Site icon ETHIO12.COM

በአዳማ ከ230 በላይ ፈረሶችና አህዮች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የአዳማ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በጎዳናዎች ላይ ተጥለው የሚገኙ የፈረሶች ቁጥር በየዕለቱ መጨመር ትልቅ ስጋት ሆኖብኛል ሲል ለቢቢሲ ተናገረ።

የከተማው ማዘጋጃ ቤት በከተማዋ አውራ ጎዳና ላይ ተለቅቀው የትራፊክ እንቅስቃሴን በማወክ እክል የፈጠሩ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶችን አስከትለዋል ያላቸውን ከ230 በላይ ፈረሶችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ጨምሮ ገልጿል።

የከተማዋ አስተዳደር በቁጥጥር ስር አዋልኳቸው ያላቸው ፈረሶች ብቻ ሳይሆኑ አህዮችም እንደሚገኙበት ገልጾ ባለቤቶቹ መጥተው እስኪረከቧቸው ድረስ በተዘጋጀው የመቆያ ስፍራ እንዲቆዩ መደረጉን ቢቢሲ መረዳት ችሏል።

በጉዳዩ ላይ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአዳማ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና የከተማ አገልግሎቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኮከብ አክሊሉ በከተማዋ ከሚገኙ የጋሪ ባለቤቶች ጋር በጉዳዩ ላይ ተደጋጋሚ ውይይት መደረጉን ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ በከተማ ውስጥ የሚለቀቁ ፈረሶች ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ መሆኑን ተናግረዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው እና አገልግሎት መስጠት የማይችሎ የጋሪ ፈረሶችን ወደ ውጪ አውጥቶ መጣል በከፍተኛ ደረጃ በከተማዋ የሚታይ ችግር መሆኑን አስተዳዳሪው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

“በከተማ ውስጥ ያለ ቁጥጥር የሚለቀቁት ፈረሶች እና አህዮች በከተማው ነዋሪ ማኅበረሰብ ላይ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ሲያደርሱ፤ የከተማው አስተዳደር ብዙ ገንዘብ በማውጣት ያስገነባቸው መሰረተ ልማቶች ላይ ደግሞ ጉዳት እያደረሱ ነው” ብለዋል ምክትል ሥራ አስኪያጁ። 

አክለውም “እነዚህ ፈረሶች አስፓልት መንገድ ላይ ወጥተው በመቆም መኪና እንዳይተላለፍ መንገድ ይዘጋሉ፤ ሌሊት ሌሊትም መንገዶች ላይ በመቆማቸው የሚደርሰው የትራፊክ አደጋ ቀላል አይደለም” ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የከተማው አስተዳደር ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት የአረንጓዴ ልማት ሥራ ያከናወነ መሆኑን በማንሳት በእነዚህ የጋማ ከብቶች ምክንያት በአትክልቶቹ ላይ በቀጥታ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

“የተለያዩ አይነት ዝርያ ያላቸው ሳሮች እና ተክሎች አሉ፤ ፈረሶቹን ሆነ ብለው ሌሊት በመልቀቅ እንዲበሉ በማድረግ እንዲሁም ጉዳት እየደረሰባቸው ነው። በዚህም የከተማው አስተዳደር እና ኅብረተሰቡ ያወጡት ወጪ ላይ ትልቅ ጉዳት እየደረሰበት ነው” ይላሉ።

በከተማው ውስጥ ከቁጥጥር ውጪ የሚለቀቁት እነዚህ ፈረሶች በከተማው ጽዳት ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት ባሻገር ከአንደኛው ፈረስ ወደ ሌላኛው በሽታ እያስተላለፉ መሆኑንም አቶ ኮከብ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተወሰዱ እርምጃዎች

የአዳማ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በከተማዋ ውስጥ የሚለቀቁት ፈረሶች የሚያስከትሉትን ጉዳት ወይንም ችግር አስመልክቶ ለጋሪ ባለቤቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዲሁም የተለያየ ውይይት ማካሄዱን አቶ ኮከብ ጠቅሰው ይሁን እንጂ የተፈለገው ለውጥ አለመምጣቱንም አመልክተዋል።

“ይህንን ማስተካከል ግዴታ ሆኖ በመገኘቱ፤ በአሁኑ ሰዓት በዘመቻ መልክ ሥራ ጀምረናል። በአሁኑ ወቅትም ከ230 በላይ ፈረሶችን ወደ ማቆያ ስፍራ አስገብተናል” ይላሉ።

አንዳንድ የፈረስ ባለቤቶች የተያዙባቸውን ፈረሶች ለማስለቀቅ ለከተማው ማዘጋጃ ቤት የአንድ ሺህ ብር ቅጣት እየከፈሉ እየወሰዱ መሆኑንም ይናገራሉ።

ፈረሶቹን ባለቤቶቻቸው የተቀመጠውን ቅጣት ከፍለው የማይወስዱ ከሆነ ማዘጋጃ ቤቱ ሌሎች እርምጃዎችን እንደሚወስድ አስተዳዳሪው ይናገራሉ።

ይህንንም ሲያብራሩ ባለቤት ለሌላቸው ፈረሶች በቢሾፍቱ ከተማ ከሚገኝ ስፓና (SPANA) ከሚባል ድርጅትን ጋር እያተነጋገርን እንገኛለን።

ድርጅቱ ጥቅም የማይሰጡ፣ የታመሙ እና የቆሰሉ ፈረሶችን ካለስቃይ በቀላል መንገድ ያስወግዳል። 

ጤነኛ ቢሆኑም ጥቅም መስጠት የማይችሉትን ፈረሶች ደግሞ በአርባ ምንጭ ከተማ ለሚገኝ የአዞ እርባታ ድርጅት ለአዞዎች ምግብነት እንዲሆውሉ የትስስር ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ይናገራሉ።

ጤነኛ የሆኑ እና ጥቅም መስጠት የሚችሉትን ደግሞ በተደጋጋሚ ማስታወቂያ ወጥቶም ባለቤቶቹ መጥተው ቅጣቱን ከፍለው የማይወስዱ ከሆነ ጨረታ በማውጣት ተሸጠው ገቢው ለመንግሥት እንደሚሆን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የከተማ አስተዳደሩ ሕጋዊ በሆነ መንገድ የጋሪ ፈረስ አስመዝግበው፣ የሰሌዳ ቁጥር ተሰጥቷቸው፣ በማኅበር ተደራጅተው እና መስመር ወይንም ወይንም የሥራ አካባቢ ተሰጥቷቸው እንዲሰሩ ምዝገባ መጀመሩንም የከተማዋ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ኮከብ ይናገራሉ።

የፈረስ ጋሪ ሰው እና እቃ ለማጓጓዝ በስፋት ጥቅም ላይ እንደሚውል የተናገሩት አቶ ኮከብ፣ በአዳማ ከተማ የሚገኙትን የፈረሶች ቁጥር በተገቢው መንገድ ተመዝግቦ የተሰናዳ መረጃ እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

Exit mobile version