ETHIO12.COM

“ ጥይት ብቻ አቅርቡልን፣ አመታቱን፣ አመካከቱን፣ አነካከቱን እኛ እናውቀዋለን…”

ʺየእኔ ባል ከአንቺው ይበልጣል፣
ከጠላት ትከሻ ማርኮ ይመጣል”

በጀግንነት የኖረች፣ ጀግና የወለደች፣ በጀግንነት ሀገር ያስከበረች፣ ታሪክ ቀርጻ ያስቀመጠች፡፡ ሀገር እንዲያስከብር፣ በታሪክ እንዲዘከር ሂድ ተዋደቅ፣ ሀገርህን ከጠላት አላቅቅ ይሉታል፣ አይዞህ በርታ፣ ወደፊት ብቻ ሂድ እያሉ ያበረታቱታል፡፡ ቤቱን፣ ልጆቹንና ምቾቱን ትቶ ከሁሉም የምትቀድመውን፣ ከሁሉም የምትበልጠውን እናት ሀገሩን እንዲያድን፣ ጠላትን በዱር በገደል እንዲያድን ይሸኙታል፡፡

እናት በእናት አትጨክንም፣ የራሷን ደስታ የቤቷን መከታ፣ የልጆቿን አለኝታ ሂድ ዝመት፣ መክት፣ ክተት ጠላትህን አንክት፣ ዓልመህ ተኩስ ለነጻነት፣ ለማንነት፣ ለሉዓላዊነት ይሉታል፡፡ የኢትዮጵያ እናቶች ማዝመት፣ መዝመት ይችሉበታልና፡፡

ተዋበች ታጠቅ እንዳለችው፣ በሄደበት እንደተከተለችውና ሀገር አንድ እንዲያደርግ እንደገፋፋችው፣ ከጎኑ እንዳልተለየችው፣ እንዳበረታችው፣ ጣይቱ የጣልያንን መልእክተኛ ለጦርነት አልፈራም ብላ ቶሎ እንዲመጣና ክንዷን እንዲቀምስ እንደነገረችው፣ የጦርነቱን ስልት እንደቀመረችው፣ ስንቅና ትጥቁን እንዳስከተለችው፣ ሠራዊቱን እንዳበረታታችው በጀግንነት ተዋግቶ ድል አመጣ፡፡ አበረታተውም ደማቅ ታሪክ አኩሪ ገድል አስቀመጡ፡፡

ጀግኖች ዛሬም ቀጥለዋል፣ ጠላትን መውጫ መግቢያ አሳጥተዋል፣ ትህነግ በአማራ ላይ ጦርነት ከከፈተ ሰነባብቷል፣ ሺዎችን አፈናቅሏል፣ ሀብትና ንብረታቸውን አውድሟል፣ የእምነት ተቋማትን አፍርሷል፣ ንጹሃንን ገድሏል፡፡ ይህ ግፍ ከተፈፀመባቸው አካባቢዎች መካከል የሰሜን ወሎ ዞን አካባቢ አንደኛው ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ጀግኖች ታዲያ ወራሪውና አሸባሪውን ቡድን በየቦታው እያስቀሩት ነው፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠሩ ያሉት የአማራ ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ደሰላኝ በላይ በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ስላለው ጉዳይ ነግረውናል፡፡ ኀላፊው እንዳሉት ሐብሩ ወረዳ በሶዶማ፣ ድሬ ሮቃ እና የራያ ቆቦ ወረዳ ቆላማ አካባቢዎች ፀረ ትህነግ ትግል ላይ ናቸው፡፡ በሶዶማ በኩል በላይ የሚመጣውና በታች በአፋር አለሌሱላ የሚመጣውን ጠላት በየጥሻው እያስቀሩ እየደቆሱት ነው፡፡

