Site icon ETHIO12.COM

ያሞጠሞጠ እባጭ – “ጥርስ ነቀላ መጣሁ”

“ስንት ዓመትህ ነው” ስለው ” 15″ አለኝ። “እንዴት ወታደር ሆንክ?” እየሳቀ / ፈገግ ብሎ ” ማን ያውቃል” አለኝ። ንግግሩ ግራ ገባኝና ” ማለቴ እንዴት ወታደር ሆንክ?” አሁንም ደገመና ” ማን ያውቃል። ሁሉም ወታደር ሁን ሲባል ይሆናል፤ እምቢ ማለት አይቻልም….” እንዴት እንደሚመለመሉ ስለሚያውቅ ጥያቄውን ቀየረና ” እንዴት መጣህ እዚህ ድረስ ” ድንገት ያመለጠው መስሎኝ በመገረም የሰማሁትን መልስ መለሰልኝ። ” ጥርስ ላወቅል ነው! ጥርስ እናወልቃለን” አለ። ከዛ በሁዋላ ምክር ለግሼው ሄድኩ። አሁን የት እንዳለ መረጃ የለኝም።

ዛሬ የአገር መከላከያ ” በቃኝ” የሚል የመጨረሻ ጥሪ አስተላልፏል። ጥሪው የተላለፈው ለትግራይ ወታቶችና ሚሊሻዎች ነው። ” አትማገዱ፣ በሰላም ወደ ቤታችሁ ተመልሱ፤ ቤተሰብ ይጠብቃችኋል”የሚል ምክር አዘል ነው ጥሪው። ጥሪውን አልቀበል ላሉ ምን መልስ እንዳለው መግለጫው ያለው ነገር የለም። ያው ” በጎደለ ሙላ” ወይም ካለፈው ጥሪ በሁዋላ ምን እንደሆነ እንደታየው ለማለት ነው።

ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ወገን የራሳቸው ያልሆነውንና “ኑልን” ብሎ ያልጋበዛቸውን ሕዝብ ወረው ስለያዙበትና ሕዝቡ የሚገለገልበትን መሰረተ ልማት ለምን እንደሚዘርፉና እንደሚያወድሙበት ይህ እስከታተመ ድረስ በግልጽ የተነገረ ነገር የለም። ሰሞኑንን ነጻ ወጡ በተባሉባቸው ወረዳና መንደሮች በፊልም ተደግፎ የቀረበው እውነት እንደሚያስረዳው እጅግ የከፋ ግፍ ስለመፈጸሙ መከራከር አይቻልም። ትህነግ ” በገለልተኛ አካል ይጣራ” ቢልም የጋሊኮማ፣ የጭና፣ የደብረ ዘቢጥ … አርሶ አደሮች ምስክርነትን የሚቀለብስ እውነት እካድሬ ምላስ ላይ ስለመገኘቱ የዚህ ሪፖርት ጸሃፊ እርግጠኛ አይደለም።

የኢትዮጵያን ድንበር ትግራይ ሆኖ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ሲጠብቅ በኖረው የመከላከያ ሰራዊት ላይ በገሃድ ክህደት፣ አገር ላይ ደግሞ የሃብት ዘረፋ ከተከናወነ በሁዋላ፣ የህግ ማስከበር በተሰኘው ዘመቻ ከሰው ልጆች መብት ጋር በተያያዘ ጥፋት መፈጸሙ ቢጋነንም የሚካድ አይደለም። ” ማን አደረገው?” የሚለውም ጉዳይ በርካታ ጥያቄ ያለበትና በስፍራው የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ሳይቀሩ ሌላ ምስክርነት እየሰጡበት በመሆኑ ጊዜና ወቅት የሚጠብቁ በርካታ ያልጠሩ ጉዳዮች አሉ።

