Site icon ETHIO12.COM

ኢሬቻ – ከኦሮሞ ባህላዊ እሴት አንጻር

አለማመን ቸግር አይደለም። አለማወቅ ግን ችግር ነው። ባህልን በበጎም ማወቅ ከግምትና ከደፈና አስተያየት ይጠብቃል። በርካታ የሰለጠኑ አገር ነዋሪዎች እምነት የላቸውም ግን በየአገሩ እየዞሩ ሌሎች እነደየእምነታቸው በዓላትን ሲያከብሩ ቀጠሮ ይዘው እስፍራው ላይ ይገኛሉ። የወደዱና የፈለጉ ያጠኑታል። ከኛ በላይ አገራችን ስላለው ባህልና ስርዓቱ አውቀው ድንቅ ጽሁፎችና ዶክመንታሪ ያዘጋጃሉ። እናም ማወቅ አይከፋም። በደፈናው ከመንጎድ የሌሎችን መብት በማክበርም ጭምር ለማወቅ እንጓጓ!! ጽሁፉን ያገኘነው ከኦሮሚያ ባህል ማዕከል ነው

የአንድን ማኅበረሰብ ማንነት ከሚገልጹ እሴቶች መካከል ባህል ትልቅ ሚና አለው፡፡ ባህል አጠቃላይ የማኅበረሰቡን እንቅስቃሴ ይገልጻል፡፡ ማኅበረሰቡ ከሚጠቀምባቸው ቁሳቁሶች አንስቶ አመራረቱን߹ አበሳሰሉን߹ አበላሉን߹ አለባበሱን߹ ደስታውን߹ አስተዳደሩን߹ አምልኮቱን ወዘተ. በሙሉ ይገልፃል፡፡

እንዲሁም ባህል ያለፈውን ትውልድ አኗኗር እንደመስታውት በማቅረብ ስለሚያሳይ የማኅበረሰቡ የታሪክ߹ የቋንቋ߹ የአርት߹ ልምድና ተሞክሮ ተጨባጭ መረጃ ነው፡፡ ባህል ከሰው ልጅ አኗኗር ጋር የተያያዘና የማኅበረሰብ ዕድገት ውጤት ነው፡፡ በመሆኑም የአንድ ማኅበረሰብ ባህል አደገ ማለት የማኅበረሰቡ ኢኮኖሚ አድጓል ማለት ነው፡፡ እንዲሁም የአንድ ማኅበረሰብ ባህል በለፀገ ማለት የማኅበረሰቡ የፖለቲካ ሥርዓት ዳብሯል ማለት ነው፤ የባህል ዕድገት አጠቃላይ የማኅበረሰቡ ዕድገት ስለሆነ፡፡ የሁሉም ሥልጣኔና ዕድገት ምንጩ ከማኅበረሰቡ ባህል ይመነጫል የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡

የኦሮሞ ህዝብም ከዕለት ተዕለት አኗኗሩ የዳበረና የበለፀገ ባህል߹ እሴትና ታሪክ ያለው ህዝብ ነው፡፡

ይህ ህዝብ ካለው አኩሪና ቀደምት ባህሎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ኢሬቻ ነው፡፡ ኢሬቻ ለአምላክ የሚቀርብ የምስጋና ስርዓት ነው፡፡ ለአንድ አምላክ߹ የሁሉ ፈጣሪ ለሆነ እሱ የፈጠረውን (ለምለም) ይዘው የሚያመሰግኑበት ስርዓት ነው፡፡ ይህ የኦሮሞ ምስጋና ስርዓት የዳበረ ባህላዊ እሴት አዲሱ ትውልድና ዓለምም ሊማርበት የሚችል በርካታ ቁምነገሮች አሉት፡፡

ይህ ጽሑፍም የኦሮሞ ኢሬቻ በውስጡ ከያዛቸው ባህላዊ እሴቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡

1. ሠላምና እርቅ፡፡ ኢሬቻ የሚካሄድበት ማንኛዉም ቀዬ߹ ሐይቅ ወይም ስፍራ የሰላምና የእርቅ ስፍራ ነው፡፡ በንፁህ ልብ߹ ያላንዳች ቂምና በቀል ሠላምና እርቅን የሚያውጁበት ነው፡፡ ቂምና በቀል߹ አለመግባባትና ጥላቻ ያለው ማንኛውም ግለሰብ ጥላቻውን ሳይሽር߹ እርቅ ሳያወርድ߹ የገደለ ሳይክስ߹ እጁ ንፁህ ያልሆነ ግለሰብ ወደ ኢሬቻ አይሄድም፡፡ እንደ ማኅበረሰቡ ባህልም የተከለከለ ነው፡፡ ኢሬቻ ከመድረሱ በፊት አባ ገዳዎች በየአከባቢያቸው በየደረጃው ባለው መዋቅር ያለውን ችግር ይፈታሉ፤ የተጣላውን ያስታርቃሉ፤ የገደለ እንዲክስ ያደርጋሉ፡፡ ይህም የሚሆነው ሠላምና እርቅ ኢሬቻ ካለው እሴት መካከል አንዱ ስለሆነ ነው፡፡

ስለዚህ የኢሬቻ ዕለት ሠላም ይታወጃል፤ ይወደሳል፡፡ በኢሬቻ በዓል ስለሠላም ይሰበካል፡፡ ከቤተሰብ߹ ከጎረቤት߹ ከሰፊው ህዝብ߹ ከፈጣሪና ከፍጡር ጋር በሠላም አብሮ መኖር እንደሚገባ ይታወጃል፡፡ የኢሬቻ ስፍራ እርቅ የሚታወጅበት ስፍራ ነው፡፡ የኢሬቻ በዓል የፈጣሪና የፍጡር እርቅ የሚለመንበት ስፍራ ነው፡፡ የኢሬቻ ስፍራ ማኅበረሰቡ ስለጥፋቱና ስለበደሉ ፈጣሪውን ይቅርታ የሚጠይቅበት የእርቅ ስፍራ ነው፡፡ ሳያስቡ የተጋጩ ሰዎች እንኳን እርቅ የሚያወርዱበት ነው፡፡ ስለዚህ ኢሬቻ የእርቅና የአምላክ ምህረት የሚወርድበት ስፍራ ነው፡፡ ኦሮሞ በአባባሉ ‹‹Yoo namni walitti araarame, Waaqnis namaaf araarama›› ‹‹ሰው እርስ በርሱ ከታረቀ እግዚአብሔርም ይታረቃል›› የሚለው ለዚህ ነው፡፡

በኢሬቻ ዕለት በአባ ገዳዎችና በኦሮሞ ሽማግሌዎች ምርቃት ውስጥ ሠላምና እርቅ ይወደሳል፡፡ ከዚህ በታች ያለው የኦሮሞ ምርቃት ስነቃልም ይህንኑን ያመላክታል፡፡

አፋን ኦሮሞ አማርኛ

Hayyee! Hayyee! Hayyee! ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ!

