ETHIO12.COM

የጥቁር አንበሳ መኮንኖች ፈለግ

በሀገራችን የመደበኛ ሠራዊት ምስረታ ሀሳብ በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት የተጸነሸና የተጀመረ ቢሆንም በውጭ ወራሪ ኃይልና በውስጥ ተቃውሞ ምክንያት የመደበኛ ሠራዊት ምስረታ በአጭር ሊቀር ችሏል፡፡

በአጼ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት ግን ከአንዳንድ የአውሮፓ ሀገሮች የውትድርና ባለ ሙያዎችን በማስመጣት የተሻለና የተደራጀ ሠራዊት ለመፍጠር ሙከራ ተደርጎ ነበር። በተለይም ከአድዋ ድል በኋላ የተለያዩ ከባድ መሳሪያዎች በምርኮ በመገኘታቸውና መሳሪያዎቹን ለመጠቀም ሠራዊት ለማ ደራጀትና ማሰልጠን በማስፈለጉ መደበኛ ሠራዊትን የማደራጀት መሰረት የተጣለበት ዘመን እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በኢትዮጵያ የውትድርና ታሪክ ሲነሳ ለመጀመሪያ ጊዜ አመራሮችን አሠልጥኖ ለማውጣት የተቋቋመው የገነት ጦር ትም ህርት ቤት ነው፡፡ ሆለታ የሚገኘውና ከ1989 ዓ.ም ሜ/ጄኔራል ኃየሎም ወታደራዊ አካዳሚ ተብሎ ሲጠራ የነበረው በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ተብሎ የተሰየመው የጦር ት/ቤት ከዛሬ 68 ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ 190 ያህል እጩ መኮንኖችን በአምስት ስዊድናውያን አሠልጣኞች መኮንኖች አማካይነት ለሦስት ዓመታት በማሰልጠን ሥራ ጀመረ።

ይሁን እንጂ በ1928 ዓ.ም የፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪ ጦር ሀገራችንን በመውረሩ ከአንድ ዓመት ሥልጠና በኋላ ሊያስመርቅ ተገዷል፡፡

እነዚህ የመጀመሪያ ምሩቃን ወጣት መኮንኖችም የሀገራቸውን ክብርና ነፃነት ላለማስደፈር በአርበኝነት ትግሉ ተሰልፈው የፈፀሙት አኩሪ ገድል ምንጊዜም ታሪክ ሲያስታውሰው የሚኖር ነው፡፡

May be an image of standing, outdoors and monument

ፋሺስት ኢጣሊያ በጀግኖች አባት አርበኞች ትግልና መስዋዕትነት ድል ተነስቶ ከሀገራችን ከወጣ በኋላ የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ዳግም ሥራውን እንዲጀምር ተደረገ፡፡ የዕጩ መኮንንት ሥልጠናውም ቀጥሎ በሂደት የውጭ ሀገር አሠልጣኞች በኢትዮጵያውያን ተተኩ። የማሠልጠን ተግባሩንም እስ 1979 ዓ.ም ቀጥሎ ከ1980 እስከ ደርግ መንግስት ውድቀት ድረስ ወደ መስመራዊ መኮንኖች ማሰልጠኛነት ተሸጋግሯል፡፡

ከገነት ጦር ትምህርት ቤት በመቀጠል በሀገራችን በሁለተኛነት ተጠቃሽ የሚሆነው በአዲስ አበባ ተቋቁሞ የነበረው የዕጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ¨የክብር ዘበኛ¨ ጦር ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ያቋቋሙትም ሲውድናዊያን መኮንኖች ናቸው፡፡ የጦር ትምህርት ቤቱም ለታለመለት ግብ በሦስት ዙር ሥልጠና ካካሄደ በኋላ ሥራውን አቁሟል፡፡ በወቅቱ ሰልጥነው ከወጡት መኮንኖችም ኮሪያ የዘመተውን የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ሠራዊት መርተው አኩሪ ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት የጦር ትምህርት ቤቶች መኮንኖችን እያሰለጠኑ በመውጣት የየወቅቱን ፍላጎት ያሟሉ ቢሆንም ከዓለማቀፋዊ የውትድርና ግዳጅ አወጣጥ ጋር የተዛመደና ችሎታ ያላቸውና ዘመናዊ መሣሪያዎችን ለመጠቀም የሚያስችሉ መሪዎችን ማፍራትን የግድ በማለቱ በዘርፉ ብቁ መኮንኖችን ማፍራት አስፈለገ፡፡ በዚህም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የጦር አካዳሚ በ1950 ዓ.ም በሐረር ከተማ የጦር ት/ቤቱም ¨የሐረር ጦር አካዳሚ¨ ተብሎ ተሰየመ፡፡