ትህነግ ሬሳ በሬሳ ሆኗል፡፡ ጦርነትን ያደጉበት እና የኖሩበት ጀግኖቹ አላሰናዝር ብለዋል፡፡ በከባድ መሳሪያ አካባቢውን ሊያስለቅቅ ሙከራ ቢያደርግም ንቅንቅ አላደርገው ይላሉ፣ በሽምግልና እባካችሁን መንገድ ስጡኝ ከእናንተ ጋር ጠብ የለኝም ማለት ያዘ፤ ጀግኖቹ ግን ሀገርና ሕዝብ የሚያጠፋን ከመንገድ እናስቀራለን እንጂ ለአንተ መንገድ አንከፍትም፣ ቀያችን የምትረግጣት፣ አልፈህም የምትሄደው ካለቅን ብቻ ነው አሉት፡፡ በፊት በኋላ በጥይት ጅራፍ እየገረፉ መመለሻም መላወሻም አሳጡት፡፡ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው ባደጉበት የጦር ስልት ቆሉት፡፡

ከጀግና ሠፈር ዘው ብሎ ከገቡ በኋላ መውጫ የለምና ሁለት ምርጫ ብቻ ቀርቦለታል፣ እንደለመደው መሞት ወይንም እጅ መስጠት ብቻ፡፡ ጀግኖቹ አሁን ጥይት ብቻ አቅርቡልን፣ አመታቱን፣ አመካከቱን፣ አነካከቱን እኛ እናውቀዋለን እያሉ ነው፡፡ ጠላትን በደፈጣ፣ በቆረጣ፣ በፊት ለፊት ውጊያ እየቆሉ፣ በዱር በገደል እያንከባለሉ፣ ግንባር ግንባሩን እያሉ፣ የመጣበትን ቀን እንዲወቅስ፣ ላኪዎችን እንዲከስ፣ ሬሳው እንደ ቅጠል በየመንገዱ እንዲልከሰከስ እያደረጉት ነው፡፡

ማን እነርሱን ችሎ ይጋፋል፣ ማንስ ያሸንፋልና፡፡ ቢሻቸው ይገሉታል፣ ነብሴን አትርፉልኝ ያላቸውን ይማርኩታል፣ ትጥቁን ይቀሙታል፣ የጀግንነትን ፊደል ያስተምሩታል፣ ያስጠኑታል፡፡ አንድ ነገር እርግጠኞች ናቸው፣ ጠላት እንደማያሸንፋቸው፣ ችሎ እንደማይደፍራቸው፡፡ ጀግኖቹ የሚማርኩትን ያስታጥቁታል፣ አስታጥቀው ይዋጉበታል፣ በራሱ ጥይት በራሱ ጠመንጃ ጠላትን ይገርፉታል፡፡

ኀላፊው ሲነግሩን አካባቢው ባለፈው የምርት ዘመን በአንበጣ መንጋ ተጎድቷል፣ ምርት አላገኙም፣ ነገር ግን እርዳታ ከምናቀርብላቸው ይልቅ ጥይት አምጡልን ነው የሚሉት፡፡ ማኅበረሰቡ የጠላትን እንቅስቃሴና ማንነት በደንብ እየተረዳ እየሄደ እንደሆነ የነገሩን ኀላፊው እየተደራጄ፣ ወደ ወደ መረረ ስሜት ገብቷልም ነው ያሉን፡፡ ወጣቱ ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፎ መዋጋት፣ ስንቅ ማቀበል፣ ማስተባበር ላይ ነው፡፡

ራያ ቆቦ አካባቢ ጠላት እየተንጠባጠበ ትንሽ ኀይል ብቻ ነው ያለው፣ ወርቄ ያያ፣ ወርቄ አጋምሳ፣ ድቢ፣ አዲስ ዓለም፣ አቧሪ፣ ወደየ፣ ወሬቄርቱ በራሳቸው ተደራጅተው እዝ መስርተው፣ ጠላትን እያጣደፉት ነው፣ ጀግኖቹ በአዝማች እየተመሩ፣ ጠፍቶ የሚሄድን፣ ስንቅ የሚያቀበልን፣ ተበታትኖ የሚጓዝን ጠላት ትጥቁን እየነጠቁ፣ ጉሮሮውን እያነቁ እስከ ወዲያኛው እየሸኙት ነው፡፡

