Site icon ETHIO12.COM

“በዲፕሎማሲ ውጤታማ ለመሆን በቅድሚያ ሀገርን መውደድ ይጠይቃል” ፕ. ሳህለወርቅ



ዲፕሎማቶችና ሌሎች የመስኩ ባለሙያዎች በዲፕሎማሲ መስክ ውጤታማ ለመሆን በቅድሚያ ሀገራቸውን መውደድ እንዳለባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለፁ።

ፕሬዚዳንቷ ለሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር መጥተው የመጀመሪያ ዙር የአቅም ግንባታ ስልጠና ለሚወስዱ ዲፕሎማቶችና ለመስኩ ባለሙያዎች ለረጅም ዓመታት ያካበቱትን ልምዳቸውንና የህይወት ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚህ ወቅት እንደገለፁት፣ በዲፕሎማሲ መስክ ውጤታማ ለመሆን ሀገር መውደድን ይጠይቃል። የዲፕሎማሲ መስክ ሥራ ሀገርን የማገልገል ኃላፊነትን የሚሸከሙበት ሙያ በመሆኑ፣ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሀገርን ከፊት በማስቀደም የሚሰራ ነው ብለዋል።

እንደእሳቸው ገለፃ፣ የዲፕሎማሲ ሀገርን በየጊዜው የሚገጥሟትን ፈተናዎች ለማሻገር መፍትሔዎች ለማፍለቅ የሚያስችል መሆን ይገባል ነው ያሉት።

ዲፕሎማሲ እንደሲቪል ሰርቪስ ሥራ ሁሉ የመንግሥትና የሀገር ግንባታ ሥራ በመሆኑ ሀገር በመውደድ አስፈፃሚው አካል የሚያወጣውን ፖሊሲ በፅኑ ማስፈፀም ላይ ማተኮር ይገባል፤ የአላማ ፅናት፣ የአገር ፍቅር፣ እውቀትን በየጊዜው ማጎልበትና ራስን ብቁ አድርጎ መንቀሳቀስ ከዲፕሎማቶች የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።

አንድ ዲፕሎማት ሥራውን በትክክል ለመከወን ሌላውን ለመቀበልና ለመማር ክፍት የሆነ አዕምሮ ኖሮት የሚሰራበትን ሀገር ባህል፣ ቋንቋና ሌሎች ነገሮችን ማወቅ የላቀ ውጤት ለመፈፀም ወሳኝ ነው። ዲፕሎማቶች በተልእኮዎቻቸው ሁሉ የኢትዮጵያን ቀጠናዊ ሁኔታ በየጊዜው ማወቅና ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል ሲሉ አስገንዝበዋል።

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version