Site icon ETHIO12.COM

“አርባ ዘጠኝ አስከሬን ቀበርኩ” – በጭና ሟቾች ከ200 በላይ ሆኑ፣ የታፈኑ አሉ

አቶ ጀምበር ብርሌ የሰጡት ምስክርነት ነው። አቶ ጀምበር ካድሬ ወይም ሹመኛ አይደሉም። ሰው ብቻ ናቸው። አቶ ጀምበርንም ሆነ አጎቶቹን ያጣውን ለጋ ጎረምሳ ካድሬ ቀርቶ ክንፍ የቀጠለ ጻድቅ ቢመጣም ሊያስተባብለው አይችልም። ” ለሁሉም በልቤ አነባለሁ። ለሁሉም ማቅ እለብሳለሁ። ከማን ጋር አለሳለሁ …” ሲሉ ልብን ይነካሉ? በሌላ በኩል ትህነግ እያስቀመጠ ያለው ሌጋሲ መጨረሻው ምን እንደሚሆን ማሰብ ህይወትን ያጨልማል።

እኚህ አባት ስራቸው እየተገታተረ፣ ሃዘን ባከስለው አንጀታቸው ” አርባ ዘጠኙን ቀበርኩ” አሉ። አርባዘጠኙ የተሳሰሩ ዘመዳሞችና በጋብቻና በተመሳሳይ ማህበራዊ ወጎች የተጋመዱ ቅርባቸው እንደሆኑ አስረዱ። አንድ መቃብር ላይ ስድስት፣ አምስት፣ አራት አነባብረው ቀበሩ። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም እንዳሉት ከመቶ በላይ ወገኖች ተሰውረዋል። የገቡበት አይታውቅም።

አምስት ቀን የፈጀ ጦርነት ከተካሄደ በሁዋላ ነሃሴ 29ና 30 የወገን ጦርን መቋቋም ያቃተው ትህነግ በሬ፣ አህያ፣ አላም፣ ድመት፣ ውሻ ሳይቀር ገደለ። ከአንድ ቤት ስድስት ሰዎችን በር ዘግቶ ረሸነ። በዚዲዮው ላይ ምስክረነት የሰጡ እንደሚሉት የቻሉ ሮጠው እንዳያመልጡ በር እየዘጉ ነበር የረሸኑት።

አንድ ታዳጊ በፊልሙ ላይ እንዳለው መብላት ያልቻሉትን እህል አውድመውታል። መጪው ጊዜም በህይወት ለተረፉ አስቸጋሪ እንዲሆን አድርገው ነው የሸሹት። ሰሞኑንን እየወጡ ያሉ መረጃዎችና የፊልም ማስረጃዎች የዕርቅ ጉዳይ ከቶውንም እንዳይታሰብ የሚያደርግ እንደሚሆን፣ ከዛም በላይ ከትህነግ ጋር ንግግር ሊኖር እንደማይችል ሆድ የባሳቸው እያስታወቁ ነው።

Exit mobile version