የጦር አካዳሚው በአንድ ጊዜ ለማሰልጠን የሚቀበላቸው ዕጩ መኮንኖች 60 ያህል ሲሆኑ፤ ለሦስት ዓመታት በወታደራዊና በቀለም ትምህርት ሠልጥነው በምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ የሚመረቁ ነበሩ፡፡ ከጦር አካዳሚው ተመርቀው ይወጡ የነበሩት ምሩቃን መኮንኖች ውጭ ሀገር ለሌላ ከፍተኛ ትምህርት ተልከውም ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉም ነበሩ፡፡

የሐረር ወታደራዊ አካዳሚው እስከ 21ኛ ኮርስ እጩ መኮንኖችን ማስመረቅ የቻለ ቢሆንም በታቀደለት የሦስት ዓመታት የማሰልጠን ሂደቱን ያከናወነው ከአንደኛ እስከ አስራ ስምንተኛ ኮርሶች ብቻ ነበር፡፡ ቀሪዎቹ ለአንድ ዓመትና ከዚያ በታች ለሆኑ ጊዜዎች የተከናወኑ ሥልጠናዎች ናቸው።

የሐረር ጦር አካዳሚ የደርግ መንግስት ሥልጣን ከተቆናጠጠ በኋላ በ1969 ዓ.ም ወታደራዊ አካዳሚነቱ ሊያከትም ችሏል፡፡ በደርግ ሥርዓት ሁርሶ መከንኖች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ተመስርቶ ከሲቪል ማህመረሰብ ወጣቶችን በመመልመል እስከአንድ ዓመት የሚደርስ ሥልጠና ይሰጥ ነበር፡፡

ከሂደቱ እንደምንረዳውም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት የተጣሉት መሠረቶች ጠንካራ ነበሩ፡፡ ይኸውም ዓላማውን ወደጎን ትተን የወታደራዊ ሥልጠናውን ጥራት ስንመለከት ከማሰልጠኛዎቹ የሚወጡት መኮንኖች ብቃትን የተላበሱ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ተጠቃሽ የሚሆነው ከሐረር ወታደራዊ አካዳሚ የሚወጡ ዕጩ መኮንኖች ወደ ከፍተኛ የትምህርት እርከኖች በማምራት በሠራዊቱ ውስጥ በጤናው፣ በቴክኒክ፣ በምህንድስናውና በወታደራዊ ጥበብ ሥልጠናው ዘርፍ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