Waaqa uumaa ፈጣሪ አምላክ

Waaqa uumama የፍጡራን አምላክ

Waaqa jechuun kan hundaa አምላክ ማለት የሁሉም

Lafa jechuun kan hundaa መሬት ማለት የሁሉም

Waaqa Saglan Booranaa የዘጠኙ የቦረና ልጆች አምላክ

Waaqa Sagaltama Gabraa የዘጠናዎቹ የገብራ ልጆች አምላክ

Waaqa Torban Baarentummaa የሰባቱ ባሬንቱማ አምላክ

Waaqa Ciicoo Gurraattii የጥቁሯ ጪጮ አምላክ

Waaqa Bokkuu Gurraachaa የጥቁር ቦኩ አምላክ

Gurracha garaa garbaa ጥቁር ሆደ ባህር

Gumgumaa garaa cabbii አስገምጋሚ ሆደ በረዶ

Leemmoo garaa taliilaa ቀጥተኛ ሆደ ፀአዳ

Tokkicha maqaa dhibbaa አንዱ ባለመቶ ስም

Uumaan si kadhanna nu dhagahi ፈጣሪ ሆይ እንለምንሃለን ተለመነን

Waaqni nutti araarami አምላክ ሆይ ታረቀን

Lafti nutti araarani ምድር ታረቂን

Malkaan nutti araarami መልካው ታረቀን

Tulluun nutti araarami ተራራው ታረቀን

Ardaa Oromoo nagaa godhi የኦሮሞን አድባር ሠላም አድርግልን

Hora Oromoo nagaa godhi የኦሮሞን ሐይቅ ሠላም አድርግልን

Malkaa Oromoo nagaa godhi የኦሮሞን መልካሠላም አድርግልን

Tulluu Oromoo nagaa godhi የኦሮሞን ተራራ ሠላም አድርግልን

Qe’ee Oromoo nagaa godhi የኦሮሞን ቀዬ ሠላም አድርግልን

Ollaa Oromoo nagaa godhi የኦሮሞን ጎረቤት ሠላም አድርግልን

Gooroo Oromoo nagaa godhi የኦሮሞን አካባቢ ሠላም አድርግልን

Dachee Oromoo nagaa godhi የኦሮሞን መሬት ሠላም አድርግልን

Oromoo nagaa godhi ኦሮሞን ሠላም አድርግልን

Oromiyaa nagaa godhi ኦሮሚያን ሠላም አድርግልን

Itoophiyaa nagaa godhi ኢትዮጵያን ሠላም አድርግልን፡፡

Nageenyi badhaadha, ሠላም ብልፅግና ነው

Godaan Rooba Nagaa! ገዳ የሠላም የዝናብ!

Barri Quufaa Gabbina! ዘመኑ የጥጋብና ብልፀግና!

Gabbisi Waaq! አምላክ ሆይ አበልፅገን!

2. ይቅርታ፡፡ የኢሬቻ ቦታ ለይቅርታ ትልቅ ስፍራ ያለው ነው፡፡ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ߹ ሳያስቡበት በድንገት አለመግባባት ተፈጥሮ ከሆነ߹ የተፈጠረ ቅሬታ ካለ በኢሬቻ ዕለት ይቅር መባባል ትልቁና ዋነኛው የኢሬቻ ተምሳሌት ነው፡፡ እንደ ኢሬቻ ባህል አለመግባባትና ቅሬታ ያለው አስቀድሞ ይቅር በመባባል በንፁህ ልቦናና አእምሮ ወደ ኢሬቻ ስፍራ መሄድ አለበት፡፡ ኦሮሞ “Garaa qulqulluun, Malkaa qulqulluu bu’u”‹‹በንፁህ ልቦና ወደ ንፁህ ጅረት/መልካ/ ይወረዳል›› ብሎ በምሳሌው የሚናገረውም ለዚህ ነው፡፡ አባ ገዳው በኢሬቻ ስፍራ ‹‹ቅራኔ ያላችሁ ዛሬውኑ ይቅር ተባባሉ›› ብሎ የሚያውጀውም ለዚህ ነው፡፡

