Site icon ETHIO12.COM

ተጨማሪ ከሱዳን የተነሳ የትህነግ ሃይል አሰበው ሳይደርስ ተመታ

ከተለያዩ ወገኖች እየተሰማ ያለው መረጃ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር በተለያዩ ግንባሮች ባሰበው መጠን የተሳካለት ባለመሆኑ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ፊቱን ወደ ሱዳን ማዞሩን ነው። ለዚህም ይመስላል ያለፈው ሙከራዎቹ ሳይጠቀሱ በዚህ ሶስት ቀን ብቻ ከአራት ጊዜ በላይ በሱዳን በኩል ሰብሮ ለመግባት ጥቃት የሰነዘረው። በግንባሩ ያሉ የመከላከያ አመራሮችም እያሉት ያለው ይህንኑ ነው።

“ በሱዳን በኩል የተዘጋውን የመገናኛ ኮሪዶር በሃይል ደምሥሰን እናስከፍታለን። ይህን የማድረግ ሙሉ አቅምና ብቃት አለን” ሲሉ ለቢቢሲ ሲናገሩ የቀድሞው ሌተናል ጀነራል ጻድቃን፣ እቅዳቸው ባስቸኳይ ተግባራዊ እንደሚሆንም ጥርጥር እንደሌላቸው ተናግረው ነበር። 

በጀነራሉ መግለጫ ላይ ተጨማሪ በማድረግ የትህነግ አፈ ቃላጤ አቶ ጌታቸው ረዳም በተደጋጋሚ ይህንኑ “የማይቀር” የሚሉትን ድል ቀን እየቆረጡ  ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲያስተላለፉ እንደነበር አይዘነጋም። 

በዚህ መካከል ፋይናንሻል ታይም  አቶ ጌታቸውን ጠቅሶ ሰላሳ ሺህ ታማኝ የትህነግ ወታደሮች በሱዳን በኩል ከትህነግ ጋር ለመቀላቀል እየተጠባበቁ እንደሆነ ይፋ አድርጎ ነበር። ሚዲያው አፍታም ሳይቆይ “ወታደሮች” ያላቸውን ” ያልታጠቁ” ሲል ቀየረው። ከታች የቲውተር መረጃውን ያንብቡ።

የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ሃይል ኮማንድ ፖስት የኦፕሬሽን ዘርፍ አሰተባባሪ ኮ/ል ሰይፈ ኢንጊ እንደሚሉት ትህነግ በሁሉም ግንባር አልሆን ስላለው ፊቱን ወደ ሰሜን በማዞር ሱዳን ባዘጋጀው ሃይል አማካይነት ደጋፊዎቹን ለማስደሰትና የህዳሴውን ግድብ ስራ ለማስተጓጎል አቅዶ ተደጋጋሚ ጥቃት ከፍቷል።

ይህንኑ ዓላማውን ለማሳካት በአልምሃል በኩል ሰርጎ ለመግባት የሞከረውና ኮሎኔል ” ቅጥረኛ” ያሉት የትህነግ ሃይል፣ በጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ክንድ ተደምስሷል። በተወሰደው በዚህ እርምጃ ሀምሳ የሽብር መልዕክተኞች ሲደመሰሱ ከሰባ በላይ ቁስለኛ መሆናቸውን ኮሎኔሉ ለአማራ ሚዲያ ኤጀንሲ አመልክተዋል። አክለውም ቅጥረኛው የተለያዩ ፀረ ሰው እና ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጂዎችን ለማጥመድ የሞከረ ቢሆንም መቋቋም ተስኖት ተበታትኗል ሲሉ ተናግረዋል። 

ቡድኑ አሳቻ ስዓት ጠብቆ አካባቢውን ለማተራመስ ቢቀሳቀስም፣የጠላትን ኮቴ ከመነሻው በንቃት ሲከታተሉ የነበሩት የመከላከያ ሰራዊት የተለያዩ ክፍሎች በቅንጅትና በመናበብ እርምጃ  እንደወሰዱበት ከኮሎኔሉ አንደበት ለመረዳት ተችሏል። የጠላት ሃይል የቻለውን ያክል መከላከል ቢሞክርም በጀግናው የመከላከያ ሰራዊት የበላይነት ተወስዶበት ፣የተረፈው ሃይል አግሬ አውጪኝ በማለት መፈርጠጥን ብቻ አማረራጭ ማድረጉን ተናግረዋል። 

የጥፋት ሃይሉ ሲጠቀምባቸው እና ለእኩይ ስራው ሲያዘጋጃቸው የነበሩ ቀላል እና ከባድ የቡድን መሳሪያዎች ፣ ፈንጂዎች የወደሙ ሲሆን የተቀሩት በጀግናው መከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ገብተዋል። 

“አሸባሪው የሕወሃት ቡድን በግንባር ድል አልቀና ሲለው አብዛኝው ጦር ወደ ሰሜኑ ክፍል አቅንቷል በሚል ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ተቀናጅቶ የህዳሴ ግድባችንን ስራ ለማስተጓጎል ለማጥቃት ቢሞክርም አልተሳካለትም” ብለዋል።

በአሁኑ ስዓት በአካባቢው ጀግናው የመከላከያ ሃይላችን ፣ እግረኛና ሜካናይዝድ ክፍለጦሮች እንዲሁም የክልል ልዩ ሐይሎች አስፈላጊውን ዝግጁነት በማረጋገጥ ግዳጃቸውን እየፈፀሙ እንደሚገኙ ኮ/ል ሰይፈ አረጋግጠዋል። 

Exit mobile version