ደርግ ለገነባው ግዙፍ ሠራዊት መሪ መኮንኖችን ለማፍራት በሺዎች የሚቆጠሩ ዕጩ መኮንኖችን በሆለታና በሐረር፣ ሁርሶ ማሰልጠኛዎች ከአንድ ዓመት ላልዘለለ ጊዜ እያሰለጠነ ያወጣ ነበር፡፡ ደርግ በሥልጣን ዘመኑ ከሶሻሊስት ሀገሮች ጋር ባለው ግንኙነት በሺህዎ የሚቆጠሩ የሠራዊት አባላትንም ለትምህርት እየመለመለ ልኮ ያሰለጥን እንደነበረም ይታወቃል። በዚህ ረገድ ሀገሪቱ በተለያየ ሙያ የሰለጠኑ ወታደራዊ ሙያተኞችን ማፍራት ችላለች፡፡ እኒህ ወታደራዊ ሙያተኞች ደርግ ከሥልጣን ቢወገድም ሀገራቸው በጠራቻቸው ጊዜ በሙያቸው ደግፈዋል፡፡ በተለይ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት ሀገርን ከጥቃት ለመከላከል የድርሻቸውን አበርክተዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወደ መደበኛ ሠራዊት የማሸጋገር ሂደቱ በተጠናከረ አኳኋን ቀጥሎም ዛሬ የመደበኛ ሠራዊትን ቅርጽ ለማስያዝ በማዕከል፣ በኮሮችና በማሰልጠኛዎች በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በተለይም የዚሁ ጥረት አጋዥና መሠረት የሆኑት አመራሮችን የማፍራቱ ሂደትም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ መሪ መኮንኖችን በማስመረቅ ሥራ ውን የጀመረው የሁርሶ መኮንኖች አካዳሚ እራሱን እያደራጀና ጎን ለጎን ሥልጠናውን ያካሂድ ነበር፡፡ ይህም ወደሚፈለገው ግብ ለመድረስ ብቃት ያላቸውን እጩ መኮንኖች ማፍራት እንደሚቻል ያመላከተ ነበር፡፡

መሪ መኮንኖችን ለማፍራት በተለይ ከ1987 ዓ.ም በኋላ የመመልመያ መስፈርት እንዲሻሻል አድርገዋል። ቀደም ሲል ለመኮንንነት የሚመለመለው ሠልጣኝ ከሠራዊቱ ብቻ ነበር፡፡ ይህ ዝግ የሆነው የመመልመያ መስፈርት ከሲቪሉ ማህበረሰብ በውትድርና ሙያ ሀገራቸውን ለማገልገል የተማሩ ወጣቶች የእድሉ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጎ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ካካሄዳቸው የሪፎርም ሥራዎች አንዱ የትምህርትና ሥልጠና ሂደትን ማሻሻል ነው፡፡ በዚህም የሠራዊቱን ማቋቋሚያ አዋጅን በማሻሻል ለመኮንንነት ሥልጠና ከሲቪሉ በቀጥታ እንዲመለመሉ እድል እንዲሰጥ አድርጓል፡፡ ወደተግባርም በመሸጋገር ሠልጣኖችን በመቀበልየመጀመሪያ ዙር ሠልጣኞችን እያሠለጠነ ይገኛል፡፡

እነዚህ ወጣት ሠልጣኞች ከካዴት ሥልጠና በኋላ በቀጣይ የተቋሙን አቅም በማሳደግ ድርሻቸው ከፍተኛ ነው፡፡

የአካዳሚው ተልዕኮ አመሰራረት

አካዳሚው በአፍሪካ የመጀመሪያው እድሜ ጠገብ የሆነ በ1930ዎቹ ገነት ጦር ተብሎ የተመሰረተ ነው፡፡ ከተመሰረተ ጀምሮ መሪ መኮንኖችን በማፍራት ስመጥር ሆኖ በማገልገል ይገኛል፡፡ መጀመሪያ እንደተቋቋመ ሲማሩ እና ሲሰለጥኑ የነበሩ መኮንኖች ጣሊያን ሀገራችንን በመውረሩ ምክንያት ትምህርት እና ሥልጠናቸውን አቋርጠው ¨የጥቁር አንበሳ ንቅናቄ” ¨Black lion movement¨ወይም በሚል ከጣሊያን ጋር ተፋልመው ታሪክ የማይሽረው በደማቅ ቀለም የተፃፉ ከፍተኛ ድልን የተጎናፀፉ ጀግኖች ወታደሮች የውጊያ አመራሮችን ያፈራ ስመጥር ተቋም ነው፡፡ ዛሬም ድረስ የተለያዩ ሂደቶችን እያለፉ መኮንኖች አሠልጥኖ እያወጣ ይገኛል፡፡

እስከ 2013 ዓ.ም ሜ/ጄኔራል ኃየሎም አርአያ ወታደራዊ አካዳሚ ተብሎ ሲጠራ የነበረውና በአሁኑ ወቅት ¨የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ¨በሚል ስያሜ በርካታ ዙር እጩ መኮንኖችን በአጭርና በረጅም ኮርሶች አሰልጥኗል፡፡ ሻለቆችን እየመሩ ድልን ያስመዘገቡ በርካታ መኮንኖች አፍርቷል፡፡