3. ምስጋና ወይም ምልጃ፡፡ የኢሬቻ ስፍራ የሚለቀስበት߹ የሚረጋገሙበት߹ የሁካታ ስፍራ ሳይሆን በንፁህ ልቦና߹ ከቂምና ጥላቻ ውጭ ፈጣሪ የሚለመንበት ወይም የሚመሰገንበት ስፍራ ነው፡፡ ኢሬቻ ያጡትን ነገር ወይም የተቸገሩበትንና የተጨነቁበትን የሚለምኑበት፤ ላገኙት ወይም ለተደረገላቸው ደግሞ አንዱ ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት ስፍራ ነው፡፡ ኦሮሞ የበጋ ወቅት በሚጠነክርበት ጊዜ߹ ድርቅ በሚበዛበት ጊዜ߹ ዝናብ ሲጠፋ߹ መጥፎ ነገር ሲከሰት߹ የተመኘውን ነገር ሲያጣና ማንኛውም ችግር በሚገጥመው ወቅት የተቀደሱ ቁሶች እንደ ከለቻ߹ ጫጩ߹ ቦኩ߹ ሲቄ߹ ጋዲና ጪጮ ያሉትን ይዞ ወደ ተራራ ወይም ወደተቀደሰው የማመስገኛ ስፍራ ወጥቶ ፈጣሪውን ይማፀናል፡፡ የበልጉ ዝናብ ሠላማዊ እንዲሆንለት ይለምናል፡፡

ኦሮሞ በተራራ ላይ ወይም በተቀደሰው ስፍራ በንፁህ ልብ ወጥቶ መርቆ߹ መርቆም በመሰዋት ‹‹ፈጣሪ ሆይ ዝነብልን߹ ፈጥረህ አትጉዳን߹ ሰጥተህ አትንሳን߹ ሰውንም ከብቱንም ጠብቅልን߹ እምቦሶችንና ቤተሰባችንን ጠብቅልን߹ አገራችንን ሠላም አድርግልን߹ የጎደለውን ሙላልን›› ብሎ ይለምናል፡፡ ኦሮሞ በተራራ ወይም በተቀደሱ ስፍራዎቹ ላይ ወጥቶ߹ ሰውቶና ፈጣሪውን ለምኖ አጥቶ አያውቅም፡፡ ይህ በተራራ የሚደረገው ልመናና ምስጋና የተራራ ኢሬቻ ይባላል፡፡

በሌላ መልኩ የመልካ ኢሬቻ በፀደይ/በብራ/ ወቅት የሚከናወንና በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ ያለው ነው፡፡ እንደሚታወቀው የክረምቱ ወቅት ዳፈና፣ ኃይለኛ ዝናብና ዶፍ የሚበዛበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ወቅት በረዶና ጭቃ የሚከፋበት ወቅት ነው፡፡ ወንዞች ሞልተው ዘመድ ከአዝማድና ቤተሰብ የሚራራቁበት ወቅት ነው፡፡ ይህ የክረምት ወቅት አልፎ ደመናው ሲገፍና መስከረም ሲጠባ ከሩቅና ቅርብ ያሉ ኦሮሞዎች በህብረት ተሰባስበው የክረምቱን ጨለማ አሳልፎ ወደ ብርሃን ያወጣቸውን አምላክ߹ ወደ መልካ ወርደው ያመሰግናሉ፡፡ ሁሉን የፈጠረ አምላክ߹ ከሁሉ ነገር ያወጣቸውን አምላክ߹ ሁሉን ነገር የዋለላቸውን አምላክ በንፁህ ልብ በማመስገን በረከትና ምርቃት ይለምናሉ፡፡ ስለውለታውም ፈጣሪን ያወድሳሉ፤ ይሰብካሉ፡፡ ፀደዩ/ብራው/ መልካም እንዲሆን߹ የዘሩትን በሠላም አጭደው የሚበሉበት እንዲሆንላቸው ይለምናሉ፡፡ ስለዚህ ኢሬቻ ትልቅ የምስጋና ወይም የምልጃ እሴት በውስጡ ይዟል ማለት ይቻላል፡፡

