ኢትዮጵያ የ “50 ሚሊዮን የአፍሪካ ሴቶች ይናገሩ” ፕሮጀክትን ውጤታማ በማድረግ የመሪነት ሚናዋን ትወጣለች

ኢትዮጵያ የ”50 ሚሊዮን የአፍሪካ ሴቶች ይናገሩ” ፕሮጀክትን ውጤታማ በማድረግ የመሪነት ሚናዋን እንደምትወጣ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ። የአፍሪካ ልማት ባንክ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መመደቡን ገልጿል።

በአፍሪካ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማሳደግን ያለመ “50 ሚሊዮን የአፍሪካ ሴቶች ይናገሩ” ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ተከናውኗል።
እ.አ.አ በ2019 በርዋንዳ ኪጋሊ ይፋ የሆነው መርሃ ግብር በኮቪድ-19 ምክንያት ዘግይቶ ቆይቶ ዛሬ ተጀምሯል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ምስረታ በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መሪ መሆኗን አስታውሰው፤ “50 ሚሊዮን የአፍሪካ ሴቶች ይናገሩ” መርሃ ግብር ለማሳካት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራት ጠቁመዋል።

በመሆኑም በአፍሪካ ህብረት ምስረታና ጸረ ቅኝ ቅዛት ትግል የነበራትን ተሳትፎ በ “50 ሚሊዬን የአፍሪካ ሴቶች ይናገሩ” መርሃ ግብር በመድገም የመሪነት ሚናዋን በአግባቡ ትወጣለች ሲሉ አረጋግጠዋል።

በመርሃ ግብሩ የተቀመጠውን ሴቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያለንን ትስስር ይበልጥ እናጎለብትበታለን ብለዋል። የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ በበኩላቸው፣ በዲጂታል አለም ቴክኖሎጂ አለመጠቀም በድቅድቅ ጨለማ መጓዝ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በ”50 ሚሊዮን የአፍሪካ ሴቶች ይናገሩ” መርሃ ግብር የተቀመጠውን ሴቶችን ከአፍሪካ አቻ የስራ ፈጣሪና ነጋዴዎች ጋር በበይነ መረብ ማስተሳሰር ለነገ የማይባል ስራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

“መርሃ ግብሩ የሴቶችን የንግድና ስራ ፈጠራ በማሳደግ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ላይ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ይኖረዋል” ብለዋል። የአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱል ካማራ፤ “ሴቶች በኢኮኖሚ እድገት ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ድጋፍ ይደረጋል” ብለዋል።

ሚኒስትሯ ባንኩ መርሃ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት ለሴቶች ድጋፍ የሚያደርግበት ፕሮጀክት ነድፎ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸው፤ እ.አ.አ ከ2021 ጀምሮ ለአምስት ዓመት የሚቆይ 5 ቢሊዮን ዶላር እንደመደበ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

See also  አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት ላይ 11 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ጉዳት አድርሷል

Leave a Reply