Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያን ለማፍረስ ተዘጋጅቶ የመከነው ስትራቴጂ

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት አገር የማፍረስ ቅዠቱን እያጠናከረ የመጣው ከማዕከል ሸሽቶ መቀሌ ከከተተ በኋላ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ሾልከው የሚወጡ ማስረጃዎች ዋቢ ናቸው። አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን በማተራመስ፣ ለእርሱ ትርፍ ሊያመጣለትና ወንጀሉን ለመሸሸግ በየአካባቢው ግጭቶችና ሁከት እንዲፈጠር በማድረግ፣ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት በህዝብ ላይ ሽብር በመፍጠር፣ ያልተፈጠረውን ተፈጥራል፣ ያልተከሰተውን ተከስቷል እያለ በማወናበድ የለውጥ ሃይሉን ለመጣል ስትራቴጂ ነድፎ መስራቱ ተጋልጧል። 

አሸባሪው ህወሃት አገር ለማተራመስ የነደፈው ባለ 80 ገጽ ስትራቴጂ ሾልኮ መውጣቱ የቡድኑን እኩይ ድርጊት ከስር መሰረቱ የሚያሳይና የክፋቱን ጥግ ለመረዳት የሚያስችል ነው። ይህ ሰነድ “የትግል ልዩ ምዕራፍ እድገቶች እና የምከታችን ቀጣይ ስትራቴጂዎች፣ ስልቶች እና አቅጣጫዎች (ቁጥር – ሁለት)” የሚል ርዕስ የተሰጠውና መስከረም 2013 ዓ.ም የተዘጋጀ ነው። ሰነዱ በጥብቅ የሚያዝ ስለመሆኑም ተገልጿል። ዋነኛ ትኩረቱ ቡድኑ የለውጥ መንግስት አስወግዶ ተመልሶ ስልጣን ላይ የሚቆናጠጥበትን መንገድ፤ አሊያም ሀገረ ትግራይን የሚመሰርትበትን ስትራቴጂ ላይ ነው።

ይህን ከግብ ለማድረስ በሃይል የዞት ከኖረው የመንግስት ሥልጣን ያሰወገደውን የለውጥ አመራር ፋታ እንዳያገኝ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ የመንቀሳቀስን አሰፈላጊነት ይዘረዝራል። በተለይ በአገሪቷ ውስጥ በልዩ ልዩ አካባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ እንዲቀጣጠል ማድረግ፣ በጸጥታ አካላት ላይ ጥቃት መፈጸም እንዲሁም የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ከውስጥና ከውጭ ሀይሎች ጋር በቅንጅት እየሰሩ ያለመረጋጋትን መፍጠር በአንድ አቅጣጫ ዘርዝሯል። የጦርነት አይቀሬነት በመዘርዘር ህዝቡ እንዲዘጋጅ ማድረግ ወሳኝ ስትራቴጂ አድርጎ አስቀምጧል።

