Site icon ETHIO12.COM

በአማራ ክልል በተፈጸመ ወረራ ከ700 ሺህ በላይ ንጹሀን ዜጎች ተፈናቅለዋል

በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ከ700 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ለእርዳታ መጋለጣቸውን የክልሉ አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ለኢዜአ እንደገለጹት የጥፋት ቡድኑ ወረራ በመፈጸባቸው የክልሉ አካባቢዎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሰብአዊ ቀውስ ተፈጥሯል።

“ከሰሜን ወሎ፣ ዋግ ኽምራ፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር እንዲሁም ደቡብ ወሎ ዞኖች እስካሁን 700 ሺህ ንጹሀን ዜጎች ከመኖሪያ ቄያቸው ተፈናቅለው በደሴ፣ ኮምበልቻ፣ እብናት፣ ደባርቅ እና ባህር ዳር ተጠልለው ይገኛሉ” ብለዋል።

የክልሉ መንግስት፣ የፌደራል አካላትና የረጅ ድርጅቶች የጋራ ጥምረት በማቋቋም ከተፈናቀሉት ውስጥ 594 ሺህ 583 ለሚሆኑት የሰብአዊ ርእዳታ ለማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።

ለእነዚህ ተፈናቃዮችም እስካሁን ከ61 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል ማሰራጨት የተቻለ ሲሆን የአልባሳትና የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉንም ኮሚሽነር ዘላለም ገልጸዋል።

“ሰብአዊ ድጋፍ ሰው ለሆነ በመቸገሩ ብቻ የሚደረግ ድጋፍ ነው” ያሉት አቶ ዘላለም፣ ከተፈናቃዩ ቁጥር መብዛት አንጻር ለህጻናት፣ እናቶችና አረጋዊያን ቅድሚያ በመስጠት ሁሉንም ለመድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ አቶ ዘላለም ገለጻ ጠላት በወረራ ይዟቸው የነበሩና ነጻ በወጡ አካባቢዎች የደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት መልሶ ለማቋቋም የሚሰራውን ስራ ፈታኝ ከሚያደርጉት ሌላው የሚጠቀስ ነው።

የወደሙ የመንግስትና የማህበራዊ ተቋማትን፣ የግለሰብ ድርጅቶችን፣ ፋብሪካዎችንና ኢንተርፕራይዞችን መልሶ ለመገንባትና ለመጠገን እንዲቻል በክልል ደረጃ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደጥናት መገባቱንም ጠቁዋል።

ከወረራው ነጻ በወጡት ደቡብና ሰሜን ጎንደር ወረዳዎች፣ ውርጌሳ፣ ድሬ ሮቃ፣ ዳውንት፣ መቄትና ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ሃብትና ንብረታቸው በአሸባሪው ቡድን በመዘረፉና በመውደሙ ችግር ውስጥ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በነዚህ አካባቢ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ከዓለም ምግብና ከካቶሊክ ሪሊፍ ሰርቪስ ጋር በመተባበር 19ሺህ 396 ኩንታል የምግብ እህል እየተሰራጨ ነው።

“አሸባሪው ህወሓት እስካሁን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች መንግስት ለጊዜው መግባት ባለመቻሉ በአካባቢው የሚገኙ በርካታ ንጹሀን በምግብ እህልና በመድሃኒት እጥረት ህይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋል” ብለዋል።

በተለይም የምግብ ዋስትና ተጠቃሚ በሆኑት በሰሜን ወሎ፣ በዋግ እና በሰሜን ጎንደር የሚገኙ የሴፍትኔት ተጠቃሚዎችና ከሌሎች ክልሎች ተፈናቅለው የመጡ ከ1 ነጥብ 9 በላይ ዜጎች ህይወት በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።

“ችግሩን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለመፍታት በተደረገ ጥረት የዓለም ምግብ ፕሮግራም የምግብ እህል ቢያቀርብም የማጓጓዝና በፍትሃዊነት የማሰራጨት ስራው በሌላ አካል ስለሚሰራ መጓተት አሳይቷል ብለዋል” አቶ ዘላለም።

በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉ የቅንጅት ችግሮችን በመፍታት ለወልድያና አካባቢው የሚሆን የምግብ እህል እየተጓጓዘ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት።

ኮሚሽነሩ እንዳሉት ቀደም ሲል መንግስት ለህዝብ አገልግሎት ሲሰጥባቸው የነበሩ የእህል ማከማቻ መጋዘኖች በአሸባሪው ቡድን በመውደማቸው ችግሩን እንዲከብድ አድርጎታል።

ድርጅቶቹ ይህን ችግር ተቋቁመው በአሸባሪው ህወሓት ቁጥጥር ስር በሚገኙ የሰሜን ወሎና ዋግ አካባቢዎች ገብተው የጀመሩትን ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።

የወገናቸው ችግር ገብቷቸው በየከተማው ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ ለሚገኙ ወጣቶች፣ ለንግዱ ማህበረሰብና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ኮሚሽነር ዘላለም ምስጋና አቅርበዋል።

Via ENA

Exit mobile version