Site icon ETHIO12.COM

በማይጸብሪ ግንባር ጭናና ጫንቃ የገባው የትህነግ ሃይል ተደመሰሰ፤ አማራ ክልል የድሉ ፍጻሜ መቃረቡን አስታወቀ

በማይጸብሪ ግንባር ጭና እና ጫንቅ የገባው አሸባሪው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ሃይል ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን የመከላከያ ሰራዊት አመራር አስታወቁ። የተረፈውና የተበተነው ሃይል እየተለቀመና እየተቃረመ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዳባት በኩል ቆርጦ ለመግባት የሞከረው የአሸባሪው የትህነግ ሃይል ተከቦ በተወሰደበት እርምጃ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበታል። ይህ ሃይል በመከላከያ ሰራዊት፣ በአማራ ልዩ ሀይልና ሚሊሺያ እንዲሁም በኦሮምያ ክልል ሚሊሺያ በጣምራ በተወሰደበት እርምጃ ነው ከፍተኛ ቁሳዊና ሰብዓዊ ኪሳራ የደረሰበት። ትላንት አመሻሹን ጀምሮ በማይጠምሪ ግንባር በጭናና በጫንቅ አካባቢዎች በተወሰደው እርምጃ በአሸባሪ ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት ለኢቲቪ ያስታወቁት የማይጠምሪ ግንባር የሚዲያ አስተባባሪ ኮሎኔል ጥላሁን በቀለ ናቸው።

አሸባሪ ቡድኑ ሙሉ በሙሉ መመታትቱን ያስታወቁት ኮሎኔል ጥላሁን ይህን ሃይል እስከመጨረሻው ለመደምሰስ በግንባሩ የተሰማራው የፀጥታ ሀይል በቅንጅትና በጀግንነት ክንዱን እያሳረፈበት መሆኑንን አመልክተዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ህዝብ አሸባሪ ቡድኑን ለመደምሰስ ከፀጥታ ሀይሉ ጎን በመሆን የሚያደርገውን ተጋድሎ እጅግ የሚደነቅ መሆኑን ያመለከቱት ኮሎኔል ጥላሁን፣ ከሚወርበት የቅጣት በትር አምልጦ የተበተነውን የወንበዴ ሃይል ህዝቡ እየተከተለ እንዲቃርመው አሳስበዋል።

ዘግይቶ በደረሰ መረጃ በአካባቢው ገብቶ የነበረው የህወሃት አሸባሪ ሃይል በሰራዊቱ የተቀናጀ ጥቃት መደምሰሱ ይፋ ሆኗል። በደረሰበት ጥቃት ደንብሮ የተበተነው ሃይል እጅ እየሰጠና እየታደነ መሆኑ ተመልክቷል። የዛሬውን ጨምሮ በሰሞኑ ጥቃት ከፍተኛ ጥቃት ደርሶበታል የተባለው የትህነግ ሃይል አመራሮች ይፋ የሆነ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ አልሰጡም። ይሁን እንጂ የቅርብ ደጋፊዎቻቸው ሳይቀሩ ቅሬታ እያሰሙ ስለመሆኑ ግን እየተደመጠ ነው።

Exit mobile version