በእጅጉ የሚገርመውና የአሸባሪ ሕወሃት እኩይ ተግባር በግልጽ የሚያስቀምጠውና ከወራት በኋላ ተግባራዊ ያደረገው የመከላከያ ሰራዊት የለውጥ ሃይሉ ደጀን እንዳይሆን ለማድረግ ያወጣው ስትራቴጂ ነው። የዚህ ስትራቴጂ አንኳር ነጥብ በሁሉም ገጽታዎች ጦርነት አይቀሬ መሆኑን በመጥቀስ ይህን ለመመከት ወታደራዊ ሚዛን አንገዳግዶ/አዛብቶ የመናድ አስፈላጊነትን አሰቀምጧል። አሸባሪው ሃይል የፌዴራል መንግስት (ጠላት ብሎ የፈርጆታል) የተጠናከረ አቅሙን አሰባስቦ “እኛን ለማጥፋት እስከሚመጣ ድረስ በመከላከል ስም የምንጠፋበትን እድል መፍጠር የለብንም” በሚል ገልጾ ወታደራዊ ሚዛን በማናጋት ወደ ጥቃት የመሸጋገር ስትራቴጂ መከተልና ወደ ሀገራዊ ጥቃት መግባት እንደሚገባ አስፍሯል። የትግራይ ህዝብ ለዚሁ ጦርነት መዘጋጀት እንዳለበትም ገልጿል፡፡ ይህን በግልጽ የሚያሳየውና የሚያረጋግጠው የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊትን ለመምታት፣ ትጥቁን ለመጠቅለል ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀሱን ነው። የአገር ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ፣ በማንኛውም ወቅት ሊነሳ የሚችል ወራሪ ሃይልን በመመከት የትግራይ እናቶችን፣ አባቶችን፣ ወጣቶችን ለመታደግ ሌት ተቀን የሚለፋውን መከላከያ ሰራዊት ለመምታት የነደፈውን እስትራቴጂ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ፈጽሞታል። በዚህም ብዙዎች ዋጋ እነዲከፍሉ አድርጓል። የእርሱ ቃል አቀባይ የሆነው “መብረቃዊ እርምጃ” ወሰድን በማለት የገለጸው ጥቃት አድርሷል። በዚህም አሸባሪ ቡድኑ አገር የማፍረስ ዓላማውን በግልጽ አረጋግጧል።   

አሸባሪው ቡድን “የአብይ አስተዳደር” ከሪፎርሙ በኋላ የምእራባውያንን ተልዕኮ ተቀብሎ በተመኙት መንገድ ሊተገብርላቸው ባለመቻሉ እነርሱ ያስጀመሩት ሪፎርም አደጋ ላይ ወድቋል፤ ስለዚህም ሌላ አማራጭ ለማፈላለግ ተገደዋል በማለትም በወጣቶች ተጋድሎ የተገኘውን ለውጥ ይክዳል። የመላ ሕዝቡን ተጋድሎ በተለይም ቄሮ፣ ፋኖና የሌሎች አካባቢ ወጣቶች የተሰዉለትን ትግል ምዕራባዊያን ያመጡት አድርጎ በመሳል ከሀዲነቱን በተጨባጭ አረጋግጧል። ከአዲስ አበባ ሸሽቶ መቀሌ እንዲከትም ያደረጉትና ሪፎርሙን ያመጡት ምዕራባውያን በማሰመሰል በሰነዱ ውስጥ ሽንፈቱን ለመደበቅ ይውተረተራል።

ቀደም ሲል የትራምፕ አስተዳደር በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የያዘውን አቋም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ ባለመቀበላቸው የአሜሪካን መንግስት የሚያዋርድ ተግባር እንደፈጸሙ ይገልጻል። በዚህ ምክንያት “ከትራምፕ አስተዳደር ጋር የነበረው ግንኙነት እና ተአማኒነት በእጅጉ እንዲበላሽ አድርጎታል” በማለት ክስተቱ ለአሸባሪው ቡድን ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረለት ያትታል። ከዚህ ባሻገር የጆ ባይደን አስተዳደር ለቡድኑ የተሻለ እድል እንደሚፈጥር አስቀምጧል። አሸባሪው ቡድን በሰነዱ ውስጥ እነዚህ ጉዳዮችን ሲጠቃቅስ ለእርሱ የተንበርካኪነትና የተላላኪነት ሚናው ይጠቅመኛል በማለት ነው። በሌላ በኩል ግን ሲጠና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመሩት መንግስት ምዕራባዊያን በፈለጉት መንገድ ሊመሯቸው እንዳልቻሉ፣ ይህን አድርግ አታድርግ ለመባል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን የሚያረጋግጥ ምስክርነት ሰጥቷል። ምንም እንኳን በአደባባይ ባይመሰክሩም ኢትዮጵያን ሊያስከብራት የሚችል የማይላላክ መሪ በመምጣቱ የትራፕም ሆነ የጆ ባይደን አስተዳደር መከፋታቸውን በሰነዱ ላይ አትቷል። የሚደነቅ ምስክር ነት ነው። እነርሱ ግን መላላክ አመላቸው በመሆኑ “የጆ ባይደን አስተዳደር” የተሻለ እድል እንደሚፈጥርላቸው ገልጿል። በርግጥም አሁን በተጨባጭ የሚታየው የኢትዮጵያን እውነት ያለመስማትና ጫና ማሰደር ለተላላኪው ቡድን የተለየ ምልከታ መኖሩን ያረጋግጣል።

