Site icon ETHIO12.COM

አሁን ባለው ሁኔታ ሃገራችን ውስጥ ጋዜጠኛ ለመሆን የሚያስፈልገው … ደፍሮ ዘው!!

አሁን ባለው ሁኔታ ሃገራችን ውስጥ ጋዜጠኛ ለመሆን የሚያስፈልገው ፡ ብዙ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ …. የዩቲዩብ ቻናል ወይም በአንድ ቴሌቪዥን ላይ የአየር ሰአት መከራየት …… እና ድፍረት ብቻ ነው ። ጋዜጠኝነትና የፖለቲካ ተንታኝነት ሁሉም ደፍሮ ዘው የሚልበት ሙያ እየሆነ መጥቷል ። ሁሉም ተንታኝ ሁሉም ጋዜጠኛ ሆኖ ኤኮኖሚውን ፖለቲካውን እና ወታደራዊ ጉዳዮች ሳይቀሩ በእውቀት አጠር ደፋሮች ሲተነተኑ ፡ ማየት የዚህ ትውልድ እጣ ሆኗል ።

እናም በዚህ ጋዜጠኝነት ማለት አላዋቂነት ማለት እስኪመስል ድረስ ሙያው ትዝብት ላይ በወደቀበት በዚህ ወቅት እንደገነነ መኩሪያ ያሉ ጥቂት እንቁዎችን እያየን በነሱ እንፅናና ዘንድ ግድ ነው ። ጋዜጠኛና ደራሲ ገነነ መኩሪያ በቅርብ የሚያውቁት ሰወች ተነቃናቂው ቤተ መዛግብት በሚል ቅፅል ስም የሚጠሩት ገነነ መኩሪያ ፡ የጋዜጠኝነት መለኪያ ነው ቢባል አልተጋነነም ።

ሰው እንዴት ስለሁሉም ነገር ያውቃል ? ገነነ ስለ አንድ ፖለቲከኛ ሲያወራ ተጠያቂው ሁሉ ይገርመዋል ። ገነነ የሚያወራቸው ነገሮች ባብዛኛው አዲስና ተሰምተው ያልታወቁ ስለሚሆኑ ፡ ለሱ ብቻ በጆሮው ጠርተው የነገሩት ነው የሚመስለው ። ( የንባብና የትጋት ውጤት ይልሃል ይሄ ነው ) ኢህአፓና ስፖርት ፡ ፍትሃዊ የጠጅ ክፍፍል እና ሰሞኑን ደግሞ መኩሪያ የተሰኙትን ልክ እንደወሬው በአዳዲስ ነገሮች የተሞሉ መፅሃፍትን ወደ አንባቢ ያደረሰው ይህ ሰው የኢትዮጵያ ነገስታትና መሪዎች ፡ ፖለቲከኞች ስለ ሙዚቃና ሙዚቀኞች ወይም ስለ ስእል ወይም ደራሲያን ወይም ጋዜጠኞችን የሚመለከት ወሬ ካነሳ ፡ ሰምተውት የማያውቁትን አስገራሚ ነገሮች ይናገራል ።

ይህ ሰው የኢትዮጵያን እግር ኳስ ከጣልያን ጊዜ ጀምሮ አሁን እስካለው ድረስ ማወቁ ብቻ ሳይሆን በጊዜው የነበሩ ነገሮችን እቦታው እንደነበረ ሆኖ ሲያወራ ያስደንቃል ። ይህ ሰው ስለ ኢህአፓ ስለደርግ ስለኢህአዴግ ሲያወራም ሁሌ አዲስ ነገር ይዞ መቅረብ የሚችል አስገራሚ ሰው ነው ። ገነነ መኩሪያ ( ሊብሮ ) ገነነን የማውቀው ከአመታት በፊት ያሳትማት በነበረችው ሊብሮ የስፖርት ጋዜጣ ነው ። እና ያኔም እንዲሁ ነው ።

ገነነ ስለምንም ያውራ ግን ሁሌም ስለሚያወራው ነገር ያልተሰሙ ነገሮችን እየተናገረ አድማጭን ያስገርማል ። ዛሬ ገነነን ያስታወስነው ከመስከረም ሁለት ጋር አዘጋጅቶት የነበረው ፕሮግራም ትዝ ብሎን ነው ። አሻም ቴሌቪዥን ላይ ታሪክን ወደ ኋላ መለስ አድርጎ በሚያሳየው በዚህ ሁለገብ ፕሮግራም ፡ አብዮቱንና መስከረም ሁለትን ከተለያየ አንግልና አተያይ ጋር ፡ እያዛመደ አሪፍ ፕሮግራም ሰርቶ ነበር ። ይህም ምስል መስከረም ሁለትን አስመልክቶ የሰራው ፕሮግራም ላይ ለቴሌቪዥን አድማጮቹ ይዞ የቀረበው ሴቲንግ ነው ።

ገነነ መስከረም ሁለትን በተመለከተ ባቀረበው በዚህ ፕሮግራም ላይ በፎቶው እንደሚታየው በወቅቱ የነበሩ መፈክሮችን የሶሻሊዝም ስርአት ቀማሪዎች የነ አባባ ሊኒኒን ፎቶ ፡ በወቅቱ የነበረውን ፍርሃትና የጨለማ ጊዜ የሚገልፅ ጥቋቁር ቀለማት አስፈሪ ሁኔታ ድንግዝግዝ ብርሃን ፡ ደም የሚመስል ጨርቅና የደርግን ወታደራዊ ልብስ ለብሶ. .. ብቻ ዛሬ ላይ ተሁኖ ያኔን የሚያሳይ ምስል ከሳች ሴቲንግ ሰርቶ ነው ስለደርግና መስከረም ሁለት ያዘጋጀውን ፕሮግራም ያቀረበው ።

ለተመልካች መጨነቅ ይልሃል እንዲህ ነው ። በነገራችን ላይ ገነነ ሁሌም አንድ ፕሮግራም ሲያዘጋጅ እንዳለ ድባቡ የሚያዘጋጀውን ፕሮግራም እንዲመስል አድርጎ ነው ። ብቻ ሁሌም አንድ ፕሮግራም ይዞ ከመጣ ለአድማጭ ለተመልካች ክብር ተጨንቆ በሚገባ ተዘጋጅቶ ብዙ እውቀት አፍሶብህ ነው የሚሄደው ። ይህን መሳይ ለአድማጭና ተመልካች አክብሮት ያላቸው ገነነን መሳይ ጋዜጠኞች ያብዛልን ።

Salute ! © ይህን ያልተዘመረለት ብቁ ሰው ፡ አስታውሶ ይህን ፅሁፍ ላጋራን Wasihune Tesfaye ይልመድብህ እንላለን tnx Book for all page

Exit mobile version