“ማንም ያሸንፍ ፤ ጫካ ያሉት የኦሮሞ ልጆችም ያሸንፉ ፣ ሌሎችም ያሸንፉ ነገርግን የኦሮሞን ሕዝብ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል” ያሉት የኦፌኮ ሊቀ-መንበር “በኦሮሞ አምላክ ይሁንባች። የቻላችሁ ሰዎች አስቡበት ብላችሁ ንገሯቸው።” የኦሮሞን ህዝብ አጥፍታችሁ አትጥፉ፤ ይህ ጨወታ አያዋጣንም። በመላ የኦሮሚያ ዱር ላሉት ያቺኑ ለህወሃቶች የሰጣችኋትን ዕድል ለእነርሱም ስጡ

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና “የኦሮሞ ነጻ አውጪ ጦር” ለሚሉት፣ መንግስት “ሸኔ” የሚለውና አማጺ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የማይረሳ ግፍ እንደፈጸመ ከሚነገርለት፣ ራሳቸው መራራን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ አመራሮችንና ደጋፊዎችን ሲያሰቃይ መኖሩ ማስረጃ ከሚቀርብበት፣ እነ ነዲ ገመዳን ጨምሮ በርካታ የኦሮሞ ዕንቁ ልጆችን ማስወገዱ በየጉቤው በይፋ ከሚገለጽበት የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር በይፋ አብሮ እንደሚሰራ ስላወጀው የኦሮሞ ነጻ አውጪ ጦር መረራ ያሉት ነገር የለም።

ጀርመን ድምጽ እንደዘገበው “… ጫካ ያሉት የኦሮሞ ልጆችም ያሸንፉ ፣ ሌሎችም ያሸንፉ ነገርግን የኦሮሞን ሕዝብ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል” ብለዋል። ዘገባው እሳቸው ያስከፍላል ያሉትን ዋጋ ባይዘረዝርም አክሎ “በኦሮሞ አምላክ ይሁንባች። የቻላችሁ ሰዎች አስቡበት ብላችሁ ንገሯቸው፣ የኦሮሞን ህዝብ አጥፍታችሁ አትጥፉ፤ ይህ ጨወታ አያዋጣንም። በመላ የኦሮሚያ ዱር ላሉት ያቺኑ ለህወሃቶች የሰጣችኋትን ዕድል ለእነርሱም ስጡ” የሚል ጥሪ ማቅረባቸውን አስታውቋል።

ድርጅታቸው በድጋሚ መሪ አድርጎ የመረጣቸው ፕሮፌሰር መረራ በጥቅሉ ሸኔ ከሚባለው አካል ጋር ድርድር እንዲደረግ፣ አለያ ኪሳራው ከፍተኛ እንደሚሆን ሲያስታውቁ፣ ይህ ታጣቂ ሃይል እያደረሰ ያለውን ጥፋት፣ ነጹሃን ላይ ስለሚደርሰው ግድያ፣ መፈናቀል፣ ንብረት ላይ ስለሚፈጸም ውድመት ምንም አላሉም። በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ብቻ ስለሚገደሉ የኦሮሞ ልጆች በግልጽ አቋማቸውን አላስታወቁም። በድርጅት ደረጃም ምን አቋም እንደተያዘ አልተነገረም።

የኢትዮጵያ መንግሥት ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር እርቅ እንዲያወርድ የኦፌኮ ሊቀመንበር ጥሪ ማቅረባቸውን በበጎ ያነሱ እንደሚሉት ኦፌኮ ቢያንስ በኦሮሞ ልጆች ላይ ስለሚፈጸመው ጥቃት፣ ሌሎች ወገኖች ላይ ስለሚፈጸም ብሄር ተኮር ማፈናቀልና ግድያ ጥርት ያለ አቋም አለመያዛቸው አግባብ እንዳልሆነ ግራ አጋብቷቸዋል።

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ይኸን የኦፌኮ ሁለተኛ አጠቃላይ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሲጀመር ያሰሙት የሰላም ንግግር ጥሪ በምን መልኩና እንዴት ሊካሄድ እንደሚችል አልተብራራም። መንግስት ሸኔ አመራሩ የማይታወቅ፣ በግልጽ የተቀመጠ ዓላማና ፖለቲካዊ ግብ የሌለው በመሆኑ ለመነጋገር እንኳን አዳጋች መሆኑንን ማስታወቁ አይዘነጋም።

