Site icon ETHIO12.COM

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ተለያዩ ሀገራት ከላከው ጭምብል 114 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አገኘ


የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለውጪ ገበያ ከላከው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል 114 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።

የፓርኩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ከተማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት 2013 ዓ.ም ለዘርፉ ከባድ ጊዜ ነበር።

መንግስት የተለያዩ አማራጮችን በማመቻቸት አምራች ካምፓኒዎች ጫናዎችን ተቋቁመው ስራቸውን እንዲያከናውኑ ለማስቻል ከፍተኛ ጥረት በማድረጉ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያነት የሚውሉ ጥራት ያላቸውን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችና ሌሎች ምርቶችን በማምረት የቫይረሱን ክስተት ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር መቻሉን ጠቁመዋል።

ፓርኩ ባለፈው በጀት ዓመት ለአውሮፓና አሜሪካ ገበያዎች ካቀረበው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል 114 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም 20 የውጭ ባለሀብቶች ቦታ ወስደው ምርት ላይ እንደነበሩ ያስታወሱት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ በኢንዱስትሪ ፓርኩ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱንም አስረድተዋል።

23 ካምፓኒዎች ስራ ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ፍጹም፤ አሁን ላይ ሶስት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሼድ ወስደው ወደ ምርት መግባታቸውን ተናግረዋል።

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለ35 ሺህ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ ዕድል መፍጠሩም ተመልክቷል።

Via EBC

Exit mobile version