ባለ ሽርጦቹ ጀግኖች የጠላትን ተሸከርካሪ እየመቱ፣ ከጥቅም ውጭ እያደረጉ ጠላትን ወደፊትም ወደኋላም እንዳይል ሰንገው ይዘውታል፣ ኀላፊው እንደነገሩን በዚያ አካባቢ ያሉ ጀግኖች ወደ ዘመቻ ሲሄዱ ባለቤቶቻቸው ልጆችህን ትተህ፣ ቤትህን ዘግተህ አትሂድ አይሉም፣ ይልቅ የአንደኛው ጀግና ባለቤት ከሌላኛው ባለቤት ጋር ሆነው ስለ ባለቤቶቻቸው ጀግንነት ነው የሚያወጉት፣ የእኔ ባለቤት ከአንቺው ይበልጣል፣ ማርኮ ይመጣል ነው የሚሉት፡፡ የእኔ ባለቤት ይሄን መሳሪያ ይዟል፣ ይህንንም ማርኳል ይባባላሉ፣ ይህ ባሕላቸው ነው ከጥንት ጀምሮ የቆየ ነው፣ ጦርነት የተለመደ ነው ብለውናል፡፡ በዚያ በኩል ወደ ትግራይ ተመልሶ የሚገባ የለም፣ ሁሉም መንገድ ላይ ይቀራል፡፡

ጠላት ዓላማው አማራን ማዋረድ፣ ኢትዮጵያን መበታተንና መዝረፍ ነው ያሉት ኀላፊው መዝረፍ ያደገበትና የኖረበት ነው፣ መላው የአማራ ሕዝብ እንደ ጋይንት፣ እንደ ሰሜን ወሎ ቆላማ ቦታዎች ሁሉ ጠላትን እየመታ በገባበት እንዲቀር ማድረግ አለበት ነው ያሉት፡፡

የራያ ፋኖዎች አስደናቂ ጀብዱ እየፈጸሙ ነው፣ ጠላትን እየደመሰሱ ነው፣ ብዙ መሳሪያ ማርከዋል፣ ጠላትን አውድመዋል፣ አሁንም ውጊያ ላይ ናቸው፣ የራያ ፋኖዎች የማንም የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎች አይደሉም፣ ሕዝባዊ ናቸው፣ በአደረጃጀታቸው ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊ የሆነ የፋኖ መሪ መሆን አይችልም የሚል ሕግ አላቸው፣ አባል ሆኖ መዋጋት ግን እንዲችል ፈቅደውለታልም ብለውናል፡፡ አብረናቸው እንዋጋለን፣ የትጥቅና፣ የስንቅ ጥያቄያቸውን እየመለስን ነው፣ መስዋዕት እየከፈሉ ነው፣ ከእነዚህ ጀግኖች ጋር ሁሉም ሊሰለፍ ይገባል ብለዋል፡፡

ጠላትን ደምስሶ የመጨረሻውን ደስታ ለመደሰት፣ ነጻነትን ለማወጅ፣ ከታላቅ ታሪክ ላይ ሌላ ታላቅ ታሪክ ለመጨመር አሁን ሁሉም መነሳት፣ መዝመት፣ መምታት አለበት፡፡ ሴቶችም ወንዶችም ጀግኖች ከሆኑበት ሕዝብ አብራክ ወጥተሃልና በጀግንነታቸው ኩራ፣ በእነርሱ ጀግንነት ልክ እንድትቀመጥ አንተም ጀግንነትን ሥራ፡፡ ጠላትህን ቅበር፣ ወንዝህን፣ ቀዬህን አድባርክን አስከብር፡፡

በታርቆ ክንዴ – (አሚኮ)

Exit mobile version