ጃልመሮ የሚባሉት የጦሩ መሪ ሰራዊታቸው ማንንም ሰላማዊ ዜጋ እንደማይነካ፣ ይህን የሚያደርጉ ካሉ እርምጃ እንደሚወስድ በተደጋጋሚ ማስታወቃቸው፣ ንጽሃንን የሚገድሉና የሚያሰቃዩ፣ እንዲሁም የሚያፈናቅሉ የመንግስት ሃይል መሆናቸውን መናገራቸው አይዘነጋም። እሳቸው ይህን ቢሉም ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው የኦሮሞ ልጆች፣ እናቶች፣ ሚስቶች በይፋ ኦነግ ሸኔ ግድያ መፈጸሙን በተደጋጋሚ በተለያዩ የግልና የመንግስት እንዲሁም የውጭ ሚዲያዎች እየገለጹ ነው።

ኦእነግ ሸኔ ሸዋ አንዳንድ አካባቢዎች መዝለቁ ግራ የሚያጋባቸው ” በርግጥ ሸኔ ማን ነው” የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። ከጀርባውስ ማን አለ የሚል ጥርጣሬና ግምት የሚሰጡም አሉ። ሰሞኑንን በተካሄዱ የሕዝብ ውይይቶች ላይ ነዋሪዎች ሲናገሩ እንደተሰማው ራሱ ኦሮሚያ ብልጽግና ውስጥ ሸኔ መኖሩን በገሃድ መናገራቸው ጥርጥሩን ያጎላዋል።

ስለ ኦነግ ሰራዊትና አቋም የሚያውቁ እንደሚሉት ጦሩ ከጥንት ጀመሮ አንፌሎ ከሚባለው የሱዳን ጠረፍ ነጻ ግዛቱ ለቆ እስከ ሸዋ ድረስ ስለመድረሱ ይጠራጠራሉ። በረዣዥም ሳር የተሸፈነው ነጻ ግዛታቸው በማንም የማይነካና በአካባቢው ወርቅ እያመረቱ እንደሚኖሩ የሚያውቁ እንደሚሉት ይህ ሃይል ምዕራብ ሸዋ መድረሱን ለመቀበል ያዳግታቸዋል። ሰሞኑንን በሕዝባዊ ስብሰባዎች እንደተሰማው ሸኔ ያለው በየአካባቢው ባሉ የአስተዳደር እርከኖች ኦሮሚያ ብልጽግና ቢሮ ውስጥ ነው።

በዚህ መነሻ ይመስላል ሕዝብ ” ራሳችሁን አጽዱ ቀሪው ጉዳይ ቀላል ነው” በሚል በምሬት ጥሪ ሲያስተላልፍ ተሰምቷል። መረራ ጫካም ያሉት ሆነ እያስተዳደሩ ያሉት ሁሉም ኦሮሞ መሆናቸውን ገልጸው ድርድር የጠየቁት በዚህ መነሻ ይሁን በሌላ ስጋትና ሂሳብ የጀርመን ድምጽ ዘገባ አላብራራም። እሳቸው ለትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር የተሰጠው እድል ለኦነግ ሸኔም እንዲሰጥ መማጸናቸው የተዘገበው ” … የቻላችሁ ሰዎች አስቡበት ብላችሁ ነገሯቸው” በሚል የከረረ ተማጽኖ ነው።

ፕሮፌሰር መረራ በጉባኤው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ መንግሥት ከአንድ ዓመት በላይ ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ጋር መዋጋቱን ግጭት ለማቆም መወሰኑን አመልክተዋል። በተመሳሳይ በኦሮሚያም ባለሥልጣናቱ “ሸኔ” ከሚሉት ታጣቂ ጋር እርቅ ሊያወርድ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን ጦርነት ኦፌኮ ከጅማሮው መቃወሙን ያስታወሱት መረራ አሁንም መንግስት በትግራይ ብቻ ሳይሆን ኦሮሚያን ጨምሮ ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ልዩነቶችን በእርቅ በመቋጨት ለህዝብ ሰላም እንዲሰጥ ጠይቀዋል። “…የኦሮሞን ህዝብ አጥፍታችሁ አትጥፉ፤ ይህ ጨወታ አያዋጣንም። በመላ የኦሮሚያ ዱር ላሉት ያቺኑ ለህወሃቶች የሰጣችኋትን ዕድል ለእነርሱም ስጡ” ብለዋል። ከላይ በተገለጸው መሰረት ግን እንዴት? ለሚለው የተብራራ ነገር የለም።