ላለፉት ሁለት ወራት በአማራና አፋር የተፈጸመው ግፍ ግን ታልሞና ” ሂሳብ እናወራርዳለን ” የሚል መሪ ቃል ወጥቶለት የተፈጸመ ለመሆኑ ዝርፊያው፣ ከዝርፊያው በሁዋላ ማውደሙ፣ እንዲወድም ሲደረግ ደግሞ ድመት፣ አህያ፣ ፈርሰ፣ ከብት ሳይቀር መሆኑ ዓላማው ምን እንደሆነ የሚያሳይ እንደሆነ የደረሰውን ያዩ እየተናገሩ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት ትህነግ ወደ አማራና አፋር ለወረራ ሲነሳ ፍጹም መንግስት ለመሆን ዕቅድም ሆነ ህልም አልነበረውም። ቢያስብም ሊሆንለት እንደማይችል ያውቀዋል። ምክንያቱም በሕዝብ ልብና እሳቤ ትህነግ ከስሟል።

“ከመንግስትነት ወደ ክልል፣ ከክልል ወደ ጉድጓድ፣ ከጉድጓድ በባህሪ መቆሸሽና በምግባር ተለክቶ ወደ አሸባሪነት ያደገ” ሲሉ የሚገልጹት የፖለቲካ ሳይነስ መምህር ” ከታላላቅ የንግድ ኢምፓየር ዝርፊያ ወደ ሊጥና አሻሮ ዘረፋ” የተመነደገው ትህነግ በቅርቡ አፋር፣ በተለይም አማራ ክልል የፈጸመው ተግባር እንደ እባጭ ይመስሉታል። ትህነግ በተራመደበትና ባደረበት ሁሉ ከንጹሃን ጭፈጨፋ ጀምሮ ያከናወነው ወንጀል ልክ እንደ እባጭ አሞጥሙጧል።

በምሳሌ ያስረዱት ምሁር እንዳሉት ” እባጭ እስኪያሞጠምጥ ካልተጠበቀ ሰንኮፉ አይነቀልም። ትህነግ የሰው ማዕበል አስነስቶ ወረራ ሲፈጽም፣ ግፍ ሲያከናውን ልክ እንደ እባጭ ሰንኮፉ እንዲነቀል ሲመቻች ነበር ፤ አሁን ትህነግ ልክ እንደ እባጭ ተሰብስቦ አሞጥሙጧል። ይህን ሰንኮፍ ለመንቀል ጊዜው አሁን ነው፤ ከዚህ በሁዋላ ጊዜ የለም”

መከላከያ እንዳለው በህግ የሚፈለጉ ጥቂት በመሆናቸው፣ ለማይቀረው ሽንፈት የትግራይ ወጣቶችና ሚሊሻ አባላት ለመከላከያ ሰራዊት እጃቸውን እንዲሰጡ ተማጽኗል። በሰላም እጅ ከሰጡ ምንም እንደማይገጥማቸው አመልክቷል። ከዛ በኩል ያለው ምላሽ ምን እንደሆነ ባይታወቅም ፣ መከላከያ የሰው ጎርፍ ቢመጣ ለመመከትና በኪሳራ ለመመለስ በበቂ ደረጃ መዘጋጀቱ ይፋ ሆኗል። የተለያዩ የህዝብ አደረጃጀቶች፣ እንዲሁም የየክልሉ ልዩ ሃይል ፖሊሶችና አዲስ ምሩቅ ወታደሮች ቦታቸውን እየያዙ ነው።

ለጉዳይ ቀርብ የሆኑ አካላት እንደሚሉት የመከላከያ ሰራዊት በቀናት ውስጥ ከሰማይና ከምድር፣ በአራቱም አቅጣጫ ወደፊት ይላል። ከትህነግ ጋር ውሉን የቀደደው ሕዝብ ይህ እንዲሆንለት ልጁን እየመረቀ ልኳል። ደጀን ሆኖ እየረዳ ነው። አስፈላጊም ከሆነ ራሱ ሊመዝመት ዝግጁ ሆኗል። የትህነግ ጭፍራና አመራሩ ምን እንደፈጸመ ያየው ሕዝብ፣ የትህነግ ፍጻሜ ካልሆነ እረፍት እንደማይሰማው በይፋ አስታውቋል። መንግስትም ” ቃል በገባሁት መሰረት እብጩን ከነሰንክፉ እንቅላለሁ” ብሏል።