4. አንድነትና ወንድማማችነት፡፡ የኦሮሞን አንድነትና የብሔር ብሔረሰቦችን ወንድማማችነት ከማጠናከር አንፃር የኢሬቻ በዓል ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢሬቻ በዓል ኦሮሞ ብቻ የሚያከብረው በዓል ሳይሆን የአገራችን ብሔር ብሔረሰቦች እንደ ሲዳማ߹ ሱማሌ߹ አማራ߹ ትግሬ߹ ሀዲያ߹ ወላይታና ጋሞ ብሔሮች በዓል እየሆነ መጥቷል፡፡ የገዳ ስርዓት የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ዩኔስኮ) ቅርስነት ከተመዘገበ ወዲህ የኢሬቻ በዓል የኦሮሞና የአገሪቷ ከመሆን አልፎ ዓለም አቀፍ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይህ ደግሞ ወንድማማችነትና ከብሔር ብሔረሰቦች ጋር መቀራረብ߹ እንዲሁም የአገሪቷንና የዓለም ህዝቦች ፍቅርና አንድነት በማጠናከር በህዝቦች መካከል መተማመን እንዲኖር በማድረግ ለሀገር ሠላም ዋስትና በመሆን߹ የተረጋጋችና በኢኮኖሚ የበለጸገች አገር በመገንባት ሂደት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ያሳየናል፡፡

5. ምርቃት፡፡ የኢሬቻ ስፍራዎች የምርቃት ቦታዎች ናቸው፡፡ ምርቃት የሚገኝበት ቦታ እንጂ የሚረጋገሙበትና እርስ በርስ የሚብጠላጠሉበት ሳይሆን ታላቅ ታናሹን የሚመርቅበት߹ ታናናሾች ደግሞ ከአባ ገዳዎችና ከሽማግሌዎች ምርቃት የሚቀበሉበት ስፍራ ነው፡፡ በኢሬቻ አርሶ አደሩ߹ ነጋዴው߹ አስተማሪው߹ አርቲስቱ߹ ተመራማሪው߹ ተማሪው߹ መንግስትና የፖለቲካ አመራሮች በስራቸው ውጤታማና ፍሬያማ እንዲሆኑ ምርቃት የሚያገኙበት ስፍራ ነው፡፡

6.ፍቅር፡፡ የኢሬቻ ስፍራዎች በፍቅር የተሞሉ ናቸው፡፡ ኢሬቻ ጥላቻና መገለል የሚሰበክበት ቦታ ሳይሆን ፍቅር የሚሰበክበት ስፍራ ነው፡፡ በኢሬቻ ፈጣሪ ከፍጡር ጋር እንዲስማማ߹ ትልቅ ከትንሹ ߹ ሀብታሙ ከድሃው߹ ጎረቤት ከጎረቤት߹ ጎረቤት ከአካባቢው ማኅበረሰብ߹ ማኅበረሰብ ከማኅበረሰብ߹ አገር ከዓለም ጋር በፍቅር አብሮ እንዲኖር የሚሰበክበት ስፍራ ነው፡፡

7.መልካም ምኞትና ተስፋ፡፡ ኢሬቻ ካሉት እሴቶች መካከል ተስፋና መልካም ምኞት አንዱ ነው፡፡ በኦሮሞ ዘንድ የፀደይ/የብራ/ ወቅት ብሩህና የደስታ ወቅት ነው፡፡ የመላው ኦሮሞ ቀዬ߹ ጓዳውና አካባቢው በተስፋና በመልካም ምኞት የሚሞላበት ወቅት ነው፡፡ በፀደይ/በብራ/ወቅት ዘመድ ከአዝማዱ ያለምንም ችግርና ሀሳብ ከያለበት ተሰባስቦ የሚጠያየቅበት߹ የተዘራው በቅሎ የሚያብብበት߹ ያበበው አሽቶ መልካም ፍሬ የሚያፈራበት߹ ያፈራውም የሚበላበት ወቅት ነው፡፡ ፀደይ/ብራ/ መልካም ሽታ ያለው߹ ለማንኛውም ማኅበራዊ እንቅስቃሴ የሚመች߹ የተስፋና የምኞት߹ ጥጋብና ብልፅግና የሚሰበክበት ወቅት ነው፡፡ በኢሬቻ ቀን ላለፈው ምስጋና ይቀርባል፣ ለወደፊቱ ተስፋ ይሰነቅበታል፡፡ እነዚህ ሁለቱ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ አገር አስፈላጊ እሴቶች ናቸው፡፡ይህም ኢሬቻ የወደፊት ተስፋና መልካም ምኞት የሚያመላክት መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

