በእንደዚህ አይነት ህግወጥ ተግባር መሳተፍ ከሽብርተኝነት ተለይቶ የሚታይ አለመሆኑን ለማሳወቅ ነው፡፡

Exit mobile version