ሰሞኑንን የኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳድር ንግግር ተገልብጦ “አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የኦሮምያ ክልልን በአንድ ወር ግዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ወደ ቀድሞ ሰላሟ እንመልሳታለን” አሉ ተብሎ የተናፈሰውና የፖለቲካ ጉሊት ላይ ከፍተኛ ዋጋ አስገኝቶ የነብረው የተሳሳተ ነግግር ሳይሆን በትክክል “ህዝባችንና አደረጃጀታችን አንድ ሆኖ አቋም ከያዘ ሸኔ አንድ ወር መቆየት አትችልም” ማለታቸው ሕዝብ የሚሰጠውን አስተያየት ያጠነክራል። አቶ ሽመልስ አመራር ሲሉ ከላይ እስከታች ያለውን መዋቅር ነው።

ትህነግን በማስወገድ ትግል ውስጥ በኦህዴድ ዘንዳ ሚስጢር ለመጠበቅ ሲባል እስከ ታችኛው አደረጃጀት ድረስ ዘልቀው እንዲገቡ የተደረጉ የሌላ ድርጅት የትግል አጋሮች ከድሉ በሁዋላ የህን መዋቅር መጠቀማቸው አሁን ክልሉን እየመራ ላለው ብልጽግና ኦሮሚያ አስቸጋሪ ፈተና እንደሆነበት ሲነገር መሰነበቱ ይታወቃል። ለዚህም ይመላል የኦሮሚያ ብልጽግና ራስን ማጥራት ሸኔን ከመታገል በላይ ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍለው አምኖ ወደ ስራ መግባቱን አመልክቷል።

የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ሲጠይቅ የነበረው ኦፌኮ አሁን ጫካ ካሉት ሃይሎች ጋር ንግግር እንዲደረግ በመሪው አማካይነት ሲጠይቅ ጃል መሮ በግልጽ እንዳሉት የሽግግር ጥያቄውን ዳግም ለማደስ አስበው ይሁን አይሁን በግልጽ የታወቀ ነገር የለም።

ያነጋገርናቸው የክልሉ ተወላጆች እንደሚሉት ሸኔ አሸንፎ መንግስት አይሆንም፣ ብልጽግናም ሸኔን አያጠፋም። ሸኔ የተለያዩ አደረጃጀቶች አለው ብለው የሚያምኑት እንደሚሉት ከዋናው አመራር ጋር ግንኙነት የሌላቸውና ለዕለት ውሎ የሚንቀሳቀሱ አካባቢ ተኮር አደረጃጀቶች እያገነገኑ መሂዳቸው ስጋት ሆኖባቸዋል። እነዚህ ሃይሎች ከፖለቲካ ጥያቄ ይልቅ ሃብት መሰብሰብ፣ እያፈኑ ገንዘብ መጠየቅ፣ በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ተወላጆች የሚመሩ እንደሆኑም ይገልጻሉ። እነዚህን ሃይሎች ጃል መሮ አያውቋቸውም ባይ ናቸው።

ይህ ስጋት ያየለባቸው እነዚህን ሃይሎች ማን ነው በየሰፈሩ የሚፈለፍላቸው? ሲሉ ጠይቀው መንግስት ይህን ሲመልስ ብቻ ችግሩን መንቀል እንደሚችል ያመለክታሉ። ያም ሆነ ይህ ግን በኦሮሚያ አስቸኳይ ቀልብን የመሰብሰባና ወደ አዕምሮ ተመልሶ የሰከነ ፖለቲካ ማራመድ ካልተቻለ ክልሉ በጎበዝ አለቆች እጅ ሊወድቅ እንደሚችል የሚገምቱም አሉ።

Leave a Reply