8.የማኅበረሰብ ወግ (ሰፉ)፡፡ ኦሮሞ ሲተርት ‹‹Safuun seera qananiiti›› ይላል፡፡ በግርድፉ ሲተረጎም የማኅበረሰብ ወግ (ሰፉ) የክብር ወይም የቅድስና ህግ ነው እንደማለት ነው፡፡ ከዋቄፈና እና ከአጠቃላይ የኦሮሞ ባህላዊ እሴት አንፃር ሐይቅ፣ ጅረት/መልካ/፣ ተራራ፣ የኢሬቻ ስፍራዎች የተቀደሱና የተከበሩ ናቸው፡፡ አይሸናባቸውም፣ አይፀዳዱባቸውም፣ ቆሻሻ አይጣልባቸውም፤ ነውር ነው፡፡ በዚህ ስፍራ መጣላት፣ ሁካታ መፍጠር፣ መራገም፣ መነቃቀፍ ከባህል የወጣ/ነውር/ ነው፡፡ እንደ ኢሬቻ እሴት እነዚህ ስፍራዎች የሠላም፣ የእርቅ፣ የፍቅር፣ የምስጋና ስፍራዎች በመሆናቸው ነው፡፡ ይህ የማኅበረሰብ ወግ (ሰፉ) የምድርና የሰማይ ህግ በመሆኑ በኦሮሞ ዘንድ ትልቅ ስፍራ አለው፡፡ እንደ ኢሬቻ እሴትም እንደ ሆቦና ጮራ (ታላቅና ታናሽ) ክብር የሚሰጣጡበት ነው፡፡ ታናሽ ታላቁን ያከብራል፡፡ ይደማመጣሉ፤ ይቻቻላሉ፡፡ ሁሉም ሊደረግለት የሚገባውንና ሊደረግለት የማይገባውን፤ መሆን ያለበትንና መሆን የሌለበትን ያውቃል፡፡ ይህ የኦሮሞ ወግ (ሰፉ) ነው፡፡ ስለዚህ ኢሬቻ በታላቅ ወግና ስርዓት የሚከናወን ነው፤ ከእሬቻም ትልቅ ወግና ስርዓት ይቀሰማል፡፡ ትንሹ ትልቁን ሲያከብር፣ ትልቁም ለትንሹ ምሳሌ ሲሆን ወጣቶች የኣያት ቅድመ አያቶቻቸውን ወግ ከአባ ገዳዎችና ከሽማግሌዎች የሚማሩበት ነው፡፡

በአጠቃላይም ኢሬቻ በአኩሪና የዳበረ እሴት የተሞላ ነው፡፡ ኢሬቻ እርቅና ሠላም የሚሰበክበት ስፍራ ነው፡፡ ኢሬቻ በይቅርታ እሴት የታጀበ ነው፡፡ የኢሬቻ ስፍራ የኦሮሞ አንድነት የሚጠነክርበት፣ የሚወደስበት፤ የብሔር ብሔረሰቦች ወንድማማችነት የሚጠነክርበት ስፍራ ነው፡፡ ኢሬቻ በንፁህ ልቦናና አእምሮ ፈጣሪ አምላክ የሚለመንበትና የሚመሰገንበት ስርዓት ነው፡፡ ኢሬቻ በምስጋና፣ በፍቅር፣ በተስፋና በመልካም ምኞት የዳበረ ነው፡፡ ለዚህ ነው በጠንካራ ወግና ስርዓት የሚከናወነው፡፡ በርካታ ወግና ስርዓቶችም የሚቀሰሙበት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ምንጭ: የኦሮሞ ባህል ማዕከል

Exit mobile version