ETHIO12.COM

ዛሪማና አካባቢው «በወገን ሀይል» ቁጥጥር ስር ሆነ

በማይጠብሪ ግንባር በዛሪማ ድብባህር ሊማሊሞ ደባርቅን ለመቁረጥ ውጊያ የከፈተው የሽብርተኛውን ጀሌ በመደምሰስ አካባቢው ከሽብርተኛው ነፃ ማድረግ መቻሉን በግንባሩ የሚገኙ የወገን ጦር ከፍተኛ አመራር አስታወቀዋል ።

በዳባት ውቅን አቅጣጫ የደረሰበትን ሽንፈት ለማካካስና ደባርቅን ተቆጣጥሮ ወደ ጎንደር ለመገስገስ ያለመው የሽብርተኛው ቡድን በብናሜዳ ፣ ቦዛ ፣ ጭና የነበረውን የቀኙን ክንፍ የውጊያ አቅጣጫ ለማዛባት ቢጥርም መደምሰሱን የወገን ጦር መሪው ገልፀዋል።

የወገንን ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመግታት የዛሪማ ድልድይን በፈንጂ ለማፍረስ ብዙ ቢጥርም በደረሰበት ጥቃት መሽመድመዱን የተናገሩት ከፍተኛ አመራሩ ፣ ጠላት መልሶ እንዳይቋቋም የሚያደርግ ምት በማሳረፍ ዛሪማና አካባቢው በማይጠብሪ ግንባር በተሰለፈው የመከላከያ ሰራዊታችንና የወገን የፀጥታ ሀይሎች ቁጥጥር ስር እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ጠላትን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ለተገኘው ድል በማይጠብሪ ግንባር የተሰለፈው የወገን ሀይል ጥምረት የላቀ እንደነበር የተናገሩት የጦር መሪው ፣ አሁንም ዙሪያ መለስ የውጊያ ቁመናን በማሟላት ለቀጣይ ግዳጅ በሙሉ አቋም ላይ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።

የሽብር ቡድኑ በዛሪማ ከተማ የሚገኙ የመንግስት ተቋማትን ከመዝረፍና ከማውደም ባለፈ የህዝቡን ገንዘብ ፣ ንብረት ፣ እህልና እንስሳት በመዝረፍ አርዶ በልቷል። አሁን ላይ ማህበረሰቡ ወደ መደበኛ ኑሮው በመመለስ ላይ መሆኑን አክለዋል።

መላክ በቃሉ (ከግዳጅ ቀጣና) ENDF Fb
ፎቶግራፍ መላክ በቃሉ

የሽብርተኛው ግፍና በደል በዛሪማ

ዘራፊውና ተስፋፊው የህወሓት ቡድን ሀይሎች በዛሪማና አካባቢው ሰርገው በገቡባቸው ቀናት የተለያዩ ግፍና በደሎች መፈፀሙን የአይን እማኞችና ሰለባ የሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በዛሪማ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ የተከራየውን ንብረትነቱ የኪዳነምህረት ገዳም የሆነ ህንፃ የሚቆጣጠሩት አባ ገብረማርያም ሳሙኤል እንደተናገሩት ፣ ወመኔዎቹ ወያኔዎች እኔን እንኳ በአባትነት ሳያከብሩኝ ገፍትረው ጥለው የባንኩን ኤቲኤም ማሽን ሰብረው መዝረፋቸውንና ወደውስጥ በመግባትም የፈለጉትን አድርገው መውጣታቸውን መስክረዋል።

በዛሪማ ከተማ ተወልደው ያደጉት አቶ ባየ አትክልት እና አቶ ዳግማዊ ገነነውም የሽብር ቡድኑ ዘራፊዎች የሞቀ ቤታቸውን በማዘጋት ሱቃቸውንና የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሳቸውን እንደዘረፏቸው ተናግረዋል።

ቋንቋና ዘርን እየለዩ አሰቃይተውናል ያሉት አቶ ባየ እና አቶ ዳግማዊ መሳሪያ ተደግኖባቸው እጃቸውን ወደላይ አሰንዲያነሱ ተደርገው ከኪሳቸው የነበሩ ብሮችና ወዛቸው ያለባቸው ልብሶቻቸው ጭምር በብርበራ እንደተወሰዱባቸው በምሬት አስረድተዋል።

ህወሃቶች በዘር ፣ በብሄርና በሀይማኖት እየለዩ መግደል ፣ መዝረፍና ማሰቃየት መለያቸው እንደሆነ የሚያስረዱት ደግሞ ከዛሪማ መስጊድ ሲወጡ ያገኘናቸው መሃመድ ሱለይአደም ሲሆኑ ፣ ነውረኞቹ የወያኔ ሽፍቶች የእምነቱ ሰዎች ሶላት ላይ በነበሩበት ሰዓት ወደ መስጊዱ በመግባት የሰጋጆቹን ኪስ በመፈተሽ የነበራቸውን ገንዘብ ሁሉ መቀማታቸውንና አውልቀውት የነበረውን ጫማ ሳይቀር መውሰዳቸውን በእዝነት ገልፀውልናል።

መከላከያ ሰራዊቱ ፣ የአማራ ልዩ ሀይል ፣ ሚሊሻና ፋኖ ዛሪማና አካባቢውን ከተቆጣጠረ በኋላ ከሰቀቀን ወጥተው እንቅልፍ መተኛት መቻላቸውን ከምስጋና ጋር ይናገራሉ።

መላክ በቃሉ (ከግዳጅ ቀጣና)
ፎቶግራፍ መላክ በቃሉ

Exit mobile version