በሱዳን በኩል መውጫ መግቢያ ለመፍጠርም እንደወሳኝ ስትራቴጂ መንቀሳቀስ እንደሚገባ በሰነዱ ላይ ተመላክቷል። የኤርትራ መንግስት ከስልጣን ማስወገድ ሌላኛው ወሳኝ ስትራቴጂ ተደርጓል። የሚገረበው በሌላ አገር የውስጥ ጉዳይ በመግባት መንግስት ለመገልበጥ ማሴራቸውን በሰነዳቸው አጋልጠዋል። የኤርትራ መንግስት ቅርብና አደገኛ ሁኔታ ተጋርጦብኛል በማለት ራሱን ለመከላከል እርምጃ ቢወስድ የትኛው የዓለም አቀፍ ህግ ይከለክለዋል?

አሸባሪው ህወሃት በክልሎች በተለያዩ ቦታዎች ሁከት እንዲፈጠር፣ ብጥብጥ እንዲከሰት፣ የውስጥ መፈናቀል እንዲባባስ፣ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ ማድረጋቸው የስትራቴጂው አንድ አካል ነው።

በሀገሪቱ ሰላም እና ፀጥታ የሚባል እንደሌለ በማስተጋባት እስከ ወዲያኛውም እንደማይኖር ፕሮፖጋንዳ በመስራት እንዲሁም ኢኮኖሚው ጠቅልሎ እየሞተ እንደሚገኝ፣ ህዝቦች እርስ በእርሳቸው እየተናከሱ እንደሚገኙ፣ ብቸኛው መፍትሄም ይህን ቡድን ማጥፋት መሆኑን በመግለጽ በአጭር ጊዜ መንግስትን ለማስወገድ መሰራት እንዳለበት በሰነዱ ላይ ተገልጿል። ይህን የተመለከቱ አገሮች ደግሞ አገር ትፈርሳለች የሚል ስጋት አደረባቸው። ሰነዱም ላይ አውሮፓውያን እንደሰጉ ተገለጸ።

በአውሮፓ አብዛኞቹ ሀገሮች “ሀገር እየፈረሰች ነው” የሚል ሰፊ ስጋት እንዳለባቸው ያትታል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጠር በሚችል አለመረጋጋት ምክንያት “የአፍሪካ ቀንድ በአጠቃላይ ይታመሳል” የሚል ስጋት እንዳላቸው ይገልጻል። ከዚህ በመነሳትም ብዙ የአውሮፓ መንግስታትም ሆነ የሩቅ ምስራቅ ሀገራት ከኢትዮጵያ መንግስት ይልቅ ከቡድኑ ጋር የመገናኘት ፍላጎት እያሳዩ መሆኑንንም ያብራራል። በሌሎች አገሮች ዘንድ የዚህ ዓይነት ስሜት እንዲመጣ ነው ሲሰራ የቆየው።         

