Site icon ETHIO12.COM

በኦሮሚያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት አመቱ ለአንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል

የኦሮሚያ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ በ2013 አም በጀት አመት ለአንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን አስታወቀ። ይህ ይተገለጸው ቢሮው የ2013 በጀት አመት አፈፃጸም እና 2014 እቅድ ላይ በአዳማ ገልማ አባገዳ አዳራሽ ውይይት ባድረገበት ወቅት ነው።

የኦሮሚያ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ ቦጋለ ፈለቀ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፣ በ2013 በጀት ዓመት የኦሮሚያ ክልል የኢኮኖሚ አቅም መፍጥር የሚችለውን የስራ እድል አሟጦ በመጠቀም ረገድ ልዩ እቅድ በማውጣት ስራ አጦችን ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።በዓመቱም ለአንድ ሚሊየን ሁለት መቶ ሃምሳ ሺ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ለአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል።

ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ተማሪዎች ድርሻም ቁጥሩ ከፍተኛ መሆኑንና ከ 79 ሺ በላይ የሚሆኑት ተመራቂዎች መሆናቸው አመልክተዋል፡፡ በስራ እድል ፈጠራው የሴቶች ድርሻ 33 በመቶ በመሆኑ፣ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሻሻል አለበትም ብለዋል፡፡

በየደረጃው ያሉ የስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤቶች በእኩል አቅም የመንቀሳቀስና ተቀራርቦ የመስራት ውስንነት ፣የብድር አቅርቦት ውስንነት፣የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ማነስ፣ከልልሉ አቅም አማጦ በመጠቀም ረገድ ተመጣጣኝ ስራ አለመስራት እና በአስፈጻሚ አካላት ዘንድ የአፈፃፀም ልዩነቶች በበጀት አመቱ ጎልተው የተስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ መሰል ችግሮችን ለማስወገድም በቀጣይ አመት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

ባለፈው አመት አፈጻጸም መሰረት በማድረግም በ2014 በጀት አመት ለአንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዚያዊ የስራ እድል ለመፍጠር፣ ዘጠኝ ቢሊየን ብር ለመቆጠብ፣ የስራ ፈጠራው የፆታ ምጣኔን ለወንድም ሆነ ለሴት 50 በመቶ እኩል ለማድረግ ታቅዳል ብለዋል፡፡

በታምራት ተስፋዬ (አዳማ)

Ethio12 የዩቲዩብ ቻናላችንን ላይክና ሰብስክራይብ እንዲያደረጉ እናበረታታለን።

Exit mobile version