አውሮጳ እንዲሁ ትናጋዋን ፣

በፋሽስታዊ ነቀርሳታርሳ፣ ተምሳ፣ በስብሳ

ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን፣

እንደኮረብታ ተጭኗት

ቀና ብላ እውነት እንዳታይ አንገቷን ቁልቁል ጠምዝዟት

ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት ሥልጡን ፣ ብኩን ፣ መፃጉዕ ናት

ሰቆቃው ጴትሮስ – ጸጋዬ ገብረመድህን

ይህን ጥሪ ተከትሎ ” ፈራሁ” ሲሉ አጭር ሃሳብ የላኩልን የዲሲ የዘወትር ተባባሪያችን አቶ መገርሳ፣ እስካሁን ከተካሄደው ይልቅ የአሁን የመረረና የጠነከረ እንደሚሆን ያምናሉ። ከየአቅጣጫው የሚወጡ መረጃዎች ስሜትን ያበላሻሉ። ህሊናን ይፈታተናሉ። በዚህ በነደደ ስሜት ውስጥ ሆነው የሚዋጉ ሃይሎች ምንም ከማድረግ ወደሁዋላ እንደማይሉ ያክላሉ።

የመከላከያ ሰራዊት ሚጥሚጣ ሳይቀር እየተረጨበት፣ በሚጠጣው ውሃ ውስጥ ሳይቀር ባዕድ ነገር እየተቀላቀለበት፣ ብቻውን ሲሄድ ከየመንደሩ በመውጣት እንዴት ሲያጠቁት እንደነበር ስለሚያስታውስ ዳግም እንደ ቀድሞ አይነት እድል እንደማይሰጥ ከግምት በላይ ገልጸዋል። አቶ መገርሳ እንደሚሉት ከሁሉም ወገን አንድ ተዓምራዊ ሃይል ካልተነሳ በቀር ዛሬ አስራ አንደኛዋ ሰዓት ናት። ያለው አማራጭ ጸሎት ብቻ ነው።

ለዚህም እንደማስረጃ የሚያቀርቡት ቀናት በጨመሩ ቁጥር ሁለቱም ወገኖች እየተካረሩ ሄደዋል። አሁን ጉዳይ ከሁለቱ የፖለቲካ ሃይሎች ወጥቶ የሕዝብ ጉዳይ ሆኗል። ለጊዜያዊ መሸሸጊያ ሲባል ህዝብ ሲጋት የቆየው ቅስቀሳ ዛሬ ሊቀለበስ የማይችልበት ደረጃ ደርሷል። “ያም ሆኖ ደግ አሳቢዎች ያሚችሉትን ቢያደርጉ ኪሳራው ሊቀነስ ይችላል። ግም ምን ማድረግ እንዳለባቸው እኔም አላውቀም፣ ግን ፈርቻለሁ። እንደአሁኑ የፈራሁበት ወቅት የለም”

ከደብረ ዘቢጥ ግንባር የምስክ ቅኝት የተመለሰ ለኢትዮ አስራ ሁለት እንደገለጸው አንድ የ15 ዓመት ታዳጊ ምርኮኛ አግኝቶ ነበር። ቀስ ብሎ በግል እንደ ማጫወት እያደረገ በቋንቋው አጫወተው። ሲለያዩ ውስጡ የቀረው ይህ ነበር።

“ስንት ዓመትህ ነው” ስለው ” 15″ አለኝ። “እንዴት ወታደር ሆንክ?” እየሳቀ / ፈገግ ብሎ ” ማን ያውቃል” አለኝ። ንግግሩ ግራ ገባኝና ” ማለቴ እንዴት ወታደር ሆንክ?” አሁንም ደገመና ” ማን ያውቃል። ሁሉም ወታደር ሁን ሲባል ይሆናል፤ እምቢ ማለት አይቻልም….” እንዴት እንደሚመለመሉ ስለሚያውቅ ጥያቄውን ቀየረና ” እንዴት መጣህ እዚህ ድረስ ” ድንገት ያመለጠው መስሎኝ በመገረም የሰማሁትን መልስ መለሰልኝ። ” ጥርስ ላወቅል ነው! ጥርስ እናወልቃለን” አለ። ከዛ በሁዋላ ምክር ለግሼው ሄድኩ። አሁን የት እንዳለ መረጃ የለኝም።

ጥርስ መንቀል ማለት ዘረፋ ማለት ነው

Exit mobile version