ሰነዱ በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጥናል። የመጀመሪያው ሁሉን አቀፍ ተቋማዊ አቅም የገነባች ትግራይን (ዲፋክቶ ትግራይ) መመስረት ነው። የሽብር ቡድኑ ከበረሃ ጀምሮ የያዘው ዓላማ ትግራይን ከኢትዮጵያ መገንጠል በመሆኑ አሁን ባዘጋጀው ሰነድ ላይ ይህን ለማሳካት ወሳኙ ጊዜ እንደደረሰ አስቀምጧል። በትግራይ ክልል ያካሄደው ህገ ወጥ ምርጫ አስመልክቶ በሰነዱ ላይ እንደገለጸው “ምርጫ በማካሄዳችውን ብቸኛው ህገ-መንግሥታዊ ክልል ሆነን በከፊል ሀገራዊነት (ዲፋክቶ) ክልል ውስጥ እንገኛለን” ሲል ምርጫ ማካሄዱ ያስገኘለትን ጥቅም ይገልጻል። ይህ እንግዲህ በህዝባዊ አመጽ ከማዕከል ተሽቀንጥሮ ሲወገድ ለራሱ የሚለው አገር ለመመስረት ህዝብን ምሽግ እንዳረጋ ያሳያል። ህዝብ የአሸባሪውን ድርጊትና ሴራ በጥንቃቄ ሳያጤን ከወንድሞቹ እየነጠለውና ወደ ጦርነት እየመራው መሆኑን ሳይገናዘብ ምርጫ በማካሄድ ለምሽግነት አመቻቸው። ከዚያም ራሱ ጦርነት አስጀምሮ “የመረጠከውን መንግስት ሊያፈርሱብህ፣ ራስህ በራስህ ማስተዳደር እንዳትችል ሊያደርጉህ ነው” በሚል የሀሰት ፐሮፓጋንዳ በማወናበድ ወንጀለኞችን ደብቆ ወንጀል ሲፈጽም ከረመ። 

በተጨማሪም  በክልሉ የሚፈጸሙ አደረጃጀቶች በሙሉ የዲፋክቶ ትግራይ ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲደራጁ እንደሚደረግ በሰነዱ ላይ በዝርዝር ተቀምጧል።  በተለይ በፀጥታ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከቀረጥ እና ግብር መሰብሰብ፣ ከሶስተኛ ወገን ከሚሉት ጋር ግንኙነት እንዲሁም ንግድ እና ኢንቨስትመንት የሚሳለጥበት መንገድ አስቀምጧል። ከዚህ በተጨማሪ መገናኛ ብዙሃን እና የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት የትግራይ ህገ መንግስት የሚስተካከልበትን ሁኔታ እንደሚፈጠር ይገልጻል። “ህገ መንግስት መነካት የለበትም፤ ከተነካም በመቃብሬ ላይ ነው” የሚለው አሸባሪው ህወሃት ለራሱ ሲሆን ህገመንግስት እንደሚያሻሽል ግብ አስቀምጦ ሲሰራ ከርሟል። 

ሁለተኛው ጉዳይ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በፍጥነት በማስወገድ “የሽግግር መንግስት መመስረት” ነው። በሰነዱ ላይ በስፋት ትኩረት የተደረገው የሀገራዊ ለውጡ መሪ የሆኑትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ ከስልጣን የሚወገዱበት ስትራቴጂዎችዎችን ነው። በስትራቴጂው ሰነድ ላይ “የአብይ ቡድን ሊወድቅ የሚችልበት በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሰላም እና ደህንነት ማጣት፣ ዲፕሎማሲያዊ ሁኔታዎችም በመሰረቱ ከቦታው ተንገዳግዷል፡፡

ይህ በስልጣን ላይ ያለው ሀይል በሀገራዊ የአመራር ክፍተት (ሊደር ሺፕ ጋፕ) ምክንያት በተወሰነ የሰራዊት ገመድ ካልሆነ በስተቀር መቆም የሚችልበት ነገር የለም፡፡ በማንኛውም ወቅት የመውደቅ እድሉ እየጎላ እየወጣ ነው፡፡” በሚል ተገልጿል። እዚህ ላይ ነው “በተወሰነ የሰራዊት ገመድ ካልሆነ በስተቀር መቆም የሚችልበት ነገር የለም” በማለት ሰራዊቱ ለመንግስት ታማኝ መሆኑን በዘወርዋራ የሚገልጸው። ለዚህ ደግሞ የመንፈንቅለ መንግስት ሙከራው ጨምሮ ሰራዊቱ በመንግስት ላይ እንዲነሳ ለማድረግ ብዙ ርቀት ተሄዶ ቀይ መስመር መታለፉ የቅርብ ጊዜ እውነት ነው። አገር ማፍረስ ማለት ይህ አይደለምን?

