Site icon ETHIO12.COM

የመረጃና ደህንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ልዩ የሪፐብሊካን ጋርድ አባላትን በከፍተኛ ደረጃ አስተምሮ አስመረቀ

በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ስር የሚገኘው ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከሪፐብሊካን ጋርድ የተመለመሉ በቪአይፒ እና በቁልፍ መሰረተ ልማት ጥበቃ የሰለጠኑ መኮንኖችን አስመርቋል፡፡ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የሪፐብሊካን ጋርድ አባላት ትልቅ ሃላፊነትና እምነት የተጣለባቸው ሲሆን፤ የሀገርን ብሔራዊ ደህንነት በማረጋገጥ ረገድም ከፍተኛ ሚና ሲያበረክቱ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ 

በተለይ ከሀገራዊ ለውጡ ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ ፈተናዎችን በከፍተኛ ወኔና ትዕግስት በመፍታት ያበረከቱት አስተዋጽኦ አስቸጋሪ ጊዜዎችን ለማለፍ እንዳስቻለ ያስታወሱት አቶ ተመስገን፤በቀጣይ ተልዕኳቸውን በብቃትና ጥብቅ በሆነ የስራ ዲሲፒሊኒ ለመወጣት የሚስችላቸውን ስልጠና ከዩኒቪርሲቲ ኮሌጁ መቅሰማቸውን አመልክተዋል፡፡ 

አቶ ተመስገን የሪፐብሊካን ጋርድ አባላቱ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥርላቸውን ስልጠና እንዲያገኙ ላስቻሉት ለዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ አካለት ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሪፐብሊካን ጋርድ ምክትል አዛዥ ብ/ጀነራል አብድሮ ከድር፤የሪፐብሊካን ጋርድ አባላት በርካታ ሀገራዊ ግዳጆችን እየተወጡ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

አሁንም አሸባሪው ህወሓት በተለያዩ አቅጣጫዎች የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ከሌሎች ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ጀብዱ እየፈጸሙ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹በብሔራዊ የመረጃና ደህንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የተሰጠው ስልጠና ሀገራችን ከእኛ የምትጠብቀውን ግዳጅ በላቀ ደረጃ ለመፈጸም እገዛ ያደርጋል›› ያሉት ብ/ጀነራል አብድሮ፤ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ አመራሮች ስልጠናው ከውጥኑ ጀምሮ እስከ ፍጻሜው የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ እገዛ በማድረጋቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ 

ከልጠናውም የሪፐብሊካን ጋርድ አባላቱ ለተሰጣቸው ስምሪት አጋዥ የሚሆን በጣም ጠቃሚ ግብዓት መገኘቱን መስክረዋል፡፡ የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ካሳ በበኩላቸው፤የሪፐብሊካን ጋርድ አባላትከተሰጣቸው ሀገራዊ ተልዕኮ አንጻር ውጤታማ ስምሪት እንዲያደርጉ የሚያስችላቸው ስልጠና እንደተሰጣቸው አመልክተዋል፡፡ 

የቪአይፒ እና የቁልፍ መሰረተ ልማት ጥበቃ የዘመናችን የብሔራዊ ደህንነት ስምሪት ወሳኝ አካል ናቸው ያሉት የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዚዳንት፤ የሪፐብሊካን ጋርድ አባላቱ በዚህ ረገድ አቅማቸውንና ክህሎታቸውን የሚያሳድግ የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና እንደወሰዱ መግለጻቸውን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ያደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡


ይህን ቪዲዮ ይመልከቱ

Exit mobile version