በመደበኛ ሥልጠና 15 ዙር መኮንኖችን ያሰለጠነ ሲሆን፤ በአጭር ኮርሶች 22 ዙሮችን አሠልጥኖ ያስመረቀ ወታደራዊ ተቋም ነው፡፡ አካዳሚው በሰርተፊኬት መርሀ-ግብር በዲፕሎማሲ፣ እንዲሁም አሁን በመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም ለ3 ዓመት በማስተማር ላይ የሚገኝ በሀገሪቱ ብቸኛ ወታደራዊ አካዳሚ ነው፡፡ የወታደራዊ አካዳሚው ተልዕኮዎች አሉት፡፡

ተልእኮዎቹም አንደኛው ጥራቱን የጠበቀ ትምህርትና ሥልጠና በመስጠት እና ጀማሪ ፕሮፌሽናል የሆኑ ወታደራዊ መኮንኖችን ማፍራት ሲሆን፤ ሁለተኛው ይህን ትምህርት እና ሥልጠና ሊያዳብርና ሊያሳድግ የሚችል በተቋሙ ጥናት እና ምርምር መስራት ነው፡፡ ማለትም ችግር ፈቺ ጥናት እና ምርምር በማቅረብ፤ሦስተኛው በእጩ መኮንን ትምህርት እና ሥልጠና ዙሪያ ተቋሙን የማማከር ሥራ መሥራት ነው፡፡

በዋናነት እንደማንኛውም ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እነኝህን ሦስት ተልዕኮዎች ለማሳካት በከፍተኛ ሁኔታና ተነሳሽነት ሥራ ዎችን እያከናወነ ይገኛል። ወታደራዊው አካዳሚው ከእነዚህ ተልዕኮ ጎን ለጎን ወታደራዊው አካዳሚው በ2030 በእጩ መኮንኖች ትምህርት እና ሥልጠና የልህቀት ማዕከል ለመሆን በከፍተኛ ደረጃ እራሱን አደራጅቶ እየሠራ ያለ ተቋም ነው።

ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የገጠሟትን ፈተናዎች ለማለፍ ከአካዳሚው የወጡ መኮንኖች የሚመሩትን ሠራዊት አብቅተው ተዋግተው በማዋጋት አኩሪ ጀግንነት ፈጽመዋል፡፡ እስከጄኔራል መኮንንነት በመድረስም ሠራዊት መርተዋል፡፡ እስከእስፔሻሊስት ድረስ የደረሱ ሐኪሞች፤ የአቪዬሽን ሙያተኞች፤ መሐንዲሶች ወዘተ. ከዚህ ወታደራዊ አካዳሚ የወጡ ፍሬዎች ተቋሙንም ብሎም ሀገርን ጠቅመዋል፡፡

በ1969 ዓ.ም ሶማሊያ ሀገራችንን በወረረችበት ወቅት በርካታ የተማሩ ወጣቶች በእጩ መኮንንነት ሠልጥነው ጦር መርተው ድንቅ ጀግንነት ፈጽመዋል፡፡ የአካዳሚው ፍሬዎች በሀገሪቱ የሥልጣን እርከን ውስጥ እስከአመራር ድረስ በመድረስ ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሆለታ የሚገኘው የኢትዮጵያ ወታደራዊ ተብሎ የሚጠራው የተማሩ ወጣቶችን ከሲቪሉ ማህበረሰብ በመመልመል በዲግሪ እያሰለጠነ ይገኛል፡፡ በዚህ አካደሚ ሠልጥነው የሚወጡ መኮንኖችም የነገው ወታደራዊ መሪዎች፤የልዩ ልዩ ሙያዎች ባለቤት በመሆን የተቋሙም ሆነ የሀገር አለኝታ የሚሆኑ ናቸውና የዚህ ታሪክ አካል እንሁን፡፡

አቶ በየነ በቀለ – ከመከላከያ ሚዲያ

Exit mobile version