ETHIO12.COM

በህገ-ወጥ መንገድ የተከማቸና ከፍተኛ የዋጋ ግምት ያለው ብረት በቁጥጥር ስር ዋለ

«በህገ-ወጥ መንገድ ተከማችቶ በህብረተሰቡ ጥቆማና በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ስር የዋሉት ንብረቶች በአብዛኛው ባለሃብቶቹ ከጁንታው ጋር በግንባር ተሰልፈው ሀገር በማፍረስ ተልዕኮ ላይ የተሰማሩ ሲሆን ከተማ ውስጥ ባሉ ወኪሎቻቸው እያስነገዱ ገንዘብ የሚላክላቸውና ብሩንም ለከፈቱት ጦርነት አስፈላጊ ግብአቶችን ለማሟላት እንደሚጠቀሙበት ፖሊስ ደርሼበታለሁ ብለዋል። ግለሰቦች የራሳቸውን ጥቅም ከሀገር በማስቀደም የግለሰቦችና የድርጅቶችን ማንነት ሳይለዩ ውክልና እንዳይቀበሉ ፖሊስ አሳስቧል»



የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ፊናንስ ካምፕ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባካሄደው ኦፕሬሽን በአንድ መጋዘን ውስጥ በህገ-ወጥ መንገድ ለብዙ ጊዜ የተከማቸና ከፍተኛ የዋጋ ግምት ያለው ተጨማሪ ብረት በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታውቋል።

ከፍተኛ የዋጋ ግምት ያለው ብረት፣ የከባድ መኪና ጎማዎችና የተለያዩ መጠን ያላቸው የፕላስቲክ ቱቦዎች ተይዘዋል።

በዚህ ህገ-ወጥ ድርጊት የተጠረጠረው ድርጅትም ዩናይትድ አልፋ ኮሜርሻል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መሆናቸውን ፖሊስ ገልጸዋል።

አሸባሪው የህዋሃት ቡድን በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስና ሀገርን የማፍረስ እኩይ ተልዕኮውን ለማሳካት የተለያዩ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን ሲሰራ መቆየቱና የተለያዩ የወንጀል መረቦችንም ዘርግቶ በሀገር ደረጃ የሸቀጦች እጥረት እንዲፈጠር ማድረጉ ይታወቃል፡፡

በህገ-ወጥ መንገድ ተከማችቶ በህብረተሰቡ ጥቆማና በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ስር የዋሉት ንብረቶች በአብዛኛው ባለሃብቶቹ ከጁንታው ጋር በግንባር ተሰልፈው ሀገር በማፍረስ ተልዕኮ ላይ የተሰማሩ ሲሆን ከተማ ውስጥ ባሉ ወኪሎቻቸው እያስነገዱ ገንዘብ የሚላክላቸውና ብሩንም ለከፈቱት ጦርነት አስፈላጊ ግብአቶችን ለማሟላት እንደሚጠቀሙበት ፖሊስ ደርሼበታለሁ ብለዋል። ግለሰቦች የራሳቸውን ጥቅም ከሀገር በማስቀደም የግለሰቦችና የድርጅቶችን ማንነት ሳይለዩ ውክልና እንዳይቀበሉ ፖሊስ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አሸባሪ ቡድኑ የዘረጋቸውን ኔትዎርኮች በመበጣጠስ በብዙ ቢሊየን ብር የሚገመት በተለያዩ ቦታዎች የተከማቸ ህገ-ወጥ ብረትንና በድርጊቱ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ አይዘነጋም፡፡

በህብረተሱ ያላሰለሰ ትብብርና ጥቆማ በመሆኑ ጥቆማውን ላደረሱን ግለሰቦች ሁሉ ታላቅ ምስጋና አቅርበዋል። በቀጣይም ዜጎች ተመሳሳይ ጉዳዮችና ወንጀሎች ሲያጋጥሟቸው በነፃ የስልክ መስመሮች 987፣ 816፣ 991 እንዲሁም በቢሮ ስልክ ቁጥር 0111110111 (አዲስ አበባ ፖሊስ) ፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ስልክ ቁጥር 0115524077 እና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ስልክ ቁጥሮች 0115309027፣ 0115309231፣ 0115309077 መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል። (ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version