በሰነዱ ላይ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳጣና በተለይ “በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል እና በጋምቤላ ተቃውሞ እየተጠናከረ መጥቷል” በሚል ትንተና የዐብይ መንግስት በ2013 ዓ.ም እንደሚያበቃለት ይገልጻል። ከዚህ በተጨማሪ “በምዕራባውያን ዘንድ የዐብይ አስተዳደር ተቀባይነት አጥቷል” በሚል ትንተና ላይ ተመስርቶ አዲስ መንግስት እንደሚመስረት በግልጽ አስቀምጧል። እዚህ ላይ አሸባሪው ህወሃት ከኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ውስጥ የወጣና የተተፋ መሆኑን ይዘነጋዋል። ለለውጥ አመራሩ ያለውን አክብሮትና ወደፊት በመውሰድ ያሻገረኛል የሚለውነ እምነቱን ማየት አቅቶታል።

 ዶክተር አብይን የለውጥ አርአያና መሪው መሆናቸውን የሚገልጽበትን መንገድ በጭፍን ጥላቻ ሰለሚመለከተው እውነቱን መገንዘበ አልቻለም። ሕዝቡ አገሩን እንደሚወድ፣ አንድ እንደሚሆን በ27 ዓመት የገዥነት ዘመናቸው ለመረዳት ያለመቻላቸው ከትንታኔው መገንዘብ ቀላል ነው። ያሉት ሳይሆን ቀረ። ቀይ መስመሩን ሲያልፉ ህዝቡ አንድ ሆነ፤ በአንድነት ቆመ። መንግስት ከመውደቅ ይልቅ በህዝብ የተመረጠ መንግስት የመመስረቱ ጉዳይ እውን ሆነ።

ቡድኑ እንዳሰበው ባይሳካለትም ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ መንግስት የሚባል እንደማይኖር የሚገልጸው የስትራቴጂ ሰነዱ በሁሉም ዘንድ ተጠናክሮ የወጣው ተቃውሞ እያስተባበረ የሚመራ ጠንካራ ሀገራዊ አመራር እንዳልተፈጠረ ይገልጻል። ስለሆነም የትግራይ ህዝብ እና ህወሃት ትግሉን እያስተባበሩ እንደሚመሩና ሀገራዊ አደረጃጀት በፍጥነት እንደሚፈጠር በሰነዱ ላይ ሰፍሯል።

ጦርነቱ ሀገራዊ ይዘት እንዲኖረው ማድረግ አሸባሪው ቡድን ስትራቴጂ አንዱ አቅጣጫ ሆኖ ተቀምጧል። ስለሆነም በተለያዩ አካባቢዎች ተበታትኖ የሚገኘው አቅሞቹን በሙሉ ማሰባሰብ እና ማቀናጀት የግድ እንደሚል አስፍሯል፡፡ በመጠነ ሰፊ የፕሮፖጋንዳ እና ቅስቀሳ ስራዎች መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ በማነሳሳት ይህ መንግስት በስልጣን ላይ እያለ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እንደማይኖር ማስገንዘብ እንደቁልፍ ተግባር ተወስዷል።

እነዚህንና ሌሎች እኩይ ተግባራትን በመቀየስ አገር ለማተራመስ የተነሳው ህወሃት ዛሬ ላይ ታሪክ ተቀይሮበት ከአሸባሪው ሸኔ ጋር በይፋ ተጋብቶ አገር ለማፍረስ ይሰራል። በግብጽ ቴሌቭዥን እየቀረበ ሀገር የማፍረስ ቅዥቱን ይደሰኩራል። ኢዜአ

Exit mobile version