Site icon ETHIO12.COM

ህወሓት ታጣቂዎች በወረባቦ ንፁሃንን በግፍ ገድለው አስከሬናቸው በአውሬ እንዲበላ ማድረጋቸውን የሟቾች ቤተሰቦች ተናገሩ

የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች በወረባቦ ወረዳ ከ24 በላይ ንፁሃንን በግፍ ገድለው አስከሬናቸው በአውሬ እንዲበላ ማድረጋቸውን የሟቾች ቤተሰቦች ተናገሩ

የአሸባሪው የህወሓት ታጣቂ ኃይሎች ለጥቂት ቀናት በቆዩባቸው የወረባቦ ወረዳ አካባቢዎች ከ24 በላይ ንፁሀንን በግፍ ገድለው አስከሬናቸው በአውሬ እንዲበላ ማድረጋቸውን የሟቾች ቤተሰቦች ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ ሰርጎ በመግባት ለጥቂት ቀናት በቆየባቸው የወረባቦ ወረዳ 18 ቀበሌ ብቻ ከ14 ሰዎች በላይ ስለ ፖለቲካ ምንም ያማያወቁ ንፁሃን አርሶ አደሮችን በመግደል የግፍ ድርጊት መፈፀሙን የተጎጂ ቤተሰቦቹ ገልጸዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ አርሶ አደሮችን የገደለው ሰብላቸውን እየተንከባከቡ ባሉበት እያባረረ ሲሆን፣ አቅም ያላቸው ሴቶች ልጆቻቸውን በመያዝ ህይወታቸውን ለማትረፍ ሸሽተዋል፤መሸሽ ያልቻሉ አቅመ ደካማዎች ደግሞ በግፍ ገድሏቸዋል ብሏል ነዋሪዎቹ፡፡

አስክሬናቸውም እንዳይቀበር አድርጎ በአውሬ እንዲበላ ማድረጉን የሟቾች ቤተሰቦች ተናግረዋል፡፡

የወረባቦ ወረዳ 18 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ጠይባ መሀመድ ለ22 ዓመታት በትዳር አብረው የቆዩትንና የአራት ልጆች አባት የሆነውን ባለቤታውን በሽብር ቡድኑ እንደተገደለባቸው ተናግረዋል፤ ቡድኑ አስክሬኑን አናስቀብረም ብለው በአውሬ እንዲበላ አድርጓልም ነው ያሉት፡፡

ሌላኛዋ የወረባቦ ወረዳ 18 ቀበሌ ነዋሪ ወ/ሮ አይሻ ሰኢድ አሸባሪ ቡድኑ የተኩስ እርምታ ሲከፍትባቸው መኖሪያቸውን ለቀው የሸሹ ቢሆንም መሸሽ ያልቻሉ አቅመ ደካሞችን ጨምምሮ የ60 ዓመት ወላጅ እናታቸው በሽብር ቡድኑ ተገድለዋል፤ ሰርጎ ገቦቹ አስክሬናቸው በአውሬ እንዲበላ አድርገዋልም ብለዋል፡፡

እንደ ኢቢሲ ዘገባ፤ በደቡብ ወሎ የወረባቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኻሊድ መሀመድ በወረዳው በ3 ቀበሌዎች 24 የሚሆኑ ህፃናትን ወጣቶችንና አቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን አሸባሪ ቡድኑ በግፍ ገድሏል ብለዋል፡፡

የአርሶ አደሮችን ቤት ንብረት ዘርፎ ይዞ ሄዷል፤እንሰሳታቸውን የተወሰኑትን አርዶ በመብላት ቀሪውን በጥይት ተኩሶ በመግደል ለችግር እንዲጋላጡ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡ መቀየሪያ ልብሳቸውንም ጠራርጎ ይዞባቸው መሄዱንም ነው የገለፁት፡፡

የትዳር አጋሮቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው በሽብር ቡድኑ የተገደሉባቸው ንብረታቸውን የተዘረፈባቸው ሰዎች አሁን ላይ ለችግር በመዳረጋቸውም ህይወታቸውን ለመታደግ አስቸኳይ የወገን ደጋፍ እንደሚፈልጉ ዋና አስተዳሪው ተናግረዋል፡፡ (ኢ.ፕ.